ማዕድናት በምርት ገበያ በኩል ሊገበያዩ ነው
ስምምነቱን የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ኢንጂንየር ታከለ ኡማ እና አቶ ወንድማገኘሁ ነገራ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዛሬ ዓርብ ሚያዝያ 29 ቀን 2013 ዓ.ም. በሀያት ሬጀንሲ ሆቴል ተፈራርመዋል
ምርቱን በጥራት በማምረት ለአገር ውስጥ እና ለዓለም አቀፍ ገበያዎች በስፋት ለማቅረብ ግብይቱን በዘመናዊ ሥርዓት ለማካሔድ ያስችላል ተብሏል
ኢዛ (ዓርብ ሚያዝያ ፳፱ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. May 7, 2021)፦ የአገሪቱ የከበሩ ማዕድናት በኢትዮጵያ የምርት ገበያ በኩል እንዲገበያዩ ለማድረግ የሚያስችል ስምምነት ዛሬ ተፈርሟል። ምርቱን በጥራት በማምረት ለአገር ውስጥ እና ለዓለም አቀፍ ገበያዎች በስፋት ለማቅረብ ግብይቱን በዘመናዊ ሥርዓት ለማካሔድ ያስችላል ተብሏል።
በኢትዮጵያ ምርት ገበያ እና በማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር መካከል ዛሬ በተደረገ ስምምነት መሠረት፤ ከዚህ በኋላ የከበሩ ማዕድናት በምርት ገበያው በኩል እንዲገበያዩና ለዚህም በጋራ ለመሥራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራርመዋል።
የአገሪቱን የማዕድናት ምርት በጥራት በማምረት ለአገር ውስጥ፣ አህጉራዊ እና ለዓለም አቀፍ ገበያዎች በስፋት ለማቅረብ እንዲቻል ግብይቱን በዘመናዊ የግብይት ሥርዓት ለማካሔድ የሚያስችል መኾኑን በስምምነቱ የፊርማ ሥርዓት ላይ ተገልጿል።

ስምምነቱን የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ኢንጂንየር ታከለ ኡማ እና አቶ ወንድማገኘሁ ነገራ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዛሬ ዓርብ ሚያዝያ 29 ቀን 2013 ዓ.ም. በሀያት ሬጀንሲ ሆቴል የተፈረመ ሲሆን፤ የመግባቢያ ሰነዱ ዋና ዓላማ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በዘመናዊ የምርቶች ግብይት ሥርዓት፣ በግብይት ሰንሰለት ቅንጅት፣ በኤሌክትሮኒክ ግብይት ጥራትና በመጋዘን ኦፕሬሽን ያካበተውን ሰፊ ልምድ መተግበር ነው። የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር የአገሪቱን የማዕድን ዘርፍ በመምራት ካለው ተሞክሮ ጋር በማጣመር በኢትዮጵያ ዘመናዊ የማዕድናት ግብይት ማዕከል እና ሥርዓት መዘርጋት ነው። ይህም በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሀብቶችና ኢትዮጵያዊያን አምራቾች ግልጽ የኾነ አሠራርን በማስፈን (በመዘርጋት) እኩል ተጠቃሚነትን የሚያሰፍን መኾኑን ስምምነቱን አስመልክቶ የወጣው መግለጫ ያመለክታል።
በስምምነቱ መሠረት በምርት ገበያው መገበያየት የሚጀምሩት እንደ ኦፓል፣ ኢመራልድ፣ ሳፋየር፣ ታንታለም፣ ሊቲየም፣ ፖታሽ፣ ብረትና የመሳሰሉት ምርቶች ናቸው።
ሌሎች የከበሩ ማዕድናትም ተለይተው በምርት ገበያው በኩል እንደሚገበያዩም ተገልጿል። ይህ ስምምነት ከዚህ በኋላ ማዕድናት በምርት ገበያው በኩል እንዲገበያዩ የሚያስችል ሲሆን፤ ይህንን ወደ ተግባር ለመቀየር አሁን ያሉት የሚኒስቴሩ መሥሪያ ቤት የማዕድናት ግብይትን የሚመለከቱ መመሪያዎች ማሻሻያ ይደረግባቸዋል ተብሏል።

የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ታከለ ኡማ እንዳመለከቱት፤ ግብይቱ በዚህ መንገድ መካሔዱ የማዕድን የወጪ ንግድን በ40 እና በ50 በመቶ ማሳደግ የሚችል መኾኑን ነው።
እስካሁን ያለው የማዕድን ግብይት በዘፈቀደ የሚካሔድና በሕገወጥ መንገድ የሚካሔደው ግብይት ጐልቶ የወጣበት በመኾኑ፤ ስምምነቱ ወደ ሕጋዊ መንገድ የሚያስገባ ነው ተብሏል። የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድማገኝ ነገራም ስምምነቱ የወጪ ንግድን ለማሳደግ የራሱ የኾነ አስተዋጽኦ አለው።
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለፉት 13 ዓመታት ቡና፣ ሰሊጥና ሰባት የግብርና ምርቶችን ብቻ በማገበያየት የሚታወቅ ሲሆን፣ አሁን ማዕድን ምርቶችን ይጀምራል። (ኢዛ)



