የአማራ ክልል ከሰልፍ ያለፈ መፍትሔ ያስፈልጋል አለ
የአማራ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ መግለጫውን በሰጡበት ወቅት፣ ሚያዝያ 13 ቀን 2013 ዓ.ም.
በአራቱም አቅጣጫ ጥቃት ለመፈጸም ፍላጐት መኖሩንም አስታወቀ
የአንድነት ጥሪ አስተላልፏል
ኢዛ (ረቡዕ ሚያዝያ ፲፫ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. April 21, 2021)፦ ጠላቶቻችን በአማራ ላይ በአራቱም አቅጣጫ ለመፈጸም ፍላጐት ያላቸው በመኾኑ፤ ከሰልፍ የዘለለ መፍትሔ እንደሚያስፈልግ የአማራ ክልል አስታወቀ።
በክልሉ ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት በኩል ዛሬ ረቡዕ ሚያዝያ 13 ቀን 2013 ዓ.ም. የተሰጠው መግለጫ፤ ክልሉ በአራቱም አቅጣጫ በጠላት ጥቃት ሊፈጸምበት እንደሚችል ጠቁሞ፤ አሁን ያለውን ችግር በሰልፍ ብቻ መፍታት አይቻልም የሚለው አመለካከት አንጸባርቋል።
የክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ ወቅታዊውን ችግር ለመወጣት አንድነትና በጋራ መነሳትን የሚጠይቅ መኾኑን ነው።
“አሁን ከገጠመን ችግር አኳያ ሰልፍ ሁነኛ የችግር መፍቻ መንገድ አይደለም። ችግር በዋናነት በሰልፍ አይፈታም ብለን ስናስብ፤ ከጠላቶቻችን ባህሪ በመነሳት ነው” ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ጠላቶቻችን በአራቱም አቅጣጫ ነው ጥቃት ለመፈጸም የሚፈልጉት ብለዋል። ለረዥም ዘመናት ታስቦበት የተጠነሰሰው ሴራ፤ አሁን ላይ ደርሶ ባለፉት ዓመታት እየፈነዳ መጥቶ፤ አሁን የበለጠ ተጠናክሮ የመጣበት መኾኑን መገንዘብ እንደሚያስፈልግም አስረድተው፤ ማሕበረሰቡ ያለውን ሁኔታ በአግባቡ ሊያጤን እንደሚገባም ነው የተናገሩት።
አሁን በቅርቡ በሰሜን ሸዋ አጣየ አካባቢ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰና አካባቢው ይህንን ያህል ጉዳት ከደረሰ በኋላ ተረጋጋ ማለት ግን አሁን አካባቢው ነፃ ነው ማለት ያለመኾኑን ተናግረዋል።
መቼም ቢኾን ጠላቶቻችን ተጠርገው እስካላለቁ ድረስ አማራ ክልል ሰላም እንዲኾን አይፈልጉም። ይኼ በተጨባጭ የምንናገረው ነው። ማሕበረሰባችን ይህንን እንዲረዳ እንፈልጋለን ያሉት አቶ ግዛቸው፤ ለምሳሌ አዊ ዞን ላይ ከቤንሻንጉል ታጥቆ የሚንቀሳቀሰው አማፂ ኃይል አዲስ ዓለም የሚባለው ቀበሌ ድረስ ጥቃት ለመሰንዘር ሙከራዎች አድርጓል። የዚያ አካባቢ ነዋሪ ቀደም ብሎ መረጃ ደርሶት ስለነበርና የጸጥታ ኃይላችንም መትቶ የመለሰው ቢኾም ምልክቱ ጥሩ አለመኾኑንም ተናግረዋል። በዚህም ምክንያት በአራቱም ማዕዘናት ጥቃት ሊፈጸም ይችላል ተብሎ የክልል ልዩ ኃይል በሁሉም አቅጣጫ እንዲመደብ ተደርጓል።
“ያልጨረስነው የጠላት ብዙ የቤት ሥራ አለን” ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በሰሜን አካባቢ በራያና በወልቃይት አካባቢ ያልተጨረሰ ሥራ እንዳለም ጠቁመዋል።
አሁንም የጠላት ኃይል አሰፍስፎ የሚጠብቅበት ቀጠና እንደኾነ አመልክተው፤ በሱዳን በኩልም ጠላት እንዳለ አመልክተዋል። በዚህ አካባቢም ልዩ ኃይሉ ተወጥሮ ያለና ይህንንም በራሳችን ኃይል እየጠበቅንና እየተከታተልን ያለነው በማለት ስላለው ሁኔታ አስረድተዋል።
በተመሳሳይም በቅማንት አካባቢ ያገረሸ ችግር እንዳለም ከአቶ ግዛቸው ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል። በቅማንት አካባቢ ያለው ችግር በጽንፈኛ ኃይል የሚመራ ነው ተብሏል። በአጐራባች አካባቢም እንዲህ ያሉ ፍላጐቶች ያሉና በቀላሉ የሚቆሙ ያለመኾናቸውን ነው። ስለዚህ ማሕበረሰቡ ይህንን አውቆ ከሰልፍ በዘለለ ሌላ መፍትሔ መፈለግ እንዳለበትና በጋራ መሠራት ያለበት ነገር እንዳለ የአቶ ግዛቸው ማብራሪያ አመልክቷል።
በአንድነት እና በጋራ መሠራት ያለበት
ከወጣቶች ተደራጅተን እናግዝ የሚል ጥያቄ እየቀረበ በመኾኑ ይህ በመልካም የሚወሰድ መኾኑንም በዚሁ መግለጫቸው ያመለከቱት ዳይሬክተሩ፤ መደራጀት ግን ፎርማል መኾን አለበት። መደራጀት እና እገዛው ደግሞ በመንግሥት ቀርቦ መንግሥት አደራጅቶ በልዩ ኃይል፣ በሚሊሻ፣ በሀብትና በቁሳቁስ መደገፍን ሁሉ ያጠቃለለ መኾን አለበት።
እንዲህ ዐይነቱ እርዳታና እገዛ የሚያስፈልገው ጠላቶቻችን ብዙ ስለኾኑና የጠላት ፍላጐት ደግሞ ማጥፋት በመኾኑ፤ ከመጥፋት መዳን የሚቻለው የአማራ መንግሥትና ሕዝብ የራሱን አቅም በማጐልበት መኾኑን ተናግረዋል።
ስለዚህ በኢኮኖሚ ራሳችንን በማደርጀትና አንድ መኾን የሚያስፈልግ መኾኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ በአስተሳሰብም ራሳችንን በማደርጀት አንድ መኾን ይገባል ብለዋል። አሁን የአንድነት ጉድለት እንዳለ በመጠቆምም መደማመጥ ተገቢ ነው በማለት ተናግረዋል። አንድ ከኾንን ጠላቶቻችን ሊያጠፉን አይችሉም።
በሰልፍ ሐሳብን መግለጽ ነውር ነው እያሉ ያለመኾኑን በማመልከትም፤ እነዚህ በአራት አቅጣጫ ያሉት ጠላቶች ሰልፉን የሚፈልጉት በሰልፉ መኻል ገብተው ለመበጥበጥ ስለመኾኑም ማሰብ ተገቢ ነው ይላሉ።
እንደ ምሳሌ የጠቀሱትም በአጣየ ተደራጅተው የተፈጸመውን ጥቃት ነው። “ጦርነቱን አማራ ክልል መኻል ላይ ማድረግ አለብን፤ እርስ በርስ መጋጨት አለብን የሚል የጠላት ፍላጐት አለ” ያሉት አቶ ግዛቸው፤ ለዚህ ሰለባ ላለመኾን ጥንቃቄ የሚደረግበት ወቅት መኾኑንም አሳስበዋል። አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች ደግሞ ሰልፉን ፖለቲካ መነገጃ ሊያደርጉት እንደሚችሉም መታወቅ አለበት ብለዋል። (ኢዛ)



