በአገሪቱ ከሚገኙት ነዳጅ ማደያዎች አንዱ

በአገሪቱ ከሚገኙት ነዳጅ ማደያዎች አንዱ

የእጥረቱ መንሥኤ በሶማሌና በአፋር ክልሎች አዋሳኝ በተፈጠረ ግጭት ነዳጅ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች እንደልብ መንቀሳቀስ አለመቻላቸው እና ከሱዳን የሚገባው ነዳጅ በአግባቡ እየገባ ባለመኾኑ ነው የሚሉ አሉ

ኢዛ (እሁድ ሚያዝያ ፫ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. April 11, 2021)፦ ባለፉት ሁለት ቀናት በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች የተፈጠረው የነዳጅ እጥረት ተገልጋዮችን ሲያጉላላ በተለይ አዲስ አበባ ከተማ በትራፊክ መጨናነቅ ምክንያት ኾኖ ታይቷል። ዛሬን ጨምሮ ባለፉት ሦስት ቀናት በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ አብዛኞቹ ነዳጅ ማደያዎች ነዳጅ የለንም በሚል አገልግሎት እየሰጡ አልነበረም።

ነዳጅ ያላቸው ማደያዎችም ያላቸውን ነዳጅ ለመቅዳት የሚሰለፉ ተሽከርካሪዎች ነዳጅ ማደያዎቹ አካባቢ ያሉ አውራ ጐዳናዎችን በማጨናነቅ የትራፊክ ፍሰቱን አስተጓጉለዋል። ነዳጅ እጥረት አለ ተብሎ ከተወራ ወዲህ የተሽከርካሪ ባለቤቶች ወደማደያዎች በመሔድ ረዣዥም ሰልፎችን በመጠበቅ ነዳጅ መቅዳት ግድ ብሏቸዋል።

የሰሞኑ የነዳጅ እጥረት መንሥኤ ግልጽ ባይኾንም ነዳጅ ለመቅዳት ሰዓታት መጠበቅ ግድ መኾኑ ብቻ ሳይኾን የትራንስፖርት አገልግሎት ላይ እንቅፋት እስከመፍጠር ደርሷል።

በአብዛኛው እጥረቱ የታየው ቤንዚን ላይ እንደኾነም ለመረዳት ተችሏል። ለእጥረቱ መባባስ ሌላው ምክንያት የኾነው ደግሞ ነዳጅ እጥረት መኖሩ እንደታወቀ አብዛኛዎቹ ባለአሽከርካሪዎች በሌላ ወቅት ከሚቀዱት በላይ ነዳጅ እየቀዱ በመኾኑ እንደኾነም ለመታዘብ ተችሏል።

በኢትዮጵያ ወቅት እየጠበቀ እንዲህ ያለ የነዳጅ እጥረት በተለያዩ ምክንያቶች ሲፈጠሩ የታዩ ሲሆን፣ ይህም ረዣዥም ሰልፎችን ታግሰው መቅዳት ያልቻሉ በጥቁር ገበያ ገዝተው ሲጠቀሙ እንደነበር ይታወሳል።

አሁንም በነዳጅ ማዲያዎች ያልተገኘ ነዳጅ በጥቁር ገበያ በመገኘቱ ሰሞኑንም አንድ ሊትር ቤንዚን እስከ 40 ብር በመግዛት የተጠቀሙ የታክሲ ሹፌሮች እነርሱም በአገልግሎታቸው ላይ ጨምረው ደንበኞቻቸውን እንዳስተናገዱ የገለጹልን አሉ።

እንዲህ ዐይነት የነዳጅ እጥረቶች የበለጠ ሮሮ የሚያብሱት ረዣዥም ሰልፍ ይዘው እና ሰዓታት ጠብቀው ነዳጅ አለቀ የሚባልበት ወቅት ነው።

የሰሞኑ እጥረት በተመለከተ በይፋ መንሥኤው ባይገለጽም አንዳንድ ወገኖች በቅርቡ በሶማሌና በአፋር ክልሎች አዋሳኝ ላይ በተፈጠረ ግጭት ነዳጅ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች እንደልብ ባለመንቀሳቀሳቸው ነው የሚል ግምት ያላቸው ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ በአሁኑ ከሱዳን የሚገባው ነዳጅ ወደ አገር ቤት በአግባቡ እየገባ ካለመኾን ጋር ያያይዙታል።

ለእጥረቱ የተለያየ መላምት የሚሰጥ ቢኾንም፤ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት አሁን የተፈጠረው እጥረት በሁለት ቀናት ውስጥ ይቀረፋል ማለቱ ተገልጿል።

ኢትዮጵያ ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ከውጭ ከምታስገባቸው ምርቶች መካከል ነዳጅ አንዱ ሲሆን፤ በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ ሰጥተው የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት በአንድ ወር ብቻ ለነዳጅ ብቻ 3 ቢሊዮን ብር ድጐማ ማድረጉን ነው።

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በበኩሉ ይፋ ባደረገው መረጃው፤ ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ ለነዳጅ አቅርቦት ከ344 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን ነው።

ከነዳጅ አቅርቦትና ወጪው እየናረ ከመምጣት ጋር ተያይዞ ሌላው ችግር የኾነው ቤንዚን ከኢታኖል ቀላቅሎ የመሥራቱ ሥራ የታሰበውን ያህል አለመኾኑ ነው። ለዚህም ዋናው ምክንያት ኢታኖሉን ያመርታሉ የተባሉ ትላልቅ የስኳር ፋብሪካዎች እውን መኾን ካለመቻላቸው ጋር ይያያዛል።

ከኢትዮጵያ ነዳጅ ድርጅት የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው እ.ኤ.አ. ከ2017 እስከ መጋቢት 2021 ድረስ 344.2 ቢሊዮን ብር ለነዳጅ ግዥ ወጥቷል። የነዳጅ ፍላጐትና ወጪ መጨመር አስረጅ የሚኾነው ደግሞ እ.ኤ.አ. በ2017 ለነዳጅ የወጣው ወጪ 43 ቢሊዮን ብር ሲሆን፤ በ2020 ላይ ግን 86 ቢሊዮን ብር ደርሷል።

በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚገዛው ነዳጅ በአግባቡ የሚገባ እንኳን ቢኾን፣ ሕገወጥ ተግባራት የሚፈጸሙበት እንደኾነ ሲነገር ቆይቷል። አንዳንዴ ወደተለያዩ ማደያዎች የተላኩ ነዳጅ ጫኝ ተሽከርካሪዎች ምርቱን የተባለው ቦታ ሳያደርሱ በአየር ላይ ሲሸጡ መያዛቸው ይታወሳል።

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነዳጅን በተመለከተ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ ለነዳጅ መንግሥት ከፍተኛ ድጐማ እያደረገ ቢኾንም፤ ተገዝቶ ወደ አገር የሚገባው የነዳጅ ምርት ለስርቆትና ብዝበዛ የተዳረገ መኾኑን መግለጻቸው ያለውን ችግር ያሳያል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ