በዶክተር አብርሃም የሚመራው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ተኩስ አቁም እንዲደረግ በይፋ ጠየቀ
ዶክተር አብርሃም በላይ
ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ለቀረበው ጥያቄ ላይ ዘጠኝ ምክንያቶችን አስፍረዋል
ኢዛ (ሰኞ ሰኔ ፳፩ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. June 28, 2021)፦ በዶክተር አብርሃም በላይ የሚመራው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በትግራይ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ለፌዴራል መንግሥት ጥያቄ ማቅረቡን አስታወቀ። ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በቀረበው በዚሁ የተኩስ አቁም ጥያቄ ላይ ዘጠኝ ምክንያቶች ሰፍረዋል።
የጊዜያዊ አስተዳደሩ ለፌዴራል መንግሥት የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ጥያቄ ማቅረቡን የገለጹት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር አብርሃም በላይ ናቸው።
ዶ/ር አብርሃም በዚሁ ጉዳይ ለኢዜአ በሰጡት ማብራሪያ መንግሥት ሰብአዊነትን መሠረት ባደረገና ተጨማሪ ጉዳት በማያደርስ መልኩ እንዲደረግ ጥያቄ ማቅረባቸውን ነው።
ጥያቄውን ያቀረቡት ባለፈው ሳምንት መኾኑን በመግለጽ፤ ጥያቄው የቀረበው ከክልሉ ሕዝብ ተወካዮች፣ የቢሮና የዞን አመራሮች፣ በተለያዩ ቦታዎች ከሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ምሁራን፣ ባለሀብቶችና የሃይማኖት አባቶች ጋር ከመከረ በኋላ መኾኑንም ጠቅሰዋል።
አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በክልሉም ኾነ በአገሪቱ ላይ የፈጠረው ውስብስብ ችግር ወታደራዊ ብቻ ሳይኾን ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መኾኑን የገለጹት ሥራ አስፈጻሚው፤ እስካሁን የጊዜያዊ አስተዳደርና በፌዴራል መንግሥት የተለያዩ እርምጃዎች ሲወሰዱ መቆየታቸውንም አስታውሰዋል።
እንደ ዶክተር አብርሃም ገለጻ የተኩስ አቁሞ ስምምነት እንዲደረስ ጥያቄ እንዲቀርብ ከተፈለገበት ምክንያቶች አንዱ ክረምት እየገባ በመኾኑ፤ የትግራይ አርሶ አደሮች ተረጋግተው የእርሻ ሥራቸውን እንዲያከናውኑ የሚለው ይጠቀሳል። ከዚህም ሌላ የሰባዊ ድጋፍ ለተረጅዎች ያለምንም ችግር እንዲደርስ ወቅቱን የሚመጥን የፖለቲካ ምፍትሔ ለመስጠት እንደኾነም አመልክተዋል። ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተላከው ሙሉ ደብዳቤ ከዚህ በታች ቀርቧል። (ኢዛ)
ለኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር
አዲስ አበባ
ጉዳዩ፥ በሕወሓት የጥፋት ኃይል ምክንያት የተፈጠረውን የትግራይን ችግር ለመፍታት ሐሳብ ስለ ማቅረብ
በኢትዮጵያ ሕዝብ ግፊትና ፍላጎት የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ሕወሓት ከማዕከላዊ መንግሥት ጋር ቅራኔ ውስጥ መግባቱ ይታወሳል። የለውጡ መግፍኤ ምክንያት ሕወሓት በኢትዮጵያ ላይ ያስከተለው ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ቀውስ ነበር። ሕዝቡ ግን ሕወሓት ከስሕተቱ ታርሞ በለውጥ ሒደቱ የሚሳተፍበትን እድል ሰጥቶት ነበር። ይሄንን እድል መጠቀም ያልቻለው ሕወሓት ከለውጥ ሒደቱ መውጣት ብቻ ሳይኾን በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት፣ ሕልውናና የግዛት አንድነት ላይ የከፋ አደጋ መደቀን ጀመረ። በትግራይ ክልል ከሚፈጽመው የሽብር ድርጊትና ከሚጎስመው የጦርነት ነጋሪት በተጨማሪ በመላው አገሪቱ ሠርጎ ገቦችንና ቅጥረኞችን እያዘመተ፤ ከኢትዮጵያ የውጭ ጠላቶች ጋር እየተባበረ፤ ኹከትና ብጥብጥ፣ ግጭትና መፈናቀል ማምረት ቀጠለ።
ይሄንን የሕወሓት የሽብር ተግባር ለመቅረፍ መንግሥት ሦስት ዐይነት የመፍትሔ ሥራዎችን በየምዕራፉ አከናውኗል። የመጀመሪያው ሕወሓት የለውጡ አካል ኾኖ እንዲቀጥል በፓርቲና በመንግሥት መድረኮች እድሎች ተሰጥቶት ነበር። ይሄን እድል አልጠቀምም ብሎ፤ የመንግሥትን የሰላም እጅ ገፍቶ ጠቅልሎ ወደ ትግራይ ገባ። ከዚህ በኋላ በተለያዩ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ተሰሚነት ባላቸው አካላት በኩል የውይይትና የሰላማዊ ሒደት መንገዶች ተመቻችተውለት ነበር። ሕወሓት ግን “ወይ እኔ ብቻ እመራለሁ፤ ወይም አገር አፈርሳለሁ” ብሎ በያዘው አጥፊ አቋም የተነሳ የሰላም ጥረቶቹ ሁሉ ሊሳኩ አልቻሉም።
በመጨረሻም የጦርነት ነጋሪት እየጎሰመ፣ ወታደራዊ ዐቅሙን እያደራጀ ቆይቶ በሰሜን ዕዝ ላይ አሳዛኝና ታሪክ የማይረሳው ጥቃት ፈጸመ። ይህም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት፣ ሕልውናና የግዛት አንድነት አደጋ ውስጥ የሚጥል “ግልጽ እና ቅርብ አደጋ” ደቀነ። የፌዴራል መንግሥትም አገር ለማዳን በሕገ መንግሥቱ የተጣለበትን ኃላፊነት ለመወጣት ሲል ወደማይፈልገው ግጭት ገባ።
አጥፊው የሕወሓት ኃይል በጥቂት ጊዜ ውስጥ መቀሌን ለቅቆ፤ በየጥሻው ገባ። አብዛኛው አመራሩ ተገደለ ወይም ተማረከ። ያሠለጠነው ሚሊሻና ልዩ ኃይል የነበረው አማራጭ መሣሪያውን ደብቆ ከሕዝቡ ጋር መቀላቀል ነበር። የተወሰነው መሪ ኃይል ወደ በረሐ ሲወርድ አብዛኛው ሚሊሻና ልዩ ኃይል ግን አእምሮውን ትጥቅ ሳያስፈታ (disarmament of the mind) መሣሪያውን በየጥሻው ደብቆ ከሰፊው ሕዝብ ጋር ሰላማዊ መስሎ ተቀላቀለ። መንግሥት ዋና ዓላማው ለአገር አደጋ የኾነውን ከሃዲው የጥፋት ኃይል አደጋ ከማያደርስበት ደረጃ ማድረስና ለሕግ ማቅረብ በመኾኑ አብዛኛውን ተሰላፊና ተለጣፊ ኃይል በምሕረት ዓይኑ ነበር የተመለከተው።
ከሕግ ማስከበሩ ዘመቻ በኋላ የመንግሥት ዋና ትኩረት የተፈናቀለውን ሕዝብ መመለስ፣ አጥፊው የሕወሓት ኃይል ያፈረሰውን መሠረተ ልማት መልሶ መገንባት፣ ሰብአዊ ርዳታ እንዲደርስ ማድረግ እና ሰላምና ደኅንነትን በትግራይ ክልል ማስፈን ነበር። ለዚህም ሲባል የቴሌኮሙኒኬሽንና የመብራት መሠረተ ልማቶች እንዲጀመሩ፤ የጤናና የትምህርት አገልግሎቶች እንዲቀጥሉ፤ የባንክ አገልግሎቶች እንዲጀምሩ፤ አቁመው የነበሩ ፋብሪካዎች ወደ ስራ እንዲመለሱ፤ ቆመው የነበሩ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች እንዲጀምሩ፤ የፖሊስና የፍትሕ አገልግሎቶች እንዲጠናከሩ፤ የግብርና ግብአቶች እንዲቀርቡ፤ ለተረጅዎች በቂ ርዳታ እንዲቀርብ ከሚመለከታቸው የአገር ውስጥና የውጭ ተባባሪ አካላት ጋር በመኾን ሲሠራ ቆይቷል።
ይህ ሁሉ ቢኾንም ግን፣ የጥፋት ሃይሉ እየሠራ ባለው ተደጋጋሚ የአጥፊነት ተግባር እና የእርሱን ጩኸት እንደ ገደል ማሚቶ በሚያስተጋቡ አካላት የተነሣ የታሰበው ውጤት ሊመጣ አልቻለም። የኢትዮጵያ መንግሥት ከ100 ቢልዮን ብር በላይ ባለፉት ወራት ለርዳታ፣ ለመንግሥት አገልግሎት ማስቀጠል እና መሰረተ ልማት ግንባታ ሥራ አውሏል። ይሄም በሃገሪቱ አጠቃላይ ኢኮኖሚ በተለይ በሌሎች ክልሎች የሚያደርሰው ጫናም ከፍተኛ ነው። ክልሎች ከበጀታቸው ቀንሰው የትግራይ ክልልን ለማቋቋም ድጋፍ ሰጥተዋል። እርዳታ እንሰጣለን ለሚሉ አካላት ከሚጠበቀው በላይ ተሒዶ ምቹ ሁኔታዎችን ተከፍተዋል። ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያና ትራክተር ገዝቶ ለማድረስም ተሞክሯል። የአገር ውስጥና የውጭ ሚዲያዎች በቂ መረጃ የሚያገኙበትን ሁኔታ አመቻችቷል። ለዚህ ሁሉ ተግባሩ ግን መንግሥት ባጎረሰ ቁጥር የመነከስ ዕጣ ነው የገጠመው።
አጥፊው የሕወሓት ኃይል በአሁኑ ጊዜ የተበተነ ኃይል ነው። ነገር ግን ለብዙ ዘመናት በክልሉ በዘረጋው የፍርሐት መዋቅር በኩል ዜጎችን ያስፈራራል፤ ያስገድዳል፤ ይገድላል። ለዜጎች የርዳታ እህል እንዳይደርስ ያደናቅፋል፤ የርዳታ ሠራተኞችን ይገድላል። ዜጎች ርዳታ እንዳይቀበሉ ያስፈራራል፤ ከተቀበሉም ከሚሰጠው የርዳታ እህል ለጥፋት ቡድኑ በድብቅ እንዲያዋጡ ያስገድዳል። የትግራይ ሕዝብ በፍርሐትና በሥጋት እንዲኖር ሲል ይቃወሙኛል የሚላቸውን በገዳይ መዋቅሩ በኩል ያስገድላል። እስከዛሬም ድረስ ከ50 በላይ የመንግሥት ሠራተኞችና ባለሞያዎች በድብቅ አፍነዋል፣ አቁስለዋል ገድለዋልም። አንዳንዶቹም አስከሬናቸው የአራዊት እራት እንዲኾን አድርገዋል። ይህም ከማንም በላይ የታገልንለትን ሕዝብ የሚጎዳ ኾኖ አግኝተነዋል።
የአጥፊው የሕወሓት ቡድኑ ዓላማ ሕዝቡን የጦርነት ጋሻ ማድረግ ነው። በዚህም የተነሣ ሲቪሎች ተገድደው እንዲዋጉ ያደርጋል። ሕጻናትን እየመለመለ ለጦርነት ይማግዳል። ገበሬዎች የእርሻ ሥራቸው ትተው በረሐ ለበረሐ እንዲንከራተቱ ያስገድዳል። የትምህርትና የጤና አገልግሎት እንዳይኖር እና እንዳይሰራ ያሰናክላል። ለተለያዩ ሕዝባዊ አገልግሎቶች የሚሠማሩ ባለሞያዎችን ያስገድላል። በእናቶችና በሕጻናት መካከል ኾኖ ተኩስ ይከፍታል። ሲመታ ሲቪልያን ተመቱ ብሎ ይጮሃል። ለእርሱ የትግራይ ሕዝብ የሥልጣኑና የጥቅሙ መጠበቂያ ግንብ እንጂ ወገኑ አይደለም።
በተለይ አሁን ያለንበት ወቅት የእርሻ ወቅት ነው። በዚህ ወቅት ገበሬው ወደ ግብርና ካልገባ የዘር ወቅት ስለሚያልፍ በቀጣይ ገበሬው ለአመታት ተረጂ ኾኖ እንዲኖር ያደርገዋል። አሸባሪው ቡድን ይሄንን ቀውስ ራሱ እየፈጠረ ነገር ግን እንደ ኦሪት ፍየል የኢትዮጵያ መንግሥትና ሠራዊት ዕዳውን እንዲሸከሙለት ይፈልጋል። መንግሥትና የርዳታ ድርጅቶች ርዳታ እንዳያደርሱ፤ ለገበሬው ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ እንዳያቀርቡ እያሰናከለ ‘ሕዝብ ተራበ’ ብሎ ራሱ ይጮኻል። ምክንያቱም ሕወሓት መኖር የሚችለው የትግራይ ሕዝብ ሲሞት እና መከራ ስያገኝ ነውና።
በመኾኑም የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ባለፉት ጊዜያት በትግራይ ያለውን ሁኔታ አስመልክቶ ከክልሉ ሕዝብ ተወካዮች፣ ከዞንና ቢሮ አመራሮች፣ በተለያዩ ቦታዎች ከሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች፣ ከትግራይ ሙሁራን፣ ከባለሀብቶች እና ከሃይማኖት አባቶች ጋር ያደረገውን ተከታታይ ምክክር መሠረት በማድረግ፡-
1. በክረምቱ ወቅት ገበሬው ያለውን ዐቅም ተጠቅሞ ተረጋግቶ ማረስ እንዲችል ፋታ ለመስጠት፤
2. እስካሁን ድረስ ለችግረኞች ሁሉ ሊዳረስ የሚችል በቂ የእርዳታ እህል አለን። ነገር ግን በትግራይ ባለው ግጭት ምክንያት የሚተጓጎል ዕርዳታ አቅርቦት ተግባር እንዳይፈጠርና ለችግረኞች በተሻለ መንገድ የእርዳታ ቁሳቁስ ለማቅረብ እንዲቻል ለማድረግ፣
3. በተለይም በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ቤታቸው የፈረሰባቸውንና የሚሰቃዩትን ክረምቱ ሳይገባ መንግሥት ለመርዳት እንደሚስራው ሁሉ፣ በትግራይም ቤቱ የፈረሰበትን ተፈናቃይ በሰላም ወደ ቤቱ የሚመለስበትን መንገድ ለመክፈት፤
4. በረሃ ካለው ኃይል መካከል ከመንግሥት ጋር ተነጋግረው ወደ ሰላም መንገድ ለመምጣት የሚፈልጉ ኃይሎች በመፈጠራቸውና ለእነዚህ ኃይሎች የሰላም መንገድ መክፈት ስለሚያስፈልግ፣
5. እስከ ዛሬ ድረስ የመንግሥት ዋና ትኩረት የነበረው አገራዊውን ምርጫ ማሳካትና የሕዝብን ይሁንታ ማግኘት በሰላም በመጠናቀቁና መንግሥት የአገሪቱን ዋና ዋና ችግሮች በዘላቂነት ወደሚፈታበት አቅጣጫ ቢሄድ መልካም ነው ብለን ስለምናምን፣
6. አብዛኛው የጥፋት ኃይሉ አመራር የተማረከ፤ የተገደለና ጥቅም ከማይሰጥበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል። ነገር ግን ጥቂቶች ሕዝቡን አስገድደው የጦርነት ሽፋን በማድረግ የከፋ ጉዳት እያደረሱበት በመኾኑ እና ሰሞኑን በተደረጉ ግጭቶች አሸባሪው የጥፋት ኃይል ይበልጥ ለማዳከም በመቻሉ፣
7. የሕወሓት ርዝራዥ ኾን ብለው ሕዝቡን እንዲራብ በማድረግ ለሚድያ ፍጆታ ለመጠቀም እንቅስቃሴ እያደረገ በመኾኑ፣
8. ለትግራይ ሕዝብ ፖለቲካዊ መፍትሔ መፈለግ ያለበት መንግሥት እንጂ ለሕዝቡ ግድ የሌለው የሕወሓት የጥፋት ኃይል አይደለም። በመኾኑም መንግሥት ይበልጥ ቻይና ሆደ ሰፊ ኾኖ ፖለቲካዊ መፍትሔዎችን መስጠት ስላለበት፣
9. ሕዝቡ ፋታ አግኝቶ የመፍትሔው አካል የሚኾንበትን እድል ለማመቻቸት እንዲቻል፣
የፌዴራል መንግሥቱ ሰብአዊነትን መሠረት ያደረገ ተጨማሪ ጉዳት በማያስከትል መልኩ የተኩስ አቁም ስምምነት (Humanitarian Ceasefire) እንዲያደርግ በትግራይና በመላው ሰላም ወዳድ ሕዝብ ስም እንጠይቃለን።
ከሰላምታ ጋር



