ኮንዶሚንየም

በአዲስ አበባ የካ አካባቢ በመገንባት ላይ ያለ ኮንዶሚንየም

ቀድሞ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ተመዝጋቢዎች መረጃው ይጣራልን እያሉ ነው

ኢዛ (ሰኞ መጋቢት ፳ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. March 29, 2021)፦ የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማት አስተዳደር ከነገ ጀምሮ የማኅበር ቤት ምዝገባ እንደሚጀምር አስታውቋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ፕሬስ ሴክሬተሪያት በኩል ዛሬ ይፋ በኾነው መረጃ መሠረት ከነገ መጋቢት 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ቀደም ብሎ በ2005 ነባር በ20/80 እና በ40/60 የቤት ልማት ፕሮግራም ተመዝጋቢ የኾኑ በእድሉ ተጠቃሚ ይኾናሉ።

ከመረጃው መገንዘብ የሚቻለው ግን እነዚህ ተመዝጋቢዎች ቁጠባቸውን ያላቋረጡ፣ በማኅበር ተደራጅተው ቤት ለመሥራት ፍላጐቱ ያላቸው መኾን እንደሚገባቸው ያመለክታል።

አያይዞም እነዚህ ተመዝጋቢዎች በማኅበር ከተደራጁ በኋላ እያንዳንዱ አባል የሚጠበቀውን የቤቱን ወጪ 70 በመቶ ክፍያ በቅድሚያ ለመክፈል ፍቃደኛ መኾን ይጠበቅባቸዋልም ተብሏል።

ለአሥራ አምስት ቀን የሚደረገው ምዝገባ በአካል መቅረብ ሳያስፈልግ በኦንላይን መመዝገብ የሚቻል መኾኑንም አስታውቋል።

ይህ የከተማው አስተዳደር ቤቶች ልማትና አስተዳደር ይፋ ያደገው መረጃ ግን ብዥታ የፈጠረ መኾኑ ታውቋል።

በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው ለዓመታት የኮንዶሚኒየም ቤት እናገኛለን ብለው ሲጠብቁ የነበሩ ቆጣቢዎች፤ አሁን አስተዳደሩ እተገብረዋለሁ ያለው አሠራር ግልጽ ካለመኾኑም በላይ፤ ከአቅማቸው ጋር የማይመጣጠን ይኾናል ብለው እንደሚያምኑ አስረድተዋል።

ከ2005 ጀምሮ እየቆጠቡ ዛሬ ላይ ደርሰው፤ አሁን እንደ አዲስ በማኅበር ተደራጅታችሁ ገንቡ መባሉንም ተገቢ ያለመኾኑን ያመለከቱት እነዚህ ተመዝጋቢዎች፤ እንደገና እንዲመዘገቡ መፈለጉ አግባብ ያለመኾኑን ያምናሉ።

ይህ ብቻ ሳይኾን በአስተዳደሩ የዛሬ መረጃ መሠረት በማኅበር ቤት ለመገንባት የሚቻሉ ተመዝጋቢዎች ከጠቅላላ የቤቱ ወጪ 70 በመቶ ቅድሚያ መክፈል አለባቸው ማለቱ የበለጠ የሚያሳስባቸው ነው። እስካሁን ሲቆጥቡ የነበሩት ቀድሞ በነበረው ዋጋ ከ10 እና ከ20 በመቶ የማይበልጠውን ሲሆን፤ አሁን እንዴት 70 በመቶ በቅድሚያ ይጠየቃል የሚለው ጉዳይም ፈጽሞ ሊተገበር የማይችል ኾኖባቸዋል።

እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ አመለካከት ከኾነ፤ በተለይ በ20/80 የቤት ልማት ፕሮግራም አብዛኛዎቹ ቆጣቢዎች ሳያቋርጡ ቆጥበዋል ተብሎ ስለማይታመን፤ በማኅበር ቤቶቹ ደግሞ ለመመዝገብ እድል የማይኖራቸው በመኾኑ፤ አስተዳደሩ እተገብረዋለሁ ያለውን አሠራር እንዴት አጥንቶት እንደኾነ ለማወቅ መቸገራቸውን ነው።

በመሥፈርቱ መሠረት አንዱ ቁጠባው ያላቋረጠ የሚል በመኾኑ፤ ይህንን ለማሟላት የማይችሉት ደግሞ ስንቶች ናቸው የሚለው መታየት ስላለበት፤ እስካሁን በ20/80ም ኾነ በ40/60 የቤት ልማት ፕሮጀክት የተመዘገቡ ነዋሪዎች በቀደሙ ምዝገባቸው መሠረት እየተሠሩ ያሉ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን እንዲያገኙ መደረግ አለበት የሚል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በአስተዳደሩ የዛሬ መረጃ መሠረት ፍቃደኛ የነበሩ ተመዝጋቢዎች በማኅበር በመደራጀት በማኅበር ቤት ምዝገባ ማካሔድ የሚችሉ ቢኾንም፤ አቅም የሌላቸውስ እንዴት ይስተናገዳሉ የሚለውን በዝርዝር ያለማስቀመጡንም እኒሁ አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ግን ነባሩና በመደበኛው የ20/80 እና የ40/60 የቤቶች ልማት ፕሮግራም ግንባታ ሥራ በተለመደው አሠራር እንደሚቀጥል ቢሮው በዛሬው መረጃ ላይ የጠቀሰ ቢኾንም፤ እነዚህ ቤቶች ሲያልቁ የቀድሞ ተመዝጋቢዎች የሚረከቡዋቸው ናቸው ወይስ አይደሉም? የሚለው ጥያቄ ግን መልስ የሚሰጥ አይደለም። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ