የዘገየው የ40/60 ቤቶች ርክክብ
የ40/60 መኖሪያ ቤቶች
የዘገየው የ40/60 ቤቶች ርክክብ ዘግይቶም ያላለቀ ቤት ይረከባሉ መባሉ አነጋጋሪ ኾኗል
ኢዛ (ሰኞ የካቲት ፳፱ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. March 8, 2021)፦ የርክክብ ጊዜው የዘገየው የ40/60 ባለእድለኞች ዛሬ ቁልፍ መረከብ መጀመሩ ተገለጸ። ግንባታቸው የዘገየው የ40/60 መኖሪያ ቤቶች በተለያየ ዙር ለባለእድለኞች እጣ የወጣ ቢኾንም ቤቱን መረከብ ሳይችሉ ለዓመታት ቆይተዋል። ይህም ለግንባታው ሙሉ ለሙሉ የከፈሉ የቤት ፈላጊዎችን ሲያማርር መቆየቱ አይዘነጋም።
ዛሬ ሰኞ የካቲት 29 ቀን 2013 ዓ.ም. በወጣው መረጃ ግን በሁለተኛ ዙር እጣ የወጣላቸው ባለእድለኞች የቁልፍ ርክክብ እየተደረገላቸው ነው።
ርክክቡን አስመልክቶ የተላለፈው መረጃ የተላለፉት ቤቶች የግንባታ አፈጻጸማቸው የተሻሉትን ቤቶችን ነው።
በዛሬው ርክክብ የተደረገው በሃያት አካባቢ 49 ማዞሪያ ሳይት ባለው የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሲሆን፤ በቦታው ለባለእድለኞች ቁልፉን ያስረከቡት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር ዓባይና የአዲስ አበባ ከተማ የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መስከረም ዘውዴ ናቸው።
የአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬተርያት ቢሮ እንዳመለከተው ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን በየቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ በሚያወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ባለእድለኞች የቤቶቹን ቁልፍ እንደሚያስረክቡ ገልጿል።
በሁለተኛው ዙር እጣ ከወጣባቸው 11 ሳይቶች የግንባታ ሥራቸው ከ220 ሕንፃዎች ቁልፋቸውን የሚረከቡ ባለእድለኞችም የቤቱን ቀሪ የማጠናቀቂያ ሥራዎች ማሠራት የሚችሉ መኾኑን በቁልፍ ርክክቡ ፕሮግራም ላይ ስለመገለጹ ይኸው የቢሮው መረጃ ያስረዳል።
ይህም አሁንም እየተላለፉ ያሉት ቤቶች የማጠናቀቂያ ሥራ የሚቀራቸው መኾኑን የሚያመላክት ሲሆን፣ ባለእድለኞች ያላለቀ ቤት እንዲረከቡ መደረጉ ግን አነጋጋሪ ኾኗል።
በመጀመሪያ ዙር ላይ የተካተቱ 220 ሕንፃዎች የሚገኙበት የግንባታ ሳይቶች ዝርዝር እንደሚከተለው ቀርቧል።
መሪ ሎቄ (14 ሕንፃዎች)፣ እህል ንግድ (5 ሕንፃዎች)፣ ሕንፃ አቅራቢ (8 ሕንፃዎች)፣ አስኮ (13 ሕንፃዎች)፣ አያት 1 ሳይት 1 (14 ሕንፃዎች)፣ አያት 1 ሳይት 2 (38 ሕንፃዎች)፣ አያት 1 ሳይት 3 (41 ሕንፃዎች)፣ አያት 1 ሳይት 4 (39 ሕንፃዎች)፣ ፊሚት (8 ሕንፃዎች)፣ ቦሌ ቡልቡላ ሎት 1 (27 ሕንፃዎች)፣ ቦሌ ቡልቡላ ሎት 2 (13 ሕንፃዎች)። (ኢዛ)



