ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል

ሱዳን የእኔ ነው በማለት የይገባኛ ጥያቄ ያቀረበችበትና የህዳሴ ግድብ የሚገኝበትን የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል

የህዳሴ ግድብ የሚገኝበትን የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሱዳን ይገባኛል ላለችው፤ ኢትዮጵያ ምላሽ ሰጠች

ኢዛ (ማክሰኞ ሚያዝያ ፳፮ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. May 4, 2021)፦ የሱዳን መንግሥት ከወራት በፊት በኃይል የያዘችው የኢትዮጵያ መሬት ሳያንስ፤ አሁን ደግሞ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የሚገኝበትን የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልልን ይገባኛል ማለትዋ ሱዳን ቅጥ ያጣችና ልክ እያለፈች መኾኑን የሚያሳይ ነው ሲል የኢትዮጵያ መንግሥት ገለጸ።

ትናንት የሱዳን መንግሥት የቤንሻንጉል ክልል ይገባኛል የሚለውን ጭፍን መግለጫዋን ተከትሎ፤ ዛሬ የኢትዮጵያ መንግሥት ባወጣው መግለጫ ሱዳን ልክ እያለፈች መኾኗን አጽንዖት ሰጥቶ ድርጊቷን ተቃውሟል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ በትናንቱ የሱዳን መንግሥት መግለጫ ላይ ተመርኩዘው ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ ሱዳን የቤንሻንጉል ክልል ይገባኛል ማለትም አስነዋሪና ከሕግ ውጪ ከመኾኑም በላይ፤ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚጻረር ነው ብለዋል።

“ሁሉም እንዲረዳው የምንፈልገው፤ ሱዳን በተለይ የኢጋድ ሊቀመንበር ኾና ሳለ ከሕግ ውጭ የሆነ ተግባር መፈጸሟ የሚኮነንና አሳፋሪ መኾኑን መግለጽ እንወዳለን” ያሉት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤ ሱዳን የኢትዮጵያ መሬት ከወረረች በኋላ የምታወጣቸው መግለጫዎችም ያልተገቡ እንደነበሩ አስታውቀዋል።

ሱዳን ቅጥ ያጣውን አካሔዷን እና ያልተገቡ መግለጫዎቿን በትዕግሥት ስትከታተል የቆየች ስለመኾኗም አመልክተው፤ በአጠቃላይ የሱዳኖች ድፍረት ቅጥ ያጣ መኾኑ የሚያስማማ ነው በማለትም የሱዳንን ወቅታዊ አካሔድ ኮንነዋል።

“ታላቁን የሱዳን ሕዝብ ኢትዮጵያ እንደምታከብርና ጉርብትናውን እንደምትፈልግ፣ አብሮ መኖር እንደምትፈልግ፤ ነገር ግን ይህንን የሚያደርግ ሱዳን የሱዳንን ጥቅም የወከለ ሳይኾን ከዚህ ቀደም ስንለው እንደነበረው በሌሎች ተገፋፍቶ የሌሎችን ጥቅም ይዞ የሚሔድ እየኾነ ነው” በማለትም፤ ሱዳን እያካሔደች ያለችው ድርጊት በሌሎች ግፊት ጭምር መኾኑን አስረድተዋል።

ከዚህ ሌላ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ሱዳን ለጠየቀቻቸው ጥያቄ ሁሉ ምላሽ ማግኘቷን በማስታወስም፤ የግድቡን አሞላል እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በቂ ምላሽና ማብራሪያ እንደተሰጡም ተናግረዋል።

እንዲህም ኾኖ ግን በሱዳን ቡድን በኩል እየታየ ያለው ነገር በተጻራሪው ነው። የኢትዮጵያን (ጉድ ዊል) እንደ ድክመት ነውና የቆጠረው፤ ተገቢ እንዳልኾነም በዛሬው የአምባሳደሩ መግለጫ ተወስቷል።

“ኢትዮጵያ ይህንን ሁሉ የምታደርገው ለሰላም ካላት ጽኑ ፍላጐትና ለቀጠናው ካላት አክብሮት ነው” ያሉት ቃል አቀባዩ፤ በጐረቤት አገሮችና በኢትዮጵያ መካከል ግጭት በመፍጠር የሚጠቀሙ ሌሎች ኃይሎች ያሰፈሰፉ እንደኾነና ይህን በተግባር እያየች ስለኾነ ሌላ ነገር የሌለ መኾኑን አስረድተዋል።

በሱዳን በኩል እየተደረገ ያለው ቅጥ ያጣ ተግባርን በተመለከተ ከዚህ በኋላ የሚሰጠው ምላሽ ከታየ በኋላ በሒደት የሚኾነው ነገር ይታያልም ተብሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኤርትራው ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ ኦፊሳላዊ ጉብኝት ለማድረግ ካርቱም ገብተዋል።

ይህ ጉብኝት በአሁኑ ወቅት በምሥራቅ አፍሪካ እየሞቀ ካለው ፖለቲካዊ ትኩሳት አንጻር የሱዳንና የኤርትራ ፕሬዝዳንቶች የሚመክሩበት ይኾናል። በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል የገቡበት ፍጥጫም አጀንዳቸው ሊኾን እንደሚችል ተገምቷል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!