የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጠንከር እና መረር ያለ መግለጫ አወጣ
ብልጽግና ፓርቲ
- የአማራና የኦሮሞ ሕዝብ ከብልጽግና ፓርቲም በላይ ነው
- የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤትን ጨምሮ ሁሉም የዴሞክራሲ ኃይሎች ለችግሩ ተደማሪ ችግር ከመኾን ይልቅ መፍትሔው ላይ በመተባበርና በመረባረብ ዘላቂ መፍትሔ እንዲመጣ መታገል ይኖርብናል
ኢዛ (ሐሙስ መጋቢት ፲፮ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. March 25, 2021)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ማብራሪያ የሰጡበትንና ባለፈው ማክሰኞ መጋቢት 14 ቀን የተካሔደውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባን ተከትሎ፤ የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጠንከር እና መረር ያለ መግለጫ አውጥቷል። በተለይም በሰሜን ሸዋ የደረሰው እልቂት “በኦሮሞ ዘር ላይ ያተኮረ” ነው ያሉ የኦሮሞ ብልጽግና የፓርላማ አባላትን ተከትሎ መግለጫው እንደወጣ ተገምቷል።
መግለጫው፤ “የአማራና የኦሮሞ ሕዝብ ከብልጽግና ፓርቲም በላይ ነው። ሕዝቡ ፓርቲዎችንና ፖለቲከኞችን ፈጠራቸው እንጂ በፓርቲዎችና በፖለቲከኞች የተፈጠረ ሕዝብ የለም። ስለኾነም ከሕዝብ ፍላጎት በተቃራኒ የሚደረግን ማንኛውም እንቅስቃሴ ፓርቲያችን በጽኑ ያወግዛል።” በማለት ጠንከር ያለ መልእክቱን በተለይም ለኦሮሞ ብልጽግና አስተላልፏል።
ፓርቲው ባወጣው በዚሁ ባለአምስት ነጥብ የአቋም መግለጫው ላይ፤ “የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤትን ጨምሮ ሁሉም የዴሞክራሲ ኃይሎች ለችግሩ ተደማሪ ችግር ከመኾን ይልቅ መፍትሔው ላይ በመተባበርና በመረባረብ ዘላቂ መፍትሔ እንዲመጣ መታገል ይኖርብናል” ብሏል።
አያይዞም፤ “በአካባቢው ኦነግ ሸኔ የለም ብሎ መበየን ለብዙ ትርጉም ስለሚያጋልጥ ከእርባና ቢስ ሙግት ወጥተን በታሪክ አጋጣሚ እጃችን ላይ የወደቀውን የሕዝብ አደራ በማስተዋልና በብልሀት እየተወጣን አገራችንንና ሕዝባችንን እንደመዥገር ተጣብቆ እየተፈታተናት ከሚገኝ ጽንፈኝነት አንጻራዊ ነፃነታችንን መጠበቅ ይኖርብናል ብለን እናምናለን” ሲል መረር ያለ አቋሙን የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ገልጿል። ፓርቲው ያወጣውን ሙሉ መግለጫ እንደወረደ ከዚህ በታች አስፍረነዋል። (ኢዛ)
"የአማራና የኦሮሞ ሕዝብ አንድ ነው" የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት
(መጋቢት 14 ቀን 2013 ዓ.ም) - የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ አውጥቷል። ሙሉ መግለጫው ቀጥሎ ይቀርባል።
በክልላችን ሰሜን ሽዋ ዞንና ኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን በወንድማማቾች መካከል የተለኮሰው እሳት ሳይጠፋ፣ የወደቁ የንጹሐን አስከሬኖች ሳይነሱ፣ የወደመው ንብረት፣ የተቃጠሉ ቤተ እምነቶችና መኖርያ ጎጆዎች፣ በጥፋት መልእክተኞች የተቀጣጠለው ሰደድ እሳት የለበለባቸው የእህል ክምሮችና የእንስሳት መኖዎች በውል ሳይለዩ፣ የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት እራሱ ከሳሽና ፈራጅ የኾነበትን መግለጫ ለተመለከተ ሰው ፖለቲካችን ገና በአዝጋሚ የለውጥ ሒደት ውስጥ የሚገኝ፣ የምንመራውን ሕዝብ የማይመጥን፣ ከአገርና ከሕዝብ ክብር በእጅጉ ወርዶ ጫማችን ስር የሚገኝ መኾኑን ያረጋግጣል።
የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት አካባቢው በችግር የታመቀ፣ ውስብስብ አደጋ ያለበትና የኦነግ ሸኔ እንቅስቃሴ የሚጫነው መኾኑን ከብሔረሰብ ዞኑ ብልጽግና ጽሕፈት ቤት ጋር በተደጋጋሚ የገመገመው የአደረ አጀንዳ መኾኑን ያስታውሳል።
ይህ ብቻ ሳይኾን በተደጋጋሚ በተወሰዱ ስምሪቶች እርምጃ የተወሰደባቸው፣ በቁጥጥር ስር የሚገኙና በጥብቅ የሚፈለጉ የኦነግ ሸኔ አባላት መኖራቸው አዲስ መረጃ አይደለም።
ችግሩ በተፈጠረባቸው ሁሉም አካባቢዎች ክልሉን ጨምሮ የሁለቱም ዞኖች አመራሮች ለተከታታይ ቀናት ባደረጉት እልህ አስጨራሽ ትግል አካባቢው ሰላማዊ መኾኑና የእርስ በእርስ መተማመን የተፈጠረበት ምህዳር መኖሩን ፓርቲያችን ይገነዘባል።
ይሁን እንጂ ኦነግ ሸኔና መሰል ጽንፈኛ ኃይሎች በተደጋጋሚ በሚለኩሱት እሳት በአካባቢው ነዋሪዎችና ከአጎራባች የአፋር ክልል ነዋሪዎች ጋር ተደጋጋሚ ትንኮሳዎች እንደነበሩ ያልተቋረጠ ክስተት ነው።
በተመሳሳይ በአካባቢው ስውር ሥልጠናዎችና አደረጃጀቶች እንዳሉ፣ በሒደትም ለንጹሐን አመራሮች ሳይቀር አደጋ ሊሆን እንደሚችል ከዞኑ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በግልም በጋራም ሳይነሳ ያለፈበት ጊዜ አልነበረም።
አልፎ አልፎም በጥቂት የዞኑ አመራሮች ላይ የሚስተዋለውን የሁለት ክልል አመራር የመምሰል ዝንባሌን ለማስተካከል ትግል ተደርጓል።
ይህ ሁሉ ጥሬ ሐቅ ባለበት ነባራዊ ሁኔታ የአማራ ልዩ ኃይል ከአካባቢው መንቀሳቀሱንና ፓርቲያችን ሥልጠና መጀመሩን ከህቡዕ አደረጃጀታቸው የተረዱ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ለተነሱለት የጥፋት ዓላማ ስኬት ያግዘናል ያሉትን ዘዴ ተጠቅመው የሃይማኖት መሪና የአገር ሽማግሌ በመግደል ግጭት መጀመራቸው የማይካድ ሐቅ ነው።
የአካባቢው ጉምቱ ሽማግሌዎች ችግሩን በጥንቃቄ ተመልክተው በእርቅ ለመፍታት የተስማሙ ቢኾንም "ሰዶ ማሳደድ ቢያምርህ ዶሮህን በቆቅ ለውጥ" እንዲሉ ከባድ መሳርያና ተወርዋሪ ቦንብ እስከአፍንጫው የታጠቀ የኦነግ ሸኔ ሰራዊት አካባቢውን ከልክ በላይ በመውረር ድንገተኛ ጥቃት በመፈጸም በሰውና በንብረት ላይ ከፍተኛ ውድመትና ዘረፋ ፈጽሟል።
ይህንን ኃይል መመከት ተፈጥሯዊ መብት ቢኾንም ቅሉ በአካባቢው የተሸረበው ሴራ ለጠላት የሚመች ስለኾነ ችግሩን በጋራ ከመታገል ይልቅ ጽንፈኛ ሚዲያዎችንና የረዥም ዕይታ ችግር ተጠቂ የኾኑ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በመጠቀም መፈራረጅን ያስቀደመ የአመራር ብልሽት አጋጥሟል።
የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ያወጣው መግለጫም ከችግር ፈቺነቱ ይልቅ የአእምሮን ሚዛን ያልጠበቀ ችኩልነት የሚጫነው፣ ተራ ውግንና ያጠላበት ኃላፊነት የጎደለው መግለጫ ሆኖ አግኝተነዋል። ስለኾነም የሚከተለውን ባለአምስት ነጥብ መግለጫ አውጥተናል።
1. በሰሜን ሽዋ ዞንና በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ወንድማማቾች መካከል ኦነግ ሸኔና የተልዕኮው ምርኮ የኾኑ ግለሰቦች የፈጠሩትን ድንገተኛ ጥቃት እያወገዝን ጥቃቱን ተከትሎ በሕይወታቸው፣ በአካላቸውና በንብረታቸው ጉዳት ለደረሰባቸው የፌዴራልና የክልላችን የጸጥታ አካላት እና ወንድማማቾች ሁሉ መጽናናትን እንመኛለን።
ፓርቲያችን የአማራ ብልጽግና ጽሕፈት ቤትም ጉዳት የደረሰባቸው የክልላችን ነዋሪዎችን ለማቋቋም እንደወትሮው ሁሉ በጽናት ይታገላል።
2. የአማራና የኦሮሞ ሕዝብ የበርካታ ክፍለ ዘመናት ትስስርና ውህደት ያላቸው፣ ክፉና ደግ የኾነውን የታሪክ አቀበት አብረው የወጡ፣ ረዥሙን የሕይወት መንገድ ተጉዘው አገር ያቀኑ፣ ማንም ባለጊዜ ሊነጣጥላቸው ከቶ የማይችል ውሁድ ሕዝብ ናቸው።
ስለኾነም ሕዝብን መያዣ በማድረግ የግጭት ነጋሪት መጎሰም ለማናችንም ስለማይጠቅም የጋራ ጠላታችንን በጋራ እንድንታገል ለሁሉም ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ጥሪ እናቀርባለን።
3. የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤትን ጨምሮ ሁሉም የዴሞክራሲ ኃይሎች ለችግሩ ተደማሪ ችግር ከመኾን ይልቅ መፍትሔው ላይ በመተባበርና በመረባረብ ዘላቂ መፍትሔ እንዲመጣ መታገል ይኖርብናል። በተፈጠረው ችግር የደረሰ ያልተገባ ጉዳት አለ ከተባለ የሚመለከተው አካል ገብቶ ጉዳዩን እንዲያጣራና በኃላፊነት ስሜት ችግሩ እልባት እንዲያገኝ ማድረግ የፓርቲያችን ተልዕኮ ነው። ከዚህ ውጪ በተመሳሳይ የአገር ሉዓላዊነትን በመጠበቅ ሕዝብና መንግሥት የሰጠውን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት በበርካታ ግንባሮች ተሰልፎ ለሕይወቱ ሳይሳሳ አኩሪ ተጋድሎና የሕይወት መሥዋእትነት እየከፈለ ያለን የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ መውቀስና ተጠያቂ ማድረግ ፍጹም ነውር ከመኾኑም በላይ የልዩ ኃይላችንንም ኾነ የሚሊሻችንን ክብር የማይመጥን ፍረጃ እንደኾነ ልናሰምርበት እንፈልጋለን።
በተመሳሳይ በአካባቢው ኦነግ ሸኔ የለም ብሎ መበየን ለብዙ ትርጉም ስለሚያጋልጥ ከእርባና ቢስ ሙግት ወጥተን በታሪክ አጋጣሚ እጃችን ላይ የወደቀውን የሕዝብ አደራ በማስተዋልና በብልሀት እየተወጣን አገራችንንና ሕዝባችንን እንደመዥገር ተጣብቆ እየተፈታተናት ከሚገኝ ጽንፈኝነት አንጻራዊ ነፃነታችንን መጠበቅ ይኖርብናል ብለን እናምናለን።
4. በክልላችን የተፈጠረው ይህ ችግር በአገር አቀፍ ደረጃ እየተፈታተነን የቆየው ተረፈ ትህነግ ሰንኮፍ እንጂ አዲስ ጉዳይ አይደለም። ችግር በተፈጠረ ቁጥር የአማራንና የኦሮሞን ሕዝብ በማጣላት ትርፍ ለማግኘት የሚደረገው እንቅስቃሴ እንኳንስ የምርጫ ድባብ ተጭኖት ይቅርና ወትሮም ቢኾን የሥልጣን ጥም ለሚፈታተናቸው ሱሰኞች ሰርግና ምላሽ ነው። ሕዝብ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ፍላጎት በላይ ነው።
የአማራና የኦሮሞ ሕዝብ ከብልጽግና ፓርቲም በላይ ነው። ሕዝቡ ፓርቲዎችንና ፖለቲከኞችን ፈጠራቸው እንጂ በፓርቲዎችና በፖለቲከኞች የተፈጠረ ሕዝብ የለም። ስለኾነም ከሕዝብ ፍላጎት በተቃራኒ የሚደረግን ማንኛውም እንቅስቃሴ ፓርቲያችን በጽኑ ያወግዛል።
5. ሕዝብን በመያዣነት የሚጠቀም የፖለቲካ ፍልስፍናና መንግሥታዊ እንቅስቃሴ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲቆም በአጽንኦት እናሳስባለን። ኢትዮጵያ የመላ ኢትዮጵያውያን ናት። የፌዴራል መንግሥትና ፓርቲያችን ብልጽግና የሚያደርጉትን ያልተቋረጠ ትግል በውል እንረዳለን። የሁሉም ክልሎች ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤቶችም ኾኑ የየብሔራዊ ክልሎች መንግሥታት በየቦታው የሚፈነዳውን ችግር ለመቆጣጠር እልህ አስጨራሽ ትግል ውስጥ እንዳሉም ፓርቲያችን ይገነዘባል። ይሁን እንጂ ችግር በተፈጠረ ቁጥር በንጹሐን ዜጎች ላይ የሚደርሰው ዛቻና ማስፈራርያ፣ ራሱን እንኳ ከቅርብ አደጋ እንዳይከላከል የሚፈጸምበት መድሎና ወከባ፣ በነፃነት እንዳይንቀሳቀስና በፓርቲ ማዕቀፍ ተካቶ ትግል እንዳያደርግ የሚፈጸምበት ግፍና መድሎ ከእስከአሁኑ ይልቅ የወደፊቱ ያሳስበናል። ስለኾነም እርስ በእርስ መተራረማችንን ባንጠላውም ፓርቲያችን ትክክለኛ የሕዝብ ፓርቲ ሆኖ ነጥሮ እንዲወጣ ለሁሉም ዜጎች የተመቸ የፖለቲካ ምህዳር መፍጠር አለበት ብለን እናምናለን። በጽናት የምንታገለውም ለዚህ ነው። ከዚህ ውጭ ያሉ ሁሉም አማራጮች ለማናችንም የማይጠቅሙ፣ የጊዜ ጉዳይ ካልኾነ በስተቀር ሁላችንንም የሚጎዱና ወደተጠያቂነት አደባባይ የሚያደርሱ ስሁት መንገዶች ናቸው።
በመጨረሻም የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት የብልጽግና ፓርቲ አካል እንጂ የተነጠለ ቅርጽም ኾነ ይዘት የሌለው በአገር አቀፍ ትግል ውስጥ ወሳኝ ሚና የሚጫወት የለውጥ ኃይሎች ስብስብ መኾኑን ማረጋገጥ እንፈልጋለን።
በየጊዜው በሚፈጠሩ ቀውሶች ላይ ተንተርሰን የምናወጣቸው መግለጫዎች የተነጣይነት ወይም የተገንጣይነት ልክፍት ስላለብን ሳይኾን በገፊ ምክንያቶች ስለምንታጠርና ስለምንወጠር ብቻ ነው። የኢትዮጵያንና የሁሉንም ክልሎች ጥቅም የሚጎዳ የፖለቲካ ጨዋታ ውስጥ በፍጹም አንዘፈቅም። የሚዘፈቅም ካለ ከብልሁ ሕዝባችን ጋር ኾነን እናጠራዋለን እንጂ የትህነግንም ኾነ የኦነግ ሸኔን እርካሽ መንገድ አንከተልም። ስለኾነም በማንኛውም ሁኔታ ሕዝብንና አገርን እናስቀድማለን። ከቃላት ድርደራ በላይ ለተግባር እርብርብ ቅድሚያ እንሰጣለን። መንገዳችንም ኾነ ትልማችን ይኸው ነው።
ቅድሚያ ለአገርና ለሕዝብ !!!
የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት



