PM Dr. Abiy Ahmed visiting the Grand Ethiopian Renaissance Dam with Dr. Abraham Belay

ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ (ግራ መጀመሪያ ላይ ያሉት) የህዳሴ ግድብን በጎበኙበት ወቅት፣ ዶ/ር አብርሃም በላይ (ከግራ ሦስተኛ ላይ ያሉት)

ከሦስት ሳምንት በፊት ለለቀቁት መሥሪያ ቤት የቦርድ ሰብሳቢ ኾነዋል

ኢዛ (ሰኞ የካቲት ፪ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. February 10, 2020)፦ በቅርቡ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚነት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ተነስተው፤ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር እንዲኾኑ የተሾሙት ዶ/ር አብርሃም በላይ፤ በዋና ሥራ አስፈፃሚነት ሲመሩት የነበሩት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልን በቦርድ ሊቀመንበርነት እንዲመሩ ተጨማሪ ኃላፊነት ተሠጣቸው።

የሕወሓቱ አባል ዶ/ር አብርሃም አዲሱ ኃላፊነት የተሠጣቸው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መኾኑንም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታውቋል። በዚህ መሥሪያ ቤት የነበራቸው መልካም አስተዋጽኦ አዲስ ከተመደቡበት የሚኒስትርነት ሹመት በተጨማሪ በቅርብ የሚያውቁትን መሥሪያ ቤት በቦርድ ሰብሳቢነት እንዲመሩ መደረጉ ተገልጿል።

ዶ/ር አብርሃም በላይ ከነሐሴ 2010 ዓ.ም. ጀምሮ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል (ኢኤኃ) ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኾነው ሲያገለግሉ ቆይተው ባለፈው ጥር 2012 ዓ.ም. የኢኖቬሽን ሚኒስትር ኾነው መሾማቸው አይዘነጋም። ዶ/ር አብርሃም የኢኤኃ ዋና ሥራ አስፈፃሚነቱን ሹመት በወቅቱ አግኝተው የነበሩት፤ በአሁኑ ወቅት ከሜቴክ ጋር በተያያዘ በሙስና ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸው ከኢንጂንየር አዜብ አስናቀ ምትክ እንደነበር ይታወቃል።

ዶ/ር አብርሃም ወደ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከመምጣታቸው ቀደም ብሎ በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ የሳይበር ቴክኖሎጂ ኢንጂንየሪንግ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር በመኾን አገልግለዋል። ዶ/ር አብርሃም በቅርቡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቦርድ አባል ኾነው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መሰየማቸው ይታወቃል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ