መሥራቾቹ ኢዲኃሕ፣ ኦፌዲን፣ ሶዲኃቅ፣ ዓረና፣ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳና አቶ ስዬ አብርሃ ናቸው

Ethiopia Zare (ማክሰኞ ሰኔ 17 ቀን 2000 ዓ.ም. June 24, 2008)፦ በዛሬው ዕለት በሀገር ውስጥ የሚገኙት የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ሕብረት (ኢዲኃሕ)፣ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኦፌዲን)፣ የሶማሌ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ቅንጅት (ሶዲኃቅ)፣ ዓረና ትግራይ ለዲሞክራሲና ለሉዓላዊነት (ዓረና) የተሰኙት በሀገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱት ፓርቲዎች ከቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ እና ከአቶ ስዬ አብርሃ ጋር በመሆን “መድረክ ለዲሞክራሲያዊ ምክክር በኢትዮጵያ” (መዲምኢ) በሚል ስያሜ አብረው ለመሥራት መስማማታቸውን ለኢትዮጵያ ዛሬ የደረሰው ዘገባ አስረዳ።

 

ተቃዋሚ ድርጅቶቹና ግለሰቦቹ ታዋቂ ኢትዮጵያውያንና የፖለቲካ ሰዎች በተገኙበት በጋራ ለመሥራት መግለጻቸውንና መግለጫ ማውጣታቸውን ለኢትዮጵያ ዛሬ ከኢትዮጵያ የደረሰው ዘገባ አስረድቷል። መድረኩ ዛሬ ባውጣው መግለጫ ላይ “መድረክ ለዲሞክራሲያዊ ምክክር በኢትዮጵያ” (መዲምኢ) ለተሰኘው የምክክር መድረክ መጀመር መነሻ የሆኑትን አስር የጋራ ግንዛቤ ነጥቦችን ካስቀመጠ፣ መርኆቹንና የመድረኩን የጋራ ግቦች ካሰፈረ በኋላ መሥራቾቹ አብረው ለመሥራት መስማማታቸው ተገልጿል።

 

ከተጠቀሱት አስር መነሻ የጋራ ነጥቦች ውስጥ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እየተረገጡ መሆናቸው፣ የሕግ የበላይነት በሥርዓቱ እየተጣሰ መሆኑ፣ የፍትህ ሥርዓቱ ነፃና ገለልተኛ አለመሆኑ፣ ማኅበራዊ ፍትህ መጓደሉ፣ ሃሳብን በነፃ መግለጽ መታቀቡና የፖለቲካ ፓርቲ አደራጅቶ መታገል ለከፋ እንግልት የሚዳርግ መሆኑ አፋጣኝ መፍትሔ የሚያሻው ችግር ሆኖ ስላሳሰባቸው መሆኑ ተጠቅሷል።

 

የኢህአዴግ መንግሥት የኢትዮጵያን ዳር ድንበርና ሉዓላዊነት የማስከበር ኃላፊነትና ግዴታ ሊወጣ ያለመቻሉ በእጅጉ እንዳሳሰባቸው የምክክር መድረኩ መሥራቾች በጋራ ነጥባቸው ላይ አስፍረዋል።

 

የኢትዮጵያን መሰረታዊ ችግሮች በሠላማዊ የፖለቲካ ውድድር አሸንፈው በሚወጡ አማራጮች ለመፍታትና የመቻቻል ፖለቲካዊ ባህልን ለማዳበር የሚያስችልና የዲሞክራሲ ሥርዓትን እውን ለማድረግ የትግል ትብብር መፍጠር የወቅቱ የኢትዮጵያ ህዝብ አንገብጋቢ ጥያቄ መሆኑን እንዳጤኑ መሥራቾቹ በመግለጫቸው አስፍረዋል።

 

መሥራቾቹ ካሰፈሯቸው የጋራ ግንዛቤ ነጥቦች ውስጥ እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ላይ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች ቢያንስ በመለስተኛ ፕሮግራም ዙሪያ በመሰባሰብ የኢትዮጵያን ህዝብ አስተባብረው በሠላማዊ መንገድ የሚደረገውን ትግል በተጠናከረ ሁኔታ በመቀጠል በፖለቲካው ውድድር አሸንፎ የሚወጣ አማራጭ ሆነው በመቅረብ፣ ለመንቀሳቀስ ያለመቻላቸውን ድክመት መገንዘባቸውንና ገልጸዋል።

 

በእነዚህና በመግለጫቸው ባሰፈሯቸው አስር የጋራ የግንዛቤ ነጥቦች ላይ ተስማምተው የመድረኩን መርኆች እና የጋራ ግቦች ላይ በመመስረት “መዴምኢ” በሚል ስያሜ የምክክርና የውይይት መድረክ አብረው ለመሥራት መስማማታቸውን አስታውቀዋል። መድረኩ መርኆቹን ለሚቀበሉና ለሚያሟሉ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ቡድኖችና ግለሰቦች ሁሉ በአባላቱ ሙሉ ስምምነት ክፍት እንደሚሆን አሳውቀዋል።

 

መድረኩ ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች የሚከበሩባትና ማኅበረ - ኢኮኖሚያዊ ፍትህ የሰፈነባት፣ በብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች እኩልነት ላይ የተመሰረተች፣ የበለጸገች ኢትዮጵያን መገንባት የጋራ መርኁ መሆኑን በአምስት ነጥቦች አስፍሯቸዋል። ከዚህም ሌላ የመድረኩን የጋራ ግቦችም እንዲሁ በአምስት ነጥቦች በዝርዝር አስቀምጧቸዋል።

 

በመጨረሻም “በኢትዮጵያ ተንሰራፍቶ ያለውን ፈርጀ ብዙ ችግሮች ለማስወገድና ተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች ዙሪያም ያለውን ተባብሮ ለመሥራት ያለመቻል ድክመት ለመቅረፍ የተወጠነው መልካም ጅምር የመላውን ህዝባችንን ድጋፍ እንዲያገኝ ጥሪ እናደርጋለን” ሲል መግለጫው ህዝባዊ ጥሪ አስተላልፏል። (ሙሉ መግለጫውን አስነብበኝ

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!