National Election Board of Ethiopia (NEBE)

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ (ምርጫ 2013)

በአዲስ አበባ 1,212,073 ዜጎች ተመዝግበዋል

ኢዛ (ቅዳሜ ሚያዝያ ፴ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. May 8, 2021)፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዛሬ ቅዳሜ ሚያዝያ 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው መረጃ ለስድስተኛው አገራዊ ምርጫ 2013 የተመዘገቡ የመራጮች ቁጥር 31,724,947 መድረሱን አስታወቀ። በአዲስ አበባ 1,212,073 ዜጎች ተመዝግበዋል።

ከእነዚህ እስካሁን ከተመዘገቡት መራጮች ውስጥ 54 በመቶ ወንዶች 46 በመቶ ደግሞ ሴቶች ናቸው።

በመራጮች ምዝገባና ተያያዥ ጉዳዮች ቦርዱ ያወጣው መግለጫ የሚከተለው ነው። (ኢዛ)

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመራጮች ምዝገባ እና ተያያዥ ጉዳዮች የተሰጠ መግለጫ

መግቢያ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከምርጫ ሒደት መካከል ዋና የኾነውን የመራጮች ምዝገባን እያከናወነ ይገኛል። በዚህም መሠረት እስካሁን የተመዘገቡ መራጮች ቁጥር ጊዜያዊ 31,724,947

• ወንድ 54%

• ሴት 46 %

የመራጮች ምዝገባ የሚደረግባቸው ጣቢያዎች ቁጥር 43,017

በመራጮች ምዝገባ ወቅት ያጋጠሙ ችግሮች

የመራጮች ምዝገባ በሚከናወንበት ወቅት ያጋጠሙ ዋና ዋና ችግሮች

- የመራጮች ምዝገባ ዘግይቶ መጀመር (በቁሳቁስ ስርጭት የተነሳ)

- የመራጮች ምዝገባ በመጀመሪያዎቹ ሳምንታት የተመዝጋቢዎች ቁጥር ዝቅተኛ መኾን

- የመራጮች ምዝገባ ከተጀመረ በኃላ የምርጫ ጣቢያዎች እና የተመዝጋቢዎች አለመመጣጠን በተለይ በአዲስ አበባ በጋራ መኖሪያ ቤቶች

- የአስፈጻሚዎች ክፍያ መዘግየት

- በተወሰኑ ቦታዎች (በተለይ በአዲስ አበባ) የአስፈጻሚዎች ኃላፊነትን በአግባቡ አለመወጣት

- በጸጥታ ችግር የተነሳ የመራጮች ምዝገባ ማድረግ ባልተቻለባቸው ቦታዎች በልዩ ሁኔታ የሚደረግ መኾኑ

የመራጮች ምዝገባ ላይ ላጋጠሙ ችግሮች የተሰጡ መፍትሄዎች

- የመራጮች ምዝገባ ቀናትን ማራዘም

- የመራጮች ምዝገባ የቁሳቁስ ስርጭትን አስመልክቶ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር ትብብርን ለማጠናከር ሙከራ ማድረግ

- የመራጮ ምዝገባ መልእክቶችን እና መረጃዎችን ማሰራጨት ሥራን መጨመር (አጭር የስልክ መልእክቶች፣ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ትብብር፣ የሲቪል ማህበራት ቅስቀሳ… ወዘተ)

- ከፓርቲዎች እና ከዜጎች (በ778 ነጻ የስልክ መስመር) የሚመጡ ጥቆማዎችን ከምርጫ ኦፕሬሽን ሥራዎች ጋር በማቀናጀት መፍትሄ መስጠት

- የጸጥታ ችግር ባለባቸዉ ቦታዎች ልዩ እቅድ እና ዝግጅት በማድረግ ከየክልሎቹ የጸጥታ ተቋማት ጋር በመተባበር የአስፈጻሚዎች ስልጠና እና የቁሳቁስ ስርጭት የተከናወነ ሲሆን፤ ከዚህም በተጨማሪ የመራጮች ምዝገባ ከሚያዝያ 29 ጀምሮ እንዲከናውንባቸው ተወስኗል (4ቱ ወለጋ ዞኖች (24 ምርጫ ክልሎች)፣ ካማሽ (4 ምርጫ ክልሎች) እና አማራ ክልለ ኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞን (3 ምርጫ ክልሎች) ልዩ ሁኔታ ምዝገባ እያከናወኑ ይገኛሉ።

የመራጮች ምዝገባ በአዲስ አበባ

በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር የመራጮች ምዝገባ በ1600 በላይ በኾኑ ምርጫ ጣቢያዎች ላይ የሚከናውን ሲሆን፤ በዋናነት ከፍተኛ የሰው ቁጥር ባላቸው የጋራ መኖርያ ቤቶች አካባቢዎች የመራጮች ምዝገባ በተለያየ ምክንያት ሲስተጓጎል ነበር ። ቦርዱ

1. የመራጮች ምዝገባ 1500 ከሞላ በኋላ አዲስ ንዑስ ጣቢያዎችን ለመክፈት የሚወስደው ጊዜ ክፍተት መኖሩን ተረድቷል

2. የምርጫ ክልል አስፈጻሚዎች ምርጫ ጣቢያዎች ላይ የሚያደርጉት ክትትል ማነስ እንደነበር ተገንዝቧል።

3. ንዑስ ጣቢያዎች ከተከፈቱም በኋላ በተደጋጋሚ ቅሬታ የሚነሳባቸው ቦታዎች ላይ በተደረገ የመስክ ቅኝት ጣቢያዎች ቁሳቁስ ሳይደርሳቸው ንዑስ ጣቢያዎችም ሳይከፈቱ ተገኝተዋል (በምሳሌነት በምርጫ ክልል 17፣ ምርጫ ክልል 28)

4. የምርጫ ማስፈጸም ሒደቱ ላይ የዝቅተኛ እርከን የመስተዳድሩ አካላት ጣልቃ ገብነት ተስተውሏል። (ትክክለኛ ያልኾነ ስያሜ ያላቸው ባነሮች በየምርጫ ጣቢያው ማስቀመጥ፣ አስፈጻሚዎችን ሥራ መመሪያ መስጠት፣ በምርጫ ጣቢያ መገኘት፣ የተመዝጋቢዎችን ብሎኮች መወሰን...)

5. ምርጫ ጣቢያዎችን ለመክፈት የሚሰጡት ቢሮዎች በተለይ በጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ ከጋራ መኖሪያ ቤቶች ቦታዎች የራቁ መኾናቸው ይህም በተለይ በአራብሳ (ምርጫ ክልል 17)፣ የካ አባዶ (ምርጫ ክልል 28) የታዩ ናቸው።

እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ቦርዱ የወሰዳቸው ዋና ዋና ተግባራት

1. የንዑስ ጣቢያዎችን መከፈት እና የተዘጉ ምርጫ ጣቢያዎችን ሁኔታ አስመልክቶ በከፍተኛ የቦርዱ አመራሮች የተመራ የመስክ ጉብኝት በአዲስ አበባ ተደርጓል፣ ይህም በምርጫ ክልል 17፣ 28፣ 19 … በመሳሰሉት ቦታዎች ምርጫ ክልሎች እና ጣቢያዎችን አሰራር፣ ክፍት መኾን አለመኾን፣ የመራጮች መዝገብ ቅኝትን ያካትታል። ከቅኝቱ በመለስ ተጨማሪ አዲስ ምርጫ ጣቢያዎችን ከመክፈት በተጨማሪ 30 ንዑስ ምርጫ ጣቢያዎች በሁለት ምርጫ ክልሎች አንዲከፈቱ ተደርጓል። ይህም 1500 ሞልተው ንዑስ ሳይከፈትባቸው የቆዩ ጣቢዎችን ለመክፈት ነው።

2. ሙሉ ኃላፊነታቸው ይህ ኾኖ ሳለ ይህንን ሥራ በሚገባ ማስተባበር ያልቻሉ የምርጫ ክልል አስፈጻሚዎች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ ተወስዷል። ይህም ቁሳቁስ ስርጭትን አለመከታተል፣ ተጨማሪ ምርጫ ጣቢያ ፍላጎቶችን በሚገባ አለማስተናገድ እና የንዑስ ጣቢያ አከፋፈቶችን በአግባቡ አለመፈጸም እንዲሁም የመስተዳድር አካላት ጣልቃገብነት አለመቆጣጠርን ይጨምራል። ሰባት የምርጫ ክልል አስተባባሪዎች የሥራ ውል የተቋረጠ ሲሆን፤ የቦርዱን አዲስ አበባ ከተማ የምርጫ ዴስክ ኃላፊም ውላቸው ተቋርጧል። ከዚህም በተጨማሪ የኦፕሬሽን የሥራ ክፍል ሽግሽግ እና ተጨማሪ የሰው ኃይል ዝግጅት በማድረግ የውስጥ አቅም የማሻሻል ሥራዎች ተሰርተዋል።

3. ለአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር የታዩትን የአስተዳደር ጣልቃ ገብነቶች አስመልክቶ እንዲስተካከሉ ለከተማ መስተዳድሩ አሳውቀናል።

4. የምርጫ ጣቢያዎች እና የመራጮች ቁጥር አለመመጣጠን ባጋጠመባቸው የከተማው ቦታዎች ተጨማሪ ጣቢያዎችን የመክፈት እርምጃ ተወስዷል (ይህም አዲስ ቦታዎችን ከመስተዳድሩ ጋር በመነጋገር ማስመደብ፣ ቁሳቁስ ማሰራጨት እና አስፈጻሚዎችን መመደብ ይጨምራል)

5. ተጨማሪ የምዝገባ ቀናት መጨመራቸው እነዚህን ችግሮችም ለመፍታት ይረዳል ተብሎ ይታሰባል።

በዚህም መሠረት

በአዲስ አበባ ከተማ የጋራ መኖሪያ ቤቶች የሚገኙ የመራጮች ምዝገባ ችግሮችን ለመፍታት በአጠቃላይ አዲስ 47 ያህል ምርጫ ጣቢያዎችን ለመክፈት ከከተማ መስተዳድሩ ምርጫ ጣቢያ መክፈቻ ቦታዎችን የጠየቅን ሲሆን፣ የቁሳቁስ ስርጭቶች ቦታዎቹ ዝግጁ በኾኑባቸው አካባቢዎች ተከናውኗል፣ አሁንም እየተከናወነ ነው።

1. በጀሞ ኮንደሚኒየም 15 ተጨማሪ አዲስ ጣቢያዎችን ለመክፈት ከከተማ መስተዳድሩ 15 ለምርጫ ጣቢያነት የሚያገለግሉ ቦታዎች ተመድበው፣ ቁሳቁስ አሰራጭተናል

2. በአቃቂ ቃሊቱ ክፍለ ከተማ ቱሉዲምቱ ኮንዶሚኒየም 5 ተጨማሪ አዲስ ጣቢያዎችን ለመክፈት ከከተማ መስተዳድሩ ቦታ እንዲያዘጋጅ አሳውቀን 5ቱም ቦታዎች ተዘጋጅተው፣ ቁሳቁስ አሰራጭተናል

3. በአቃቂ ቃሊቱ ክፍለ ከተማ በገላን ኮንዶሚኒየም 5 ተጨማሪ አዲስ ጣቢያዎችን ለመክፈት ቦታ እንዲዘጋጅ አሳውቀን ከከተማ መስተዳድሩ 5 ቦታዎች ተዘጋጅተው፣ ቁሳቁስ አሰራጭተናል

4. በየካ ክፍለ ከተማ የካ አባዶ ኮንዶሚኒየም 10 ተጨማሪ አዲስ ጣቢያዎችን ለመክፈት የሚኾን ቦታ እንዲዘጋጅ ከከተማ መስተዳድሩ አሳውቀን እስካሁን 7 ቦታዎች ዝግጁ ኾነው፣ ቁሳቁስ ስርጭት ዛሬ እየተከናወነ ነው።

5. የካ ክፍለ ከተማ የካ ሃያት ኮንዶሚኒየም 1 ተጨማሪ ጣቢያ ለመክፈት ከተማ መስተዳድሩ ቦታ እንዲያዘጋጅ አሳውቀን ምላሽ እየጠበቅን ነው

6. በቦሌ ክፍለ ከተማ ቦሌ ሃያት 1 ተጨማሪ ጣቢያ ለመክፈት ከተማ መስተዳድሩ ቦታ እንዲያዘጋጅ አሳውቀን ምላሽ እየጠበቅን ነው

7. በቦሌ ክፍለ ከተማ አራብሳ ኮንዶሚኒየም ተጨማሪ 5 ጣቢያ ለመክፈት አሳውቀን ከከተማ መስተዳድሩ 5 ቦታዎች ተዘጋጅተው፣ የቁሳቁስ ስርጭት አጠናቀናል።

8. ቦሌ ክፍለ ከተማ ሰሚት ኮንዶሚኒየም ተጨማሪ አዲስ 5 ጣቢያ ለመክፈት አሳውቀን ምላሽ እየጠበቅን ነው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ