ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ተጨማሪ የሲሚንቶ ፋብሪካ ሊገነባ ነው
በድሬ ዳዋ ከተማ የናሽናል ሲሚንቶ ኢንዱስትሪያል ኮምፕሌክስ የመሠረት ድንጋይ የማስቀመጥ ሥነ-ሥርዓት፣ ሚያዝያ 10 ቀን 2013 ዓ.ም.
የአካባቢ አገሮችን ገበያም ታሳቢ አድርጓል
ኢዛ (ሰኞ ሚያዝያ ፲፩ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. April 19, 2021)፦ ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ በድሬ ዳዋ ከተማ ከ350 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የሚጠይቀውን አዲስ የሲሚንቶ እና የአርማታ ብረት ፋብሪካ ግንባታ ለመጀመር የመሠረት ድንጋይ አስቀምጧል።
በትናንትናው ዕለት የመሠረት ድንጋዩ በድሬ ዳዋ ከተማ የተቀመጠለትን ይህንን “ናሽናል ሲሚንቶ” ኢንዱስትሪያል ኮምፕሌክስ ፋብሪካ የሚገነባው ከአንድ ወር ከ15 ቀን በፊት (የዛሬ ስድስት ሳምንት ግድም) በሰሜን ሸዋ ዞን በእንሳሮ ወረዳ በሁለት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር (ከዘጠና ቢሊዮን ብር በላይ) ተመሳሳይ ፋብሪካ ለመገንባት ከተሻረከው ዌስት ኢንተርናሽናል ሆልዲንግ ከተባለው የቻይና ኩባንያ ጋር ነው።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አደም ፋራህ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶ/ር ይናገር ደሴ፣ የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሙስጠፌ መሐመድ እና ከፍተኛ የፌዴራል እና የክልል ባለሥልጣኖች በተገኙበት የትናንቱ የመሠረተ ድንጋይ ማስቀመጥ ፕሮግራም ላይ እንደተገለጸው፤ የአዲሱ ፋብሪካ ዋነኛ ግብ እንደ ጅቡቲ፣ ሱማሌላንድ እና ሶማሊያ ያሉ አገሮችን ጭምር ታሳቢ ያደረገ ነው። ወደ እነዚህ አገሮች ሲሚንቶ በመላክ ጭምር ተጠቃሚ ያደርጋል ነው የተባለው።

በኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ እና በቻይናው ዌስት ኢንተርናሽናል ሆልዲንግ ሽርክና የሚገነባው የኢንዱስትሪ ኮምፕሌክሱ በቀን አምስት ሺህ ቶን ሲሚንቶ እና በዓመት ሦስት መቶ ሺህ ቶን ብረት ማምረት የሚችሉ ፋብካዎችን የሚይዝ ነው። ግንባታው በ103 ሔክታር መሬት ላይ የሚካሔድ ሲሆን፤ ከ350 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ እንደሚደረግ ይጠበቃል። ግንባታው ተጠናቆ ሥራ በሚጀምርበት ወቅትም ከአሥር ሺህ በላይ ለሚኾኑ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ይጠበቃል።
የለሚ ናሽናል ሲሚንቶ አክሲዮን ማኅበር በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ለሚ ከተማ ለሚያስገነባው የኢንዱስትሪ ኮምፕሌክስ ባለፈው የካቲት 25 ቀን 2013 ዓ.ም. ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በተገኙበት ሥራውን የማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት መካሔዱን መዘገባችን የሚታወስ ነው።
በድሬዳዋ እና በለሚ የሚካሔዱት ፕሮጀክቶች እርስ በርሳቸው የሚመጋገቡና አንዱ ለሌላው መኖር ወሳኝ መኾናቸውን የሚናገሩት የኢስት አፍሪካን ሆልዲንግስ የቦርድ ሊቀመንበር ዶክተር ብዙአየሁ ታደለ፤ የለሚው ለአገር ውስጥ አቅርቦት፣ የድሬ ዳዋው ደግሞ ኤክስፖርት በማድረግ የውጭ ምንዛሪን ማግኘትን ታሳቢ ያደረጉ፣ የስትራቴጂክ አንድነት ያላቸው መኾናቸውን ገልጸዋል። ፕሮጀክቶቹ በታቀደላቸው ጊዜ ተጠናቀው ወደ ምርት እንዲገቡ የሚቻለንን ሁሉ እናደርጋለን ያሉት ዶክተር ብዙአየሁ፤ የመንግሥትም ድጋፍ እንደማይለያቸው ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።
በዕለቱ የመሠረት ድንጋይ ማስቀመጥ ሥርዓት ላይ የተገኙት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል፤ ይህ ፋብሪካ ለአገር ውስጥ ከሚያቀርበው ምርቱ ባሻገር የጐረቤት አገሮችን ገበያ ጭምር ታሳቢ ያደረገ እንደሚኾን ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፤ አሁን ያለውን የአገሪቱን የሲሚንቶ እጥረት በማቃለልም ረገድ የራሱ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።
ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ሊቀመንበር አቶ ብዙአየሁ ታደለም እንደተናገሩት አዲሱ ፋብሪካ ለሱማሌ፣ ለሱማሌላንድ እና የጅቡቲን ገበያ ከማሰብ ጭምር የሚገነባ ሲሆን፤ ካለው የገበያ ፍላጐት አንጻር በእነዚህ አገሮችም የሲሚንቶ መፍጫና ማሸጊያ የማቋቋም እቅድ አለን ብለዋል። (ኢዛ)



