በፓርላማ አዲስ አበባ ካላት 23 መቀመጫዎች ብልጽግና ለ22ቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናትና ታዋቂ ሰዎችን በእጩነት አቀረበ
 
		ከግራ ወደቀኝ ከላይ፤ ዶ/ር ሊያ ታደሰ፣ ዶ/ር ይናገር ደሴ፣ ዶ/ር ኢንጂንየር ስለሺ በቀለ። ከታች ከግራ ወደ ቀኝ፤ ዳግማዊት ሞገስ፣ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፣ ዛዲግ አብርሃ
ዶ/ር ይናገር ደሴ፣ ዶ/ር ሊያ ታደሰ፣ ዳግማዊት ሞገስ፣ ዶ/ር ኢንጂንየር ስለሺ በቀለ፣ ዛዲግ አብርሃ፣ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፣ … ይገኙበታል
ኢዛ (ሰኞ መጋቢት ፮ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. March 15, 2021)፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥን ጨምሮ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ እያገለገሉ ያሉ ባለሥልጣናት የብልጽግና ፓርቲን በመወከል ለፌዴራል ፓርላማ እንዲወዳደሩ የአዲስ አበባ እጩ ኾነው ምርጫ 2013 ቀረቡ። ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዲስ አበባ 23 መቀመጫዎች ያሏት ሲሆን፤ ብልጽግና 22 እጩዎቹን ማቅረቡ ታውቋል።
የብልጽግና ፓርቲ ለፌዴራል ፓርላማ ከአዲስ አበባ እጩ ኾነው የሚወዳደሩ አባላቱን ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት፤ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ የኾኑት ዶ/ር ይናገር ደሴ፣ የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ፣ የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስ፣ የውኃ ሀብት ልማት ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢንጂንየር ስለሺ በቀለ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ሚኒስትር ዛዲግ አብርሃ ይገኙበታል።
ከሚኒስትሮች ሌላ እጩ ኾነው የቀረቡት ሌሎች ብልጽግናን ወክለው ከሚወዳደሩት ውስጥ፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፣ የገንዘብና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታዋ ወ/ሮ ያስሚ ወሃቢ፣ የኢትዮ ኢንጂንየሪንግ ግሩፕ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂንየር ሕይወት ሞሲሳ፣ የቀድሞ የሣይንስና ከፍተኛ የትምህርት ሚኒስትር የነበሩት ፕ/ር ሒሩት ወልደማርያም፣ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሳሃረላ አብዱላሂ፣ የአገር አቀፍ ትምህርት ምዘና ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ዲላሞ ኦቶሬ፣ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ስንታየሁ ወልደሚካኤል ተጠቃሽ ናቸው።
ከእነዚህ ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ካሉ ባለሥልጣናት ሌላ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነትና በተመራማሪነት እያገለገሉ ያሉት ፕ/ር ኢያሱ ኤልያስ፣ ዶ/ር ሃይረዲን ተዘራ፣ ረዳት ፕ/ር እንዳልካቸው ሌሊሳ፣ ዶ/ር ትእግሥት ዋሐቢ ብልጽግናን ወክለው ለፓርላማ የሚወዳደሩ ሲሆን፤ የኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ብርሃነ መስቀል ጠናም ለፓርላም እንደሚወዳደሩ ታውቋል።
ቀሪዎቹ ፓርቲው ለፓርላማ እንዲወዳደሩለት ያቀረባቸው ደግሞ ወ/ሮ ሙሉ ይርጋ (የልደታ ክፍለ ከተማ ሴቶችና ሕጻናት ኃላፊ)፣ ዶ/ር ኢንጂንየር ወንድሙ ተክሌ (የውኃና መስኖ ኢነርጂ ሚኒስቴር የመስኖ ልማት ኮሚሽነር)፣ አቶ መሐመድ ከማል አልአሩሲ (ጋዜጠኛ)፣ ዶ/ር ቤተልሔም ላቀው (ዴንታል ሰርጂን)፣ አምባሳደር ዶ/ር ቶፊቅ አብዱላሂ (የግል ባለሀብት) ናቸው።
ምንም እንኳን አዲስ አበባ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) 23 መቀመጫዎች ያሏት ቢሆንም፤ ከላይ ስማቸው የተዘረዘረውና ብልጽግና ፓርቲ በቴሌግራም ካሰራጨው የእጩዎች ስም ዝርዝር 22 ብቻ ነው። ለ23ኛው መቀመጫ ብልጽግናን ወክሎ የቀረበው እጩ እስካሁን ማን እንደኾነ ያልታወቀ ሲሆን፤ ምናልባትም 23ኛው እጩ በግል የሚወዳደር ግለሰብ ሊኾን እንደሚችል ይገመታል። (ኢዛ)



