በአማራ ክልል የተቃውሞ ሰልፎች ቀጥለዋል
”በተለያዩ አካባቢዎች በአማሮች ላይ የሚፈጸም ግድያ ይቁም”፣ "አማራን ማሳደድ ይቁም”፣ "ሕጻናትን መግደል እና ከተማ ማፍረስ ጀግንነት አይደለም”፣ ”በአማራ ላይ እየተፈጸመ ያለው ጥቃትና መፈናቀል መንግሥትን ሊያሳስበው ይገባል”
"አማራን ማሳደድ ይቁም! ሕጻናትን መግደል እና ከተማ ማፍረስ ጀግንነት አይደለም!”
ኢዛ (ማክሰኞ ሚያዝያ ፲፪ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. April 20, 2021)፦ በአማራ ላይ ያነጣጠሩ ዘር ተኮር ጥቃቶች እንዲቆሙ እና መንግሥት እነዚህን ጥቃቶች እንዲያስቆም አጥብቀው የጠየቁ ሰላማዊ ሰልፎች በባሕር ዳር፣ በደብረ ማርቆስ፣ በወልዲያ እና በተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች ተካሔዱ።
ሰልፎቹ የተካሔዱት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በቅርቡም በአጣየ፣ በሸዋ ሮቢት እና አካባቢው ከተሞች ዘር ተኮር የኾኑ ግድያዎችን እና ጥቃቶችን ለማውገዝ ነው።
በተለያዩ አካባቢዎች በአማራ ላይ የሚፈጸምን ጥቃት በማውገዝ የተቃውሞ ድምፃቸውን ያሰሙት ሰልፈኞች፤ የተለያዩ መፈክሮችን የያዙ ሲሆን፣ “በአማራ ላይ የሚፈጸም ግድያ ይቁም!” የሚለው በዋናነት ይጠቀሳል።
በዚሁ በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች በተካሔው የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ከተደመጡት መፈክሮች ውስጥ፤ ”በተለያዩ አካባቢዎች በአማሮች ላይ የሚፈጸም ግድያ ይቁም”፣ "አማራን ማሳደድ ይቁም”፣ "ሕጻናትን መግደል እና ከተማ ማፍረስ ጀግንነት አይደለም”፣ ”በአማራ ላይ እየተፈጸመ ያለው ጥቃትና መፈናቀል መንግሥትን ሊያሳስበው ይገባል” የሚሉ ይገኙበታል።
በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች አደባባይ በወጡበት በእነዚህ ትእይንት ሕዝቦች ላይ አማራን ማሳደድ ይቁም! እና ተያያዥነት ያላቸው ሌሎች መፈክሮችም ተሰምተዋል። (ኢዛ)



