የጥይት ገበያ?
በኮምቦልቻ ከተማ በሕገወጥ መንገድ ለግብይት ቀርበው በቁጥጥር ሥር የዋሉት ጥይቶች
ሁለት ሺሕ የክላሽንኮቭ ጥይት ሲገበያዩ የነበሩ እጅ ከፍንጅ ተያዙ
ኢዛ (ቅዳሜ የካቲት ፳ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. February 27, 2021)፦ ሁለት ሺሕ የክላሽንኮቭ ጥይቶችን በድብቅ ሲገበያዩ የተገኙ ሦስት ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የኮምቦልቻ ከተማ ፖሊስ አስታወቀ።
በደቡብ ወሎ ዞን ኮምቦልቻ ከተማ ቀበሌ ሦስት በሚገኝ አንድ መኖሪያ ቤት ውስጥ በድብቅ የጥይት ግብይቱን ሲፈጽሙ ነበር የተባሉት ግለሰቦች እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል።
ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት በሕብረተሰቡ ጥቆማ ነው ተብሏል። በሕገወጥ መንገድ በጥይቶቹ ግብይት ተሳትፈዋል የተባሉትና በቁጥጥር ሥር የዋሉት ደላላ፣ ሻጭና ገዥ መኾናቸው ታውቋል።
ግለሰቦቹ በአሁኑ ወቅት በቁጥጥር ሥር ኾነው ምርመራ እየተደረገባቸው ነው። (ኢዛ)



