Ethiopian Election 2021

ሰኞ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. የድምፅ መስጫ ቀን

ሐረሪ እና ሶማሌ ክልልን አይመለከትም

ኢዛ (ማክሰኞ ሰኔ ፰ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. June 15, 2021)፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. በሚካሔደው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት በዕለቱ ሥራቸው ዝግ እንደሚኾን አስታወቀ። ሐረሪ እና ሶማሌ ክልልን አይመለከትም።

ዛሬ ማክሰኞ ሰኔ 8 ቀን 2013 ዓ.ም. በዚህ ጉዳይ ላይ የሰጠው መግለጫ የሚከተለው ነው። (ኢዛ)

ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኞ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. የድምፅ መስጫ ቀንን አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 6ተኛው አጠቃላይ ምርጫ የድምፅ አሰጣጥ ሰኞ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. እንዲከናወን መወሰኑ ይታወቃል። በዚህም መሠረት በዕለቱ የተመዘገቡ ዜጎች ሁሉ ድምፃቸውን ለመስጠት ይችሉ ዘንድ እና የደምፅ አሰጣጥ ሒደቱ ያለምንም የጸጥታ ችግር ይከናወን ዘንድ ቦርዱ የሚከተሉት ተግባራዊ እንዲኾኑ የምርጫ የፓለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና ሥነምግባር አዋጅ 1162/ 2011 አንቀጽ 161 የመተባበር ግዴታ መሠረት ለመንግሥታዊ እና ለማንኛውም መንግሥታዊ ላልኾኑ ተቋማት ያሳውቃል።

በዚህም መሠረት፣

- ዜጎች ዕለቱን ለድምፅ መስጫ ብቻ መጠቀማቸው ስለሚያስፈልግ፤ የፌዴራል እና የክልል (ከሐረሪ እና ከሶማሌ ክልል ውጪ) መንግሥታዊ ተቋማት ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ሥራ ዝግ እንዲያደርጉ

- ዜጎች ዕለቱን ለድምፅ መስጫ ብቻ መጠቀማቸው ስለሚያስፈልግ በክልሎች (ከሐረሪ እና ከሶማሌ ክልል ውጪ) እና በፌዴራል የሚገኙ ማንኛውም መንግሥታዊ ያልኾኑ እና የግል ተቋማት በተመሳሳይ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ዝግ እንዲያደርጉ እያሳወቀ

- የአስቸኳይ ጊዜ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት፣ ሆስፒታሎች፣ የዕለት ተዕለት አገልግሎት ሰጪዎችም (ሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶች፣ የትራንስፓርት አገልግሎት፣ ..) በዝግ ቀናት የሚያደርጉትን አገልግሎት በተመሳሳይ የሚያከናውኑ ሲሆን፤ የመተባበር ግዴታው እነዚህን ተቋማት እንቅስቃሴ መዘጋት አያስገድድም።

- የትራንስፓርት አገልግሎት በተለመደው መንገድ የሚቀጥል ቢኾንም፤ ዜጎች ድምፅ ከመስጠት ውጪ ከፍተኛ እንቅስቃሴን የሚፈልጉ ኹነቶችን እና እቅዶችን እንዳይይዙ እና እንቅስቃሴያቸውን ድምፅ ለመስጠት ብቻ እንዲያደርጉ ቦርዱ ያበረታታል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
ሰኔ 08 ቀን 2013 ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ