በትግራይ የሚገኙ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጉዳይ አሳሳቢ ኾነ

የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች
ወላጆች ልጆቻችንን እያሉ ነው
ኢዛ (ሐሙስ ሰኔ ፳፬ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. July 1, 2021)፦ በትግራይ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ያሉ ተማሪዎች ደኅንነት እንዳሳሰባቸው የተማሪ ወላጆች እየገለጹ ነው።
መንግሥት በትግራይ የተናጠል የተኩስ አቁምን እርምጃ ከወሰደ ወዲህ የተማሪዎቹን ደኅንነት ለማወቅ እንኳን ተቸግረናል ያሉት ወላጆች፤ መንግሥት ልጆቻችንን ይስጠን እያሉ ነው።
የልጆቻችን ጉዳይ በእጅጉ እያሳሰበን ከመኾኑም ሌላ፤ ደኅንነታቸውን ለማወቅ እንኳን በመቸገራችን ከዚህ ጭንቅ እንድንወጣ መንግሥት ምላሽ ሊሰጠንም ይገባል እያሉ ይገኛሉ የተማሪዎቹ ወላጆች።
በዚሁ ጉዳይ የሣይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በዚህ ጉዳይ ትናንት ተማሪዎቹን በተመለከተ ከባለድርሻ ተቋማት እና አመራሮች ጋር እየመከረበት የሚገኝ መኾኑና የተማሪ ወላጆች በትዕግሥት እንዲጠብቁ ጠይቋል።
የተማሪዎቹ ወላጆች ግን ዛሬም በተለያዩ ሚዲያዎች የልጆቻቸው ጉዳይ የበለጠ እያሳሰባቸው መምጣቱን እያመለከቱ ነው።
በዚህ ጉዳይ ዛሬ ከመንግሥት በተሰጠ ተጨማሪ ማብራሪያ ደግሞ፤ ተማሪዎቹን በኢትየጵያ ቀይ መስቀል በኩል ከትግራይ ለማስወጣት እየተሠራ መኾኑን የሚጠቁም ሲሆን፤ ትናንት ሌ/ጄኔራል ባጫ ደበሌም የተማሪዎቹን ጉዳይ በቀይ መስቀል በኩል ለመጨረስ እየተሠራ መኾኑን መጥቀሳቸውም ይታወሳል። የኢትዮጵያ ቀይ መስቀልም ተማሪዎቹን ለማስወጣት ከመንግሥት ጋር እየተነጋገረበት ስለመኾኑ ተገልጿል። (ኢዛ)