Sudanese soldiers

የሱዳን ወታደሮች

የኢትዮጵያ ጸጥታ ኃይል ምላሽ መስጠቱ ተሰምቷል

ኢዛ (ዓርብ ሚያዝያ ፳፪ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. April 30, 2021)፦ የኢትዮጵያን ድንበር ጥሳ ትንኮሳዋን በግልጽ እያሳየች ያለቸው ሱዳን፤ ወታደሮቸዋ ዛሬ ዓርብ ሚያዝያ 22 ቀን ማለዳ በምዕራብ ጎንደር ዞን አካባቢ ለሰዓታት የቆየ ተኩስ ከፍተው እንደነበር እና የግብርና ካምፖችን ማቃጠላቸው ተሰማ።

ከንጋቱ 11 ሰዓት ጀምሮ እስከ ረፋዱ አራት ሰዓት ድረስ በሱዳን ወታደሮች ተከፍቶ በነበረው ተኩስ፤ በምዕራብ ጎንደር ዞን መንዶካ ውስጥ “እንዲብሎ” በተባለ አካባቢ ያሉ የባለሀብቶችን የእርሻ ካምፖች ማቃጠላቸውን የጀርመን ድምፅ ዘግቧል።

የአካባቢውን ነዋሪዎች በዋቢነት የጠቀሰው ይኽ ዘገባ፤ ከፍተኛ ድምፅ ያላቸው መሣሪያዎችን ሲተኩሱ ነበር። ጥቃቱ የተፈጸመባት መንዶካ ከሱዳን ድንበር በሰባ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ናት።

ለዛሬ ሌሊቱ የሱዳን ወታደሮች ጥቃት፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ ሚሊሺያዎች እና ሌሎች የጸጥታ ኃይሎች የአጸፋ እርምጃ በመውሰድ፤ የሱዳን ወታደሮች ወደመጡበት እንዲመለሱ አድርገዋል ተብሏል።

የመተማ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ለጀርመን ድምፅ እንዳመለከቱት፤ የመከላከያ ሠራዊቱ እና ሌሎች የጸጥታ ኃይሎች ጥቃቱ ወደ ተፈጸመበት ቦታ እንዲላኩ መደረጉን እና ሁኔታው አሁን ስለመረጋጋቱ እንደጠቀሱለት ዘግቧል።

የሱዳን ሠራዊት በኃይል ወደ ኢትዮጵያ ድንበር በመግባት የያዛቸውን ቦታዎች እንዲለቅ ከኢትዮጵያ መንግሥት የቀረበለትን ጥያቄ ገሸሽ በማድረግ፤ አሁንም ጥቃት እየሰነዘረ ለመኾኑ የዛሬው ድርጊቱ አመላክቷል።

ኢትዮጵያ ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መጀመሪያ የሱዳን ወታደሮች ከያዙት ቦታ ይልቀቁ የሚል ጥሪ ማስተላለፏ ይታወሳል። ከሱዳን ወገን ግን እንዲህ ላለው የኢትዮጵያ ጥሪ ምላሽ በመንፈግ ሠራዊቷን ለወራት በኢትዮጵያ ድንበር ውስጥ እንዳሰፈረች ነው።

ዛሬ በተፈጸመው ጥቃት ዙሪያ የኢትዮጵያ መንግሥት እስካሁን ማረጋገጫ ያልሰጠ ሲሆን፤ ስለጉዳዩ እስካሁን ምንም ዐይነት መግለጫም አልሰጠም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሱዳን በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር የገባችውን የውዝግብ አጀንዳ ይዘው አፍሪካውያን ይደግፉት ዘንድ ወደ ተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ጉዞ የጀመሩ ሲሆን፤ የመጀመሪያ መዳረሻቸውን ኬንያ አድርገዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ