ዶሮ 80 ብር፣ ፍየል እስከ 2250 ብር፣ እንቁላል 2 ብር ተሽጧል

Ethiopia Zare (እሁድ መጋቢት 26 ቀን 2002 ዓ.ም. April 4, 2010)፦ በዓለ ትንሣዔ በመላው ኢትዮጵያ የሚከበር እንደመሆኑ እንደባለፉት በዓላት ሁሉ ዘንድሮም የገበያ ዋጋ ንረት የታየበት እንደነበር ተገለጸ።

 

በኑሮው መወደድ ግራ የተጋባው አብዛኛው ህዝብና በሸቀጦች ዋጋ መናር ብዙ አትራፊ መሆን የቻለው ኅብረተሰብ በአንድ ላይ ሮሮ በሚያሰሙበት የገበያ ንረት ዕለት ዕለት ከመባባሱም በላይ በዋዜማው የጋዝ ዕጥረት ያጋጠመ ቢሆንም፤ መጋቢት 24 ቀን 2002 ዓ.ም. ወጥ ማብሰያ የሚሆነውን ጋዝ የሚያቀርቡት ነዳጅ ማደያዎች እጥረቱን አስወግደው ጋዙን ለሸማቹ ኅብረተሰብ አቅርበዋል ተብሏል።

 

በየጊዜው የሚያስፈልጉና ለበዓላት የሚቀርቡ አትክልት፣ ፍራፍሬና የተለያዩ ዕቃዎች ዋጋ እጅግ ከማሻቀቡም በላይ ቀይ ሽንኩርት በኪሎ ከ6 - 8 ብር፣ ”ደህና ነው” የሚባል አውራ ዶሮ በ72 ብር ሲያወጣ፤ መርካቶ ውስጥ 90 የኢትዮጵያ ብር፣ በአዲስ አበባ አንድ እንቁላል ከ1 ብር ከ20 ሣንቲም እስከ 1 ብር ከ50 ሣንቲም ሲሸጥ፤ በመሀል ሜዳ 3 እንቁላሎች 2 የኢትዮጵያ ብር ተሽጠዋል። የበግና የፍየል ዋጋ በመጋቢት 23 ቀን 2002 ዓ.ም. “እሳት” ነበረ። “ጥሩ ነዶ አለው …” የሚባለው በግ ከ900 እስከ 1200 ብር፣ ፍየል ከ1150 እስከ 1350 ብር ተጠርቷል። በዘንድሮ የፋሲካ ገበያ አንድ “እኔ ነኝ ያለ …” ፍየል “ቁርጥ መሸጫ ዋጋው 2250 ብር ነው …” ተብሏል።

 

በመጋቢት 24 ቀን 2002 ዓ.ም. ከፍ ሲል ከተገለጸው የበግና የፍየል ዋጋ ዝቅ ያለ ጥሪ የተጠየቀባቸው ቅቤ በኪሎ ከ70 - 80 ብር ለጋው የተሸጠ ቢሆንም፤ የጥራቱ ጉዳይ የብዙ ሸማቾችን ቅቤ የመመገብ ስሜት ጐድቷል። “ሚሊየነር ሆነዋል …” የተባሉት ገበሬዎችና ነጋዴዎች፤ ቅቤን ከማይገቡ ነገሮች … ጋር ቀላቅለው ለገበያ ማቅረቡን ካለፉት 5 ዓመታት ወዲህ ከጀመሩ በኋላ በኅብረተሰቡ ጤንነት ላይ ችግር ሲከሰት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።

 

በአዲስ አበባ ከተማ በመንግሥት አትክልትና ፍራፍሬ መሸጫ መደብሮች የሚታየው ሰልፍ፤ የዛሬ 25 ዓመት ዳቦ ለመሸመት የሚያዘውን ወረፋ መስሏል። በየመደብሮቹ ስኳር የሚሸጠው 13 ብር ከ50 ሣንቲም ሲሆን፤ ህዝቡ ከ18 ዓመታት በፊት 5 ብር ከ25 ሣንቲም ይገዛው የነበረውን 5 ኪሎ ስኳር ዛሬ በ67 ብር ከ50 ሣንቲም ለመሸመት ሰልፍ የያዘበት ምክንያት ለብዙዎች ዕንቆቅልሽ ሆኗል። ኢህአዲግ የስኳር ዋጋን ለማረጋጋት በየቀበሌው አቅርቦት መጀመሩን ቢያስታውቅም በአዲስ አበባ ስኳር በጅምላ ሂሳብ ኩንታሉ አንድ ሺ 700 ብር፣ በችርቻሮ ኪሎ 18 ብር ሂሣብ እየተሸጠ ነው።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ