አብን በአማራ ላይ የተቃጡት ጥቃቶች ዳግም እንዳይፈጸሙ ማረጋገጥ ያስፈልጋል አለ
አብን (የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ) እና ብልጽግና ፓርቲ
የአማራ ብልጽግና ፓርቲም መግለጫ አውጥቷል
ኢዛ (ረቡዕ ሚያዝያ ፲፫ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. April 21, 2021)፦ በአማራ ሕዝብ ላይ የተጋረጠው አደጋ ሥርዓትና መዋቅር ሠራሽ በመኾኑ እና የሕዝባችን ትግል የሕልውና ትግል እንደመኾኑ መጠን፤ በሕልውናው ላይ በእቅድና በቅንብር የተከፈቱት ጥቃቶች ዳግም እንዳይፈጸሙ የማረጋገጥ ግቡን እውን ማድረግ አለበት ሲል አብን አስታወቀ።
አብን (የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ) በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ዛሬ በመረጃ ገጹ እንዳሰፈረው፤ አብን ከጅምሩ ጀምሮ በሕዝባችን ላይ የተጋረጡ ሥጋቶችን በትክክል በመገምገም የተጠናከረ ትግል እየካሔደ ስለመኾኑም አስታውቋል።
በተመሳሳይ ማምሻውን የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ያጋጠመንን ፈተና የምንሻገረው እውነተኛ ሕዝባዊነታችንን ጠብቀን በመዝለቅ ነው በሚል ርዕስ ባወጣው መግለጫ፤ ወቅታዊውን ሁኔታ ከፓርቲው አንጻር አቋሙን አንጸባርቋል።
ሁለቱም ፓርቲዎች የሰሞኑ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ የየራሳቸውን አተያይ ያንጸባረቁበትም ነው። የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ እና አብን ዛሬ ያወጧቸው መግለጫዎች የሚከተሉት ናቸው። (ኢዛ)
ሥርዓቱ በጅምላ የተጨፈጨፉ ወገኖቻችንን የሕሊና ጸሎት ፕሮግራም በመገናኛ ብዙኀን እንዳይተላለፍ በማድረግ በአማራ ሕዝብ ላይ የሚከተለውን አደገኛ የጥላቻ ፖሊሲ ፍንትው አድርጎ አሳይቷል! - አብን
የቀጣዩ አገር አቀፍ የምርጫ ሒደት (ምርጫ 2013) አካል በኾነውና ትናንት ሚያዝያ 12 ቀን 2013 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በተዘጋጀው የፖለቲካ ፖርቲዎች የምርጫ ክርክር መርኀ ግብር ላይ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄን (አብን)ን ወክለው አቶ የሱፍ ኢብራሒምና አቶ ጣሂር መሐመድ ተገኝተው እንደነበርና በመጀመሪያ ዙር በተሰጣቸው የጊዜ ድርሻ ላይ፦
1/ በአማራ ሕዝብ ላይ በተከፈተው የተቀናጀ የዘር ማጥፋት ጥቃት ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸውና ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን ለክርክር የተገኙት የፖለቲካ ፖርቲዎች ለንቅናቄያችን የተፈቀደውን የሐሳብ ማቅረቢያ ጊዜ ተጠቅመን በምናደርገው የሕሊና ጸሎት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበን፣ ሁሉም ተቀብለውት ሥነሥርዓቱ ተፈጽሟል።
2/ የፌዴራል ሥርዓቱ የተመሠረተው በሕገመንግሥቱ ሲሆን፤ ይህ ሰነድ የኦነግና የትሕነግ ውል እንጅ የኢትዮጵያ ሕዝብ ውል እንዳልኾነ፣ ብዝኃነትን የማያስተናግዱና በብሔር ማንነት የታጠሩ አሕዳዊ ቀጠናዎችን የኮለኮለ ሥርዓት ነባራዊ እንደኾነ፣ አሁን ያለው ሥርዓት በትርክትና በመዋቅር ረገድ ካለፈው የተለየ ሳይኾን የአፈናና የማጥቂያ ስልቱን ብቻ እንደቀየረ በመግለጽ፤ በዚህ ሁሉ ኺደት በተለይ የአማራ ሕዝብ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየተፈጸመበት መኾኑና አሁን በምንናገርበት ወቅት ጭምር የሕዝባችን ደም በከንቱ እየፈሰሰ ስለሚገኝ፤ ሕዝባችን የተቀናጀ የተቃውሞና ራስን የመከላከል ትግል ውስጥ እንደገባ፣ አብንም የዚሁ አካል እንደመኾኑ መጠን እስከ ክርክሩ ፍፃሜ ድረስ በመቆየት የሕዝቡን ትግል ማሳነስ እንደማይፈልግ በመግለጽ መድረኩን ጥለን መውጣታችንን መግለጻችን ይታወሳል።
በተለምዶ በኾነ ቀን የሚካሔዱ ክርክሮች በዚያው ዕለት ከምሽት ዜና ፕሮግራም ቀጥለው ስለሚተላለፉ በዚህ መሠረት አጠቃላይ የክርክሩ ኺደት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለሕዝብ እንደሚቀርብ ስንጠብቅ ቆይተናል።
ኾኖም ከላይ የገለጽነው ፕሮግራም ትላንት ምሽት ላይ ያልተላለፈ ሲሆን፤ እኛም በጣቢያው የአሠራር ቅደም ተከተል ምክንያት ተለዋጭ የአየር ሰዓት ተሰጥቶት ሊኾን ይችላል በሚል ሐሳብ ፕሮግራሙ የሚተላለፍበትን ቀን ስንጠብቅ ቆይተናል።
በዚሁ መሠረት የክርክር ፕሮግራሙ በዛሬው ዕለት ማታ ላይ እንደሚተላለፍ ኾኖም በአብን ልዑካን የቀረበው አጠቃላይ ሐሳብ በፖለቲካ ውሳኔ ሙሉ በሙሉ መቆረጡን ለማረጋገጥ ችለናል።
ስለኾነም፦
ሀ/ በተለይም በአማራ ሕዝብ ላይ በተከፈተው ዘር ተኮር ጅምላ ፍጅት ጉዳት ለደረሰባቸው እና ሕይወታቸውን ላጡ ወገናቻችን የተደረገው የሕሊና ጸሎት ፕሮግራም መቆረጡ፤ ሥርዓቱ በአማራ ሕዝብ ላይ የሚከተለውን አደገኛ የጥላቻ ፖሊሲ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ መኾኑን፤
ለ/ በምርጫ ክርክር ኺደቶች የሚሳተፉ ፖርቲዎች የሚያቀርቧቸው ሐሳቦች ፍጹም ሳይሸራረፉና ሳይቆረጡ እንደሚተላለፉ የሚያረጋግጠውን በፖለቲካ ፖርቲዎቹ መካከል የተፈረመው ስምምነት በግልጽ የጣሰ መኾኑን፤
3/ በክርክሩ ሒደት የፌዴራል ሥርዓቱንና ሕገመንግሥቱን በተመለከተ በንቅናቄያችን በኩል የቀረቡት ሐሳቦች (የስምምነቱን ቃልና መንፈስ በጠበቀ መልኩ የተገለጹ ሕጋዊ ነጥቦች) ጭምር መቆረጣቸው፤ የፖለቲካ ሳንሱር በመርኅነት የቀጠለና የአፈና ሥርዓት ተግባራዊ መደረጉን ለመገንዘብ ችለናል።
አብን ይኼን ስሜት አልባና ሕገወጥ ተግባር በመቃወም ለፖለቲካ ፖርቲዎች የጋራ መድረክ፣ ለኢቲቪ አስተዳደር፣ በዋናነት የጉዳዩ ባለቤት ለኾነው ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አቤቱታ እንደምናቀርብ በዚሁ አጋጣሚ ለመግለጽ እንወዳለን።
መላው የአገራችን ሕዝብ በተለይም የአማራ ሕዝብ የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም ድምፅን ለመቀማት የሚንቀሳቀሱ አሠራሮችንና መዋቅሮችን የማውገዝና ያለመተባበር አቋም እንድትወስድ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
ሕልውናችንን በትግላችን እናስከበራለን!
እጣፋንታችንን በራሳችን እጆች እንጽፋለን!
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)
ያጋጠመንን ፈተና የምንሻገረው እውነተኛ ሕዝባዊነታችን ጠብቀን በመዝለቅ ነው!!! - ከአማራ ብልጽግና ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ!
አገራችን ኢትዮጵያ በለውጥ ሒደት ውስጥ ምትገኝ አገር ናት። በለውጡ ተስፋ ሰጭ ውጤቶች መመዘግብ የጀመሩበት ኢትዮጵያውን በአጠቃላይ እና በተለይም የአማራ ሕዝብ ለውጡን ደግፈው የቆሙበት ሁኔታ እንደነበር የሚታወስ ነው። ለለውጡ መቀስቀስ ምክንያት የኾኑ ሕዝባዊ ጥያቄዎች በተለይም የዴሞክራሲ ምህዳሩን የማስፋት፣ የወሰንና የማንነት ጥያቄዎች፣ የኢኮኖሚ ልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚያስችል እርምጃዎችና የተካሔዱ ሪፎርሞች፣ የማኅበራዊ ልማት ማሻሻያዎች፣ የሰብአዊ መብት አያያዝ ችግሮችን የመለየትና የማረም፣ የጸጥታ የፍትሕና የደኅንነት ተቋማት፣ የዴሞክራሲ ተቋማት፣ የሕግ ሪፎርሞች፣ የትላልቅ አገራዊ ሜጋ ፕሮጀክቶች ችግር ተፈቶ ወደ ሥራ ማስገባቱ፣ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ለውጥ … ወዘተ የለውጡ አበይት ትሩፋቶች የታዩባቸው ዘርፎች ናቸው።
ይሁንም እንጂ እነዚህ ተስፋዎች በተግዳሮች የተሞሉ ኾነው እናገኛቸዋለን። እነዚህ ተግዳሮቶች ውስጣዊና ውጫዊ ይዘትና ባህሪ ያላቸው ናቸው። አገራዊ ቀውሱን በማባባስ የተለያዩ የውጭ ኃይሎች እጅ ያለበት ቢኾንም ዋናው ግን የውስጥ ችግራችን ነው። ብልጽግና ፓርቲ ውስጥ መታረም ያለባቸው ውስጣዊ ችግሮች እንደተጠበቁ ሁነው የችግሮቻችን ሁሉ የመጀመያው የትሕነግ የክህደት ቡድን አገረ-መንግሥቱን የማፈረስ የጥፋት ሚና ሲሆን፤ ቀጥለው የሚመጡት ኦነግ ሸኔ፣ የጉሙዝ ታጣቂ ኃይልና በተከበረው የቅማንት ሕዝብ ስም የሚነግደው ቅጥረኛው ታጣቂ የሽፍታ ቡድን የችግሮቻችን ምንጭና የጥፋት ዘር የሚዘሩ ዋና የአገርና የሕዝብ ጠላቶች ናቸው። በእነዚህ ፀረ-ሕዝብ ኃይሎችና ተባባሪዎቻቸው በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች በተለይም በኦሮሚያ ክልል በወለጋ ዞኖች፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን፣ በአማራ ክልል በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞንና ሰ/ሸዋ፣ በማዕከላዊ ጎንደር በጭልጋ የተከሰቱ ዘርን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች የወገኖቻችን ሞትና የንብረት መውደም ያስከተሉ እጅግ ልብ የሚሰብር፣ ሰው በኾነ ፍጡር ሁሉ ሊደርስ የማይገባው ዘግናኝ አረመኒያዊ ድርጊት ተፈጽሟል።
የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ችግሩን ማውገዝ ብቻ ሳይኾን እስከመጨረሻው የሚታገለው በዘር ጥላቻ የመታወር የመርዘኛ አስተሳሰብ ድርጊትና ውጤት ነው ብሎ ያምናል። በዚህ አጋጣሚ በማንነታቸው በግፍ ለተጨፈጨፉና ለሞቱ ቤተሰቦች፣ የተፈጠረውን ችግር ለማስቆም መስዕዋትነት ለከፈሉ የፌደራልና የክልላችን የጸጥታ ኃይሎች ከልብ የመነጨ መፅናናትን እንመኛለን። አሁንም የአማራን ክልል ሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ በየግንባሩ የተሰለፋችሁ የፌዴራልና የክልላችን የጸጥታ ኃይሎች ለምታደርጉት ኃላፊነት የተሞላበት ተጋድሎ የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አድናቆትና ምስጋና ያቀርብላችኋል።
የአማራ ሕዝብ ባለበት ወይም በሚኖርባቸው የተለያዩ ክልሎች ሁሉ ከሌሎች ወንድም ሕዝቦች ጋር በሰላምና በፍቅር እንዲኖር ተመሳሳይ አስተዋጽኦ ለምታደርጉ አካላትም ላቅ ያለ ምስጋናችንን እያቀረብን ይህንን መልካም ተግባር አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉና የወንድማማች ሕዝቦችን ሰላምና ደኅንነት እንድታስጠብቁ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
የጥፋት ኃይሎች በአንድ በኩል ዘርን መሠረት አድርገው የሚደርሱ ጥፋቶችን የብሔር መልክ እንዲይዝ ሲያደርጉ ሌላ ጊዜ ደግሞ የሃይማኖት ገጽታ እንዲኖረው በማድረግ የጥፋት አጀንዳቸውን ማባሪያ እንዳይኖረው በተለዋዋጭ አጀንዳዎች ቀወስ ሲያቀጣጥሉ ይታያሉ።
ይህ እውነታ እንደተጠበቀ ኾኖ በቅርቡና ሰሞኑን በምዕራብ ወለጋ፣ በመተከል፣ በአጣዬና አካባቢው የተፈጠሩ ማንነት ተኮር ጥቃቶችና ይህን ተከትሎ በወገኖቻችን ላይ የደረሰው የሞት፣ ሀብትና ንብረት መውደም መፈናቀል የአማራን ሕዝብ በእጅጉ አሳዝኗል።
የአማራው ሞትና መፈናቀል መልኩን እየቀያየረ በመቀጠሉ በሕዝቡ ዘንድ ቁጭትና ብስጭትን ፈጥሯል። ይህን ሁኔታ በመጠቀም ምንጩ የሚታወቅና የማይታወቅ የፌስቡክና ሌሎች የማኅበራዊ ሚዲያ አውታሮችን በመጠቀም እርስ በእርሳችን እንድንተላለቅ የጦርነት ድግስ የሚደግሱና እርስ በርሳቸው የሚገፋፉ መልእክቶችንና ምስሎችን በማኅበራዊ ሚዲያ በመለጠፍ ችግሩ እንዲባባስ ለማድረግ ሲሰሩ ይታያል። ሌሎች ደግሞ የብሔርና የሃይማኖት ፅንፍ በመስበክ ችግሩን ከድጡ ወደ ማጡ ለመውሰድ የቀውስ አጀንዳዎችን ሲያቀጣጥሉ ይስተዋላሉ።
ይህን ተከትሎ በአማራ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች የተፈጸመውን የግፍ ጭፍጨፋ፣ የሰው ሞት፣ የንብረት መውደምና መፈናቀል ለማውገዝ እና መንግሥት አስቸኳይ እርምጃ በመውሰድ እንዲያስተካክል ለመጠየቅ ሰላማዊ ሰልፎች ተካሒደዋል።
በሠለጠነና ጨዋነትን በተላበስ መንገድ የደረሱ ጉዳቶችንና ጥፋቶችን ደግመው እንዳይከሰቱ ማውገዝና መንግሥትን የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድ መጠየቅ የዴሞክራሲያዊነትና ጤናማ አስተሳሰብ ያላቸው ዜጐች መገለጫ ነው።
ፓርቲያችን ብልጽግና እነዚህ ጥያቄዎች ተገቢና ተቀባይነት አላቸው ብሎ ያምናል። ማመን ብቻ ሳይኾን የአማራ ሕዝብ ሞትና መፈናቀል በዘላቂነት እንዲቆም ይታገላል፤ በተጨባጭም የፖለቲካና የጸጥታ ሥራዎችን ሌትና ቀን እየሰራ ይገኛል። በዚህ መንፈስና ስሜት ለተሣተፉና ሰልፉ ሰላማዊ ኹኖ እንዲጠናቀቅ ለጸጥታ ኃይሉ ተደማሪ ጉልበት የኾኑ የሕብረተሰብ ክፍሎችን የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ክብር አለው።
በሌላ በኩል የተካሔዱት ሁሉም ሰልፎች ለጥፋት ኃይሎችና የመጠፋፋት ነጋሪት ለሚጎስሙ አካላት እንዳቀዱትና ሊፈጥሩት ካሰቡት ጥፋት አኳያ መጠቀሚያ ከመኾን ወጦ በሰላማዊ መንገድ ወደ ቤቱ እንዲመለስ መደረጉ የሚያስመሰግን ነው። የጸጥታ ኃይላችን ሕዝባዊነትም ከለውጡ ወዲህ መገንባት ስለጀመረው ነፃና ገለልተኛ ተቋም ማሳያ ኾኖ የሚጠቀስ ነው። ለዚህም ሰልፉ ከጅምሩ እስከ መጨራሻው ሰላማዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ ላደረጋችሁ የክልላችን የጸጥታ ኃይል አባላት የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ምስጋናና አክብሮት ያቀርብላችኋል።
ይሁን እንጂ የተካሔዱ ሰልፎች ምንም እንኳ በሰላም ተጠናቀቁ ይባል እንጅ በአንዳንድ ከተሞች ከተጠሩበት ሕዝባዊ ዓላማ ውጭ ኾነው አግኝተናቸዋል። የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ምርጫው በሰላማዊና ዴሞከራሲያዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ ሥራ ላይ ባለበት በተቃራኒው ዓላማ ተይዞ የተካሔደ በመኾኑ ጉዳዩን አሳሳቢ ያደርገዋል።
የሰልፎቹ ዓላማ ከላይ የተገለጸው ሕዝባዊ አጀንዳ ኾኖ ሳለ በጽንፈኛ ኃይሎች ተጠልፎ የእነሱ ተልዕኮና የፖለቲካ አጀንዳ ማስፈጸሚያ ለማድረግ ሙከራ አድርገዋል።
ምንም እንኳ እነዚህ በሰልፉ የተሳተፉና ከሰልፉ ዓላማ ውጭ ሲንቀሳቀሱ የተስተዋሉ አካላት/ቡድኖች የአማራ ክልል ሕዝብን የሚወክሉ ባይኾኑም ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጩ፣ ፊት የሚያዟዙሩ፣ ጥላቻና መጠራጠርን የሚያሰፉ አሳፋሪ ኩነቶችን ሲያከናውኑ ተስተውለዋል።
የአማራና የኦሮሞ ሕዝብ ለዘመናት በአብሮነት የኖሩ የማይለያዩ ትስስር ያላቸው በደምና በአጥንት የተጋመዱ ሕዝቦች ናቸው። እነዚህ ሕዝቦች በመከራም ኾነ በደስታ አብረው ያሳለፉ፣ ረዥሙ የኢትዮጵያ ታሪክ ሲመዘዝ ከአንድ ምንጭ የሚቀዱ ሕዝቦች ናቸው። እነዚህ ሕዝቦች ከሌሎች የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ጋር አገር ያቆሙ፣ የውጭ ወራሪ ኃይልን በጋራ መሥዋእትነታቸው መመከት የቻሉ ሕዝቦች ናቸው። በዚህ ሒደትም በታሪክ ዳገትና ቁልቁለት አብረው ወጥተዋል አብረው ወርደዋል። የወደፊቱ እጣፈንታቸውም በአብሮነትና በወንድማማችነት መቀጠል አለበት ብለው በጽኑ የሚያምኑ የአገር ዋልታና ማገር የኾኑ ሕዝቦች ናቸው።
በሰልፉ የደም ነጋዴዎች እንዳሉት አንዳችን ሌላችን ልናጠፋ ከቶውንም ጤናማ በኾነ አዕምሮ ሊታሰብ የማይችል ተርት ተረት ሲናገሩ አዳምጠናል። የተራመደው አፀያፊ ሀሳብ ሕዝባችንን የማይወክል መኾኑ ብቻ ሳይኾን የአማራ ብልጽግና ፓርቲና መላው ሕዝባችን በጽናት ቁመን የምናወግዘውና የምንታገለው እኩይ አስተሳሰብ ነው። የአማራና የኦሮሞ ሕዝቦች በጽናት አብረው ይዘልቃሉ፣ አገርንም ያሻግራሉ። ትላንት አብረው በመቆም የውጭ ወራሪ ኃይሎችን እንደመከቱት ሁሉ ዛሬም ኾነ ነገ የጋራ ዕጣ ፈንታችውን አብረው ይወስናሉ::
ሌላው በዚህ ሰልፍ የታየው አፍራሽ እንቅስቃሴ ፓርቲያችን ብልጽግናን በማውገዝ ላይ የተመሰረተ የአማራን ክልል የሁከትና የብጥብጥ ማእከል በማድረግ ቀጥተኛ ተጠቂና ሕዝባችን ለአደጋ ተጋላጭ እንዲኾን የሚያደርግ ነው። ይህ ድርጊት የአማራ ሕዝብ ያለበትን የጸጥታና የፖለቲካ ሁኔታ ያላገናዘበና ይልቁንም ለከፋ ሁኔታ የሚዳርግ የተሳሳተ መንገድ ኾኖ ይታያል።
እርግጥ ነው በሀሳብ የተገነባውን የብልጽግና ፓርቲ በአደባባይ ውግዘት ዝቅ ማድረግ እንደማይቻል እነሱም ጠንቅቀው ያውቁታል። አማራን ያለወንድማማችነት ፖለቲካ ነጥለው መንዳት የሚፈልጉ ፅንፈኛ ኃይሎች በሀሳብ ሞግተው ማሸነፍ እንደማይችሉ በመረዳታቸው ብቸኛ አማራጫቸው ከዚህ ያለፈ ሊኾን አይችልም።
ብልጽግና ፀረ-ኢትዮጵያና ፀረ-አማራ የኾነውን ጠላት ትሕነግን ለአንዴና ለመጨረሻ ወደ መቃብር እንዲወርድ ያደረገ፣ የተዘረፍነውን ማንነታችንና ነፃነታችን መልሶ ያጎናፀፈንና አንገታችን ቀና እንድንል ያደረገ በፈተናዎች መካከል ትርጉም ያለው ድል የሚያስመዘግብ ተራማጅ የኾነ ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ፓርቲ ሲሆን የአማራ ሕዝብም የሚያውቀው ሐቅ ነው። ይህ የታየው ውንጀላ በጥቂት ለአማራ ሕዝብ የሚታገሉ የሚመስሉ ነገር ግን የአማራን ሕዝብ ማኅበራዊ እሴቶች በማይወክሉ ጠላቶቻችን ታስቦ የተነገረ እርባና ቢስ ድርጊት ነው። የአማራ ብልጽግና ፓርቲ በአማራ ሕዝብ ዘንድ በጽኑ መሠረት ላይ እንዲቆም የምንሠራ ብቻ ሳይኾን ፀረ-ብልጽግና ኃይሎችን ፊት ለፊት በጽናት እንፋለማቸዋልን።
ከሰልፉ ዓላማ ውጭ የተነሳው ሌላው ጉዳይ ከፌዴራል እስከ ክልል በሚገኘው አመራራችን ላይ የደረሰው የውግዘት፣ የማጥላላትና ስም የማጥፋት ዘመቻ ነው። የአማራ ሕዝብ መሪውን አክባሪ የተከበረና የዳበረ ማኅበራዊ፣ ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶች ያሉት ወረተ-ብዙ ሕዝብ ነው። ከምንም በላይ ደግሞ መከባበር ሲወርድ ሲዋረድ የኖረና አሁንም ያለ ማኅበራዊ እሴቱ ነው። ነገር ግን ከዚህ ወርቃማ እሴት ባፈነገጠ መንገድ ጥቂት ግብረ-ገብነት የጎደላቸው በጥላቻ የሰከሩ ግለሰቦች ከፓርቲያችን ፕሬዝዳንት ጀምሮ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችን በስም በመጥራት፣ ማውገዝ፣ አልፎ ተርፎም በገዳይ አስገዳይ በመፈረጅ በድፍረት ተናግረዋል። ይህ የብልጽግናን አመራር ከአማራ ሕዝብ ለመነጠል ለማስጠላት የተደረገ ሴራ የወለደው ግልጽ ጥቃት ነው። ነገር ግን የአማራ ሕዝብ ብልሕና አስተዋይ ሕዝብ ነው። ከቶውንም ሊቀበላቸው ቀርቶ ሊያዳምጣቸውም አይፈቅድም። ይልቁንስ ድርጊታቸውን በትዝብት የተመለከተና ቆም ብሎ እየኾነ ስላለው ነገር እንዲያስተውል አድርጐታል። አብዛኛው ሰውም ድርጊቱን በግልጽ ነቅፎታል። በአንጻሩ ደግሞ እኛ የብልጽግና አመራሮች ይህ ሁኔታ ለሕዝባችን ተጠቃሚነት ስንል የበለጠ የሚያጠነክረን እንጂ ከቶውንም ከእርምጃችን አንድ ስንዝር ወደኋላ ሊመልሰን አይችልም። በተለመደው የጽናትና የአሸናፊነት ወኔ ትግላችን አጠናክረን የብልጽግና ጉዟችን እንደምንቀጥል የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ያረጋግጣል።
በሰልፉ ላይ የሕዝቡን እውነተኛና ፍትሐዊ ጥያቄ ጠልፈው ለፖለቲካ ዓላማቸው ሊጠቀሙበት ያሰቡ ኃይሎች እነማን እንደኾኑ በድርጊቱ ራሳቸውን አጋልጠዋል። የሰልፉ ታዳሚ ጥቂት ግለሰቦች ከላይ ከተገለጹት እኩይ ተግባራት በተጨማሪ ከአብን በስተቀር የብልጽግና ፓርቲ እና የሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች የምርጫ ምልክትና ባነሮች ከተሰቀሉበት ቢልቦርድ ወርደው እንዲቃጠሉና እንዲቀደዱ ተደርጓል። በአንዳንድ አካባቢዎች የምርጫ አስፈጻሚዎች ተረጋግተው ሥራቸውን እንዳይሰሩ ወከባ ሲፈጥሩ የዋሉም አሉ። ይህም የሕዝቡን እውነተኛና ፍትሐዊ ጥያቄ ጠልፎ ለራሱ ስግብግበ ዓላማ በሚያመች መልኩ ስልፉን ሲያስታባርና ሲመራ የዋለው አካል ማን አንደኾነ በግልጽ የታየበት ነው። ይህ ብቻ ሳይኾን በሰልፉ የተላለፉ መልእክቶች የማን ፍላጐትና ዓላማ እንደኾነ ጭምር በይፋ የተመለከትንበት ነው።
ድርጅታችን ብልጽግና ይህ ድርጊት ፍጹም ሕገወጥ፤ ፍጹም ወንጀል ነው ብሎ ያምናል። በመኾኑም የምርጫ ቦርድና ሌሎች የሕግ አስከባሪ አካላት ጉዳዩን አጣርተው ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰዱ ጥሪያችን እናቀርባለን። በአጠቃላይ የተፈጸሙ ድርጊቶች የተከበረውን የአማራ ሕዝብ አንሶ ማሳነስ የታየበት ያላዋቂዎች ጨዋታ ኾኖ አግኝተዋል።
በመጨረሻም የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ሕዝባችን ያነሳቸውን ፍትሐዊ ጥያቄዎች ይቀበላል፤ ነገር ግን አጀንዳውን ለራሳቸው የፖለቲካ ዓላማ ጠልፈው እየተጠቀሙበት ያሉ ኃይሎች የጥፋት መንገድ በእጅጉ ያሳሰበዋል። ፓርቲያችን ይህን እኩይ ተግባር ከመላው የአማራ ሕዝብና ከሌሎች አገርና ሕዝብ ወዳድ ከኾኑ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር በጋራ በመታገል አገርና ሕዝብን ከጥፋት ለመታደግ ዝግጁ መኾናችን ደግመን ደጋግመን ለመላው የክልላችንና የኢትዮጵያ ሕዝብ እናረጋግጣለን።
በመጨረሻም በአማራ ሕዝብ ሞትና መፈናቀል እጃቸው ያለበትን ማናቸውንም የጥፋት ኃይሎች ለሕግ ለማቅረብና አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ቁርጠኛ መኾናችንን ለሕዝባችን ለማረጋገጥ እንወዳለን።
የወቅቱን ፈተና እንረዳለንና ያጋጠመንን ፈተና የምንሻገረው እውነተኛ ሕዝባዊነታችን ጠብቀን በመዝለቅ ነው!!!
“ቅድሚያ ለአገርና ለሕዝብ እንቆማለን!!!”
የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት
ሚያዚያ 13 ቀን 2013 ዓ.ም.
ባሕር ዳር



