የምርጫው አንደምታ በጨረፍታ

ምርጫ 2013
- ምርጫ 2013 በሰላም እየተካሔደ ነው
- የፖለቲካ ድርጅቶች ምልከታ
- በአንዳንድ አካባቢዎች ችግሮች እየሰማን ነው ያሉም አሉ
ኢዛ (ሰኞ ሰኔ ፲፬ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. June 21, 2021)፦ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚወዳደሩ እጩዎች ውስጥ ብዙዎች በማለዳ ድምፅ ሰጥተዋል።
ከተፎካካሪ ፓርቲዎች የኢዜማው ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ የአብን ምክትል ሊቀመንበር ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ በግል የሚወዳደሩት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት እና የመሳሰሉት በጠዋት ድምፅ ከሰጡት ውስጥ ይጠቀሳሉ። በተለይ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ከሌሎች መራጮች በተለየ የኢትየጵያ በሚል አልባሳት ምርጫውን ሲመርጡ ታይተዋል።
እስከ ረፋዱ ድረስ በምርጫ ጣቢያዎች ድምፃቸውን ከሰጡ የመንግሥት ኃላፊዎች ውስጥ ደግሞ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር አብርሃም በላይ፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊ ሞገስ እና ሌሎች ባለሥልጣናት ድምፅ ሰጥተዋል። ድምፅ ከሰጡ በኋላ አስተያየታቸውን ከሰጡት ውስጥ አንዱ የኾኑት ፕሮፌሰር ብርሃኑ እስካሁን ድረስ በጸጥታው ረገድ ምንም ችግር ያልሰሙ መኾኑን ገልጸዋል። ነገር ግን በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች ከሎጀስቲክና ከአሠራር ጋር በተያያዘ ችግር ስለመኖሩ ጠቅሰዋል። ነገር ግን ሙሉውን መረጃ ከምርጫ በኋላ እንገልጻለን።
በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች ምርጫው ዘግይቶ ከመጀመሩ ጋር በተያያዘም “ይህንን ምርጫ ቦርድን መጠየቅ ነው። የሎጅስቲክ ችግር እንዳለ እያየን ነው። ነገር ግን ኾን ብሎ ምርጫውን ለማበላሸት እስካልኾነ ድረስ እንዲህ ዐይነት ችግሮች ትንሽ ይጠበቃሉ። ብዙ ችግር አይደለም። ዋናው ሰው ያለምንም እንቅፋት ምርጫውን ማካሔዱ ነው ዋናው” ብለዋል።
ሌላው ለሚዲያ አስተያየታቸውን የሰጡት የአብን ምክትል ሊቀመንበር ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ፤ “እኔ ድምፅ በሰጠሁበት የምርጫ ጣቢያ ላይ ያለው የድምፅ አሰጣጥ ሒደት በጣም የተረጋጋ፣ ሰላማዊና ሒደቱን ጠብቆ እየተካሔደ መኾኑን መረዳት ችያለሁ” ብለዋል። ነገር ግን ስለምርጫው ፍትሐዊነትና ነፃነት አጠቃላይ በድርጅታቸው በኩል አጠቃላይ ግምገማ ከተካሔደ በኋላ የሚሰጥ በመኾኑ አሁን ባሉበት ሁኔታ ስለ ምርጫው ነፃነትና ፍትሐዊነት መናገር ያስቸግራል ብለዋል።
“የድምፅ መስጠትና ቆጠራው ከተጠናቀቀ በኋላ አጠቃላይ ሁሉም የምርጫ ጣቢያዎቻችን ላይ የምናገኛቸውን ሪፖርቶች መሠረት አድርገን አብን እንደ ንቅናቄ መግለጫ ይሰጣል” በማለትም አክለዋል።
“የሕዝባችንን ድምፅ እናከብራለን ያሉት ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ፣ “ነገር ግን በሒደት ውስጥ በቅድመ ምርጫ ያጋጠሙንን አንዳንድ ችግሮች አሉ። አሁን በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች የደረሱን ሪፖርቶች አሉ። አንዳንዱ ላይ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታዎች አሉ፤ አንዳንዶች ላይ ቀለል ያሉ ጥሰቶች ተፈጽመዋል” ብለዋል።
ዞሮ ዞሮ ግን እነዚህ ሁሉ ሒደቶች በምርጫው ላይ ምን ተፅዕኖ አላቸው የሚለውን ግምገማ ካደረግን በኋላ ለሕዝባችን እናሳውቃለንም በማለት ተናግረው፤ በመርኅ ደረጃ ግን ሕዝቡ የሚሰጠውን ማንኛውም ድምፅ አብን አክብሮ ይቀበላል በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ደግሞ፤ የድምፅ መስጠቱ ሒደት እስኪጀመር ረጅም ሰዓታት መቆየታቸውን ገልጸዋል። በዚህ ቆይታቸው የመራጩን ሕዝብ ጽናትና የመምረጥ ጉጉት ሳላደንቅ አላልፍምም ብለዋል። በማለዳ ቅዝቃዜ ሳይበግረው ኢትዮጵያ በአንድ እጅ የምርጫ ካርድ በሌላ እጁ ችግኝ ይዞ ለመጣው የአዲስ አበባ ነዋሪ አክብሮቴ ትልቅ ነው ብለዋል።
የምርጫው መዘግየት ግን እርሳቸውም የታዘቡት እንደኾነ የገለጹት ወይዘሮ አዳነች፤ ይህ ይስተካከላል ብለው እንደሚያምኑም ጠቅሰዋል። (ኢዛ)