የቦርዱ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ ለፓለቲካ ፓርቲዎች ማብራሪያ ሲሰጡ

የቦርዱ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ ለፓለቲካ ፓርቲዎች ማብራሪያ ሲሰጡ

ከአራት ሺሕ በላይ ምርጫ ጣቢያዎች የመራጮች ምዝገባ እያካሔዱ አይደለም

በአዲስ አበባ መምረጥ ከሚችለው 14 በመቶው ብቻ ነው የተመዘገበው

ኢዛ (ረቡዕ ሚያዝያ ፮ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. April 14, 2021)፦ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ለማካሔድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለመራጮች ምዝገባ የሰጠው ጊዜ ሊጠናቀቅ 8 ቀናት የቀሩት ሲሆን፤ ዛሬ ቦርዱ ይፋ ባደረገው መረጃ እስካሁን በነበሩት የቅድመ ምርጫ ተግባራት የጸጥታ ችግር ፈታኝ ሆኖብኛል ብሏል።

ቦርዱ እስካሁን ያካሔዳቸውን ተግራት ለፓርቲዎች ማብራሪያ በሰጠበት መድረክ ላይ፤ በተለይ ከተፈናቃዮች እና ጸጥታ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በጸጥታ ችግር የተነሳ በ4 ሺሕ የመራጮች ምዝገባ እየተካሔደባቸው አለመኾኑን አመልክቷል።

በጸጥታ ሥጋት የመራጮች ምዝገባ ቁሳቁሶቹ የዘገየባቸው ክልሎች ናቸው ተብለው የተጠቀሱት ኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ፣ ምሥራቅ ወለጋ፣ ሆሮጉድሩ እና ቄለም ወለጋ (ክልሉ ስለቀበሌዎቹ ጸጥታ የሰጠው መረጃ ዘግይቶ የደረሰ መኾኑ መረጃዎቹም ከደረሱ በኋላ መጣራት ስለነበረባቸው የዘገየ)፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን እና ከማሺ ዞን (በከፊል)፣ አማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር እና ሰሜን ሸዋ (ጨፋ ሮቢት፣ ሸዋ ሮቢት ማጀቴ፣ አጣየ፣ አርጎባ ልዩ ወረዳ)፣ ዋግኸምራ ብሔረሰብ አስተዳደር (ከትግራይ ክልል ጋር የሚዋሰኑ 27 የምርጫ ጣቢያዎች)፣ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ጉራፈርዳ በአራት ቀበሌዎች፣ ሱርማ፣ ዘልማም (ግጭቶችን ተከትሎ የምርጫ ተግባር መቀጠል መቻሉን የሚገልጽ መረጃ አለመኖር) ይጠቀሳሉ ተብሏል።

እስካሁን ያለው የመራጮች ምዝገባ ውጤታማ ባለመኾኑ በቀጣይ ሊወሰድ ያቀዳቸውን እርምጃዎችም አሳውቋል ተብሏል።

ስምንት ቀናት በቀሩት የዚህ የመራጮች ምዝገባ በአዲስ አበባ እስካሁን የተመዘገቡት የመራጮች ቁጥር 209 ሺሕ ብቻ እንደኾነ ታውቋል። ይኽም በሚቀጥሉት ቀናት ከፍተኛ መጨናነቅ እንደሚፈጠር ከወዲሁ መገመት አያዳግትም።

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር በመንግሥት ደረጃ 3 ሚሊዮን እየተባለ የሚነገር ሲሆን፤ አሁን ካለው የሕዝብ አሰፋፈር አንጻር የከተማዋ ነዋሪዎች ከ6 ሚሊዮን በላይ እንደኾነ ይገመታል። ግማሽ ያሕሉ እንኳን መምረጥ ቢችል ተብሎ ቢታሰብ፤ በመንግሥቱ አኀዝ 1.5 ሚሊዮን ዝቅተኛው የመራጮች ቁጥር ይኾናል። ከግምታዊው እና ከ6 ሚሊዮን በላይ ተብሎ በሚታሰበው ግማሹ መምረጥ ቢችል፤ ቢያንስ 3 ሚሊዮን መራጮች እንደሚኖሩ መገመት ይቻላል።

ከሁለቱም አኀዝ አንጻር ከ1.5 ሚሊዮን እስከ 3 ሚሊዮን የሚደርስ የመራጮች ቁጥር በአዲስ አበባ ሊኖር የሚችል ቢኾንም፤ ስምንት ቀን በቀረው የምዝገባ ጊዜ ውስጥ አንድ ሚሊዮን ሕዝብ አለመመዝገቡ ጉዳዩን አሳሳቢ አድርጎታል። በትንሹ መምረጥ የሚችሉት ነዋሪች ቁጥር 1.5 ሚሊዮን ቢኾን እንኳን አሁን የተመዘገቡት 209 ሺሕ ሰዎች ቁጥር 14 በመቶ አይሞላም።

የምርጫ ምዝገባው ላለፉት 20 ቀናት ሲከናወን ቆይቶ የተመዝጋቢዎች ቁጥር 209 ሺሕ ከኾነ፤ በሚቀጥሉት ስምንት ቀናት መምረጥ የሚችሉ የከተማዋ ነዋሪዎች ካልተመዘገቡ፤ ወይንም ሳይመዘገቡ የመመዝገቢያ ጊዜው ካለቀ፤ በዋናነት የከተማይቱን እንዲሁም የአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሊፈጠር ይችላል ተብሎ ይገመታል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!