ከስምንት ቢሊዮን ብር በላይ የኤፈርት ገንዘብ በፍርድ ቤት መታገዱን ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ገለጸ

በሕወሓት ኤፈርት ድርጅት ሥር ይተዳደሩ ከነበሩት ጥቂት ድርጅቶች
ሕወሓት ለወንጀል መፈጸሚያነት ሊጠቀምበት ነበር የተባለ 6.7 ቢሊዮን ብር እንዳይሸሽ ተደርጓል
ኢዛ (ማክሰኞ ሚያዝያ ፲፱ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. April 27, 2021)፦ በኤፈርት ሥር በሚተዳደሩ እና ተያያዥ ድርጅቶች ላይ በተከናወነ የሀብት ክትትልና ምርመራ ሥራ ከ8 ቢሊዮን ብር በፍርድ ቤት እንዲታገድ መደረጉንና የሕወሓት ቡድን 6.7 (ስድስት ነጥብ ሰባት) ቢሊዮን ብር ለወንጀል መፈጸም እንዳይችል መከላከል እንደቻለ የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አስታወቀ።
ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ዛሬ ማክሰኞ ሚያዝያ 19 ቀን 2013 ዓ.ም. በመረጃ ገጹ እንዳስታወቀው፤ የሕወሓት ሕገወጥ ቡድን በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ከፈጸመበት ማግስት ጀምሮ ሕገወጥ ቡድኑ ሲቆጣጠራቸው የነበሩ፣ እንዲሁም ገንዘብና ንብረታቸውን ለሕገወጥ ዓላማው ሊጠቀምባቸው ይችላል በሚል በተጠረጠሩ ድርጅቶች ላይ ባደረገው ክትትል ውጤታማ ሥራዎች መገኘታቸውንም ገልጿል።
በጦርነቱ በተሳተፉ የጦር መኮንኖችና ሌሎች ባለሥልጣናት ላይም በተደረገ የሀብት ክትትልና ምርመራ ውጤታማ ሥራዎች ስለመመዝገባቸውም የሚጠቅሰው ይኸው መረጃ፤ ኢትዮጵያን ከድተው ከሕወሓት ጋር በመኾን በጦርነቱ የተሳተፉ ዋና ዋና ተጠርጣሪዎች ሀብትና ንብረት ስለመታገዱ ገልጿል። (ኢዛ)