ዶክተር ሙሉ ነጋ ትግራይን ከማስተዳደር ኃላፊነታቸው ተነሱ
ዶ/ር አብርሃም በላይ፣ አዲሱ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ
ዶ/ር አብርሃም በላይ ሥልጣኑን ተረክበዋል
ኢዛ (ረቡዕ ሚያዝያ ፳፯ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. May 5, 2021)፦ ባለፉት ስድስት ወራት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመኾን ሲያገለግሉ በነበሩት ዶ/ር ሙሉ ነጋ ምትክ ዶ/ር አብርሃም በላይ መሾማቸው ተነገረ።
ዶ/ር አብርሃም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በመኾን በማገልገል ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ ዛሬ ይፋ በተደረገ መረጃ ትግራይን የማስተዳደር ኃላፊነት ተረክበዋል።
ባለፉት ሦስት ዓመታት በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ በመሥራት ከትግራይ ብልጽግና ፓርቲ በቀዳሚነት የሚጠቀሱ አመራር ሲሆኑ፤ የብልጽግና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልም ናቸው።
ከዚህ ኃላፊነታቸው ባሻገር፤ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የቦርድ ሊቀመንበርና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቦርድ አባል በመኾን እያገለገሉ ይገኛሉ።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመኾን ሲያገለግሉ የቆዩት ዶክተር ሙሉ ነጋ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እየተወጡ አይደለም የሚል ተደጋጋሚ ትችት ሲቀርብባቸው እንደነበር አይዘንጋም።
አሁን ክልሉን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት እንዲመሩ የተሰየሙት ዶ/ር አብርሃም በአመራር ብቃታችውም ኾነ በሥነምግባራቸው በብዙዎች የሚወደሱ እንደኾኑ ይነገራል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በትግራይ ክልል የታወጀው የስድስት ወር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ትናንት የተጠናቀቀ መኾኑ ታውቋል። (ኢዛ)



