ኮንዶሚኒየም

የጋራ መኖሪያ ቤቶች

8,500 ተመዝጋቢዎች ከ7 ቢሊዮን ብር በላይ ቅድመ ክፍያ ይጠበቅባቸዋል

ኢዛ (ረቡዕ ሚያዝያ ፮ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. April 14, 2021)፦ ብዥታ ፈጥሮ የነበረው የማኅበር ቤት ምዝገባ በተካሔደበት ባለፉት 15 ቀናት ውስጥ ከ8,500 በላይ ቤት ፈላጊዎች መመዝገባቸውን የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት አስተዳደር ቢሮ ዛሬ አስታውቋል።

በዛሬው የቢሮ መረጃ የተሰጠው የምዝገባ ጊዜ ትናንት ሚያዝያ 5 ቀን 2013 ዓ.ም. የተጠናቀቀ ቢኾንም፤ መመዝገብ የሚፈልጉና በሲስተም መጨናነቅ ያልተመዘገቡና በቂ መረጃ ላልነበራቸው እድል ለመስጠት ሲባል የምዝገባው ጊዜ ለተጨማሪ 10 ቀናት ተራዝሟል።

በዚህ የማኅበር ቤት አገነባብ ዙሪያ ምዝገባው ከተጀመረ በኋላ የተሠራጨው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በማኅበር የሚገነቡት መኖሪያ ቤቶች ባለ ዘጠኝና 13 ወለል ያላቸው ሕንጻዎች ናቸው።

በእነዚህ ሕንጻዎች የሚገነቡት መኖሪያዎች የቦታ ስፋት ከ60፣ 75 እና 105 ካሬ ሜትር ስፋት ያላቸው ሲሆን፤ ዋጋቸውም በአንድ ካሬ ሜትር 12,061.90 እና 13,086.82 ብር ነው።

በዚሁ ስሌት መሠረት 60 ካሬ ሜትር መጠን ያለው ቤት ጠቅላላ ዋጋ 882,086.75 ብር ሲሆን፤ ከፍተኛው ደግሞ 105 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ቤት 1,620,540.92 ብር መኾኑን ያመለክታል። ይኽ ዋጋ ወቅታዊ የገበያ ዋጋን መሠረት ያደረገ ሲሆን፤ ዋጋው እንደሚጨምር ታሳቢ ተደርጐ በተዘጋጀው በዚህ ስሌት መሠረት የአንዱ ቤት አማካይ ዋጋ 1.1 ሚሊዮን ብር እንደሚኾን መገመት ይቻላል።

ዛሬ ቢሮው ካወጣው መረጃ አንጻር ሲታይ 8,500 ተመዝጋቢዎች በአማካይ በተሰላው ዋጋ መሠረት ከ9.4 ቢሊዮን ብር በላይ ያስፈልጋቸዋል ማለት ነው።

በቀጣዩ 10 ቀናት በአነስተኛ ግምት 2,500 ሰዎች ቢታከሉ 11 ሺሕ የማኅበር ቤት ፈላጊዎች ለቤቱ የሚጠበቅባቸው አጠቃላይ ዋጋ ከ12.1 ቢሊዮን ብር ሊኾን ይችላል ማለት ነው።

ቢሮው ቀደም ብሎ ባስቀመጠው መስፈርት መሠረት ለማኅበር ቤቱ ተመዝጋቢዎች 70 በመቶውን በቅድሚያ መክፈል የሚጠበቅባቸው በመኾኑ፤ በአማካይ ግምታዊ የቤቶች ዋጋ መሠረት እነዚህ 11 ሺሕ ተመዝጋቢዎች የሚጠበቅባቸው ከ8.5 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚኾን ያመለክታል። ስለዚህ ይህ የማኅበር ቤት ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ እንደኾነ ያሳያል።

ይኽ ግምታዊ አማካይ ዋጋ ከጊዜው ጋር እየታየ የሚጨመር በመኾኑ ለ11 ሺዎቹ ተመዝጋቢዎች በአነስተኛ ግምት ቤቶችን ለመግዛት ከ12.1 ቢሊዮን ብር በላይ ይጠይቃል።

ለምሳሌ 5 በመቶ ብቻ እንኳ የዋጋ ንረት ቢኖር ከ12.7 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያስፈልግ ሲሆን፤ የዋጋ ንረቱ 10 በምቶ ቢኾን ደግሞ ከ13.3 ቢሊዮን ብር በላይ ይጠይቃል ማለት ነው። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ