135 ድርጅቶች ወደ ትግራይ እንዲገቡ ተፈቀደ

የሰላም ሚኒስቴር
አሥራ አንዱ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ናቸው
ኢዛ (ረቡዕ የካቲት ፲፯ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. February 24, 2021)፦ በትግራይ ክልል ውስጥ የሰብአዊ እርዳታ ለማድረግ ጥያቄ ላቀረቡ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ሚዲያዎች ወደ ትግራይ እንዲገቡ ፍቃድ መሰጠቱ ተገለጸ።
የሰላም ሚኒስቴር ዛሬ ረቡዕ የካቲት 17 ቀን 2013 ዓ.ም. እንዳስታወቀው፤ የሰብአዊ እርዳታ እንዲያደርጉ ፍቃድ የተሰጣቸው ለ135 ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና ሠራተኞች ናቸው። ከእነዚህ ፍቃድ ከተሰጣቸው ውስጥ አሥራ አንዱ ዓለም አቀፍ መመዘኛ ያሟሉ ሚዲያዎች ናቸው። በውሳኔው መሠረት ወደ ትግራይ ክልል በመግባት የሰብአዊ ድጋፍ ሒደቱን እንዲያግዙ እና እንዲዘግቡ ፈቃድ የተሰጠ ስለመኾኑ መረጃው አመልክቷል።
መንግሥት ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውና ቀደም ሲል በሴፍቲኔት ፕሮግራም ታቅፈው ድጋፍ ይደረግላቸው የነበሩ 1.8 ሚሊዮን (አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን) ዜጎችን ጨምሮ፤ የ2.5 ሚሊዮን (ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን) ዜጎች ልየታ ተደርጎ እንደነበር የሰላም ሚኒስቴር በዚሁ መረጃው የጠቀሰ ሲሆን፣ ኾኖም በማንኛውም ሁኔታ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል የተባሉ ወገኖችን በማካተት ለ3.1 ሚሊዮን (ለሦስት ነጥብ አንድ ሚሊዮን) ወገኖች ድጋፍ ማድረግ መቻሉን ገልጿል። (ኢዛ)