አገሪቱ የበለጠ ቀውስ ውስጥ እንዳትገባ የብዙዎች ሥጋት ኾኗል

አገሪቱ የበለጠ ቀውስ ውስጥ እንዳትገባ የብዙዎች ሥጋት ኾኗል

“በአዲስ አበባ ተጠርጥረው የታሰሩ የትግራይ ተወላጆች ጉዳይ፤ በነዋሪዎች ላይ ማንነትን በመለየት ለጥርጣሬ እና መድልዎ የሚያጋልጥ ተግባር እንዳይኾን ሥጋት የሚያሳድር ነው” ኢሰመኮ

ያሳስቡኛል ያላቸውን ጉዳዮች አስታውቋል

ኢዛ (ቅዳሜ ሰኔ ፳፮ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. July 3, 2021)፦ መንግሥት በትግራይ ክልል የተኩስ አቁም ማወጁን ተከትሎ የግንኙነት መስመሮች መቋረጣቸው የሚያሳስበው መኾኑን እና መንግሥት የነዋሪዎቹን ደኅንነት ለመጠበቅ የሚረዱ እርምጃዎችን በአፋጣኝ ሊወስድ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮምሽን አስታወቀ።

ኮምሽኑ ዛሬ ቅዳሜ ሰኔ 25 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፤ በክልሉ የግንኙነት መስመሮች መቋረጣቸው እና በክልሉ የሚገኙ ነዋሪዎች የሚገኙበት ሁኔታ ያሳስበኛል ከማለቱም ሌላ፤ በትግራይ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ ተማሪዎችን ስለሚገኙበት ሁኔታ ተገቢው ምላሽና ማብራሪያ እንዲሰጣቸው እየጠየቁ መኾኑንም አስታውሷል።

ከዚሁ ከትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ በአዲስ አበባ የታሰሩ ሰዎች ሁኔታንም በዛሬው መግለጫ ላይ ያካተተ ሲሆን፤ ሊኾኑ ይገባቸዋል ያላቸውን ምክረ ሐሳቦችንም አካትቷል።

ኢሰማኮ ዛሬ ያወጣው መግለጫ የሚከተለው ነው። (ኢዛ)

ትግራይ ክልል፡ የሲቪል ሰዎችን ሁኔታ ለማሻሻል አፋጣኝ እርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም. የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ክልል የተኩስ አቁም ማወጁን ተከትሎ የግንኙነት መስመሮች በመቋረጣቸው፣ በክልሉ ነዋሪዎች የሚገኙበት ሁኔታ እንደሚያሳስበውና መንግሥት የነዋሪዎችን ደኅንነት ለማስጠበቅ የሚረዱ እርምጃዎች በአፋጣኝ ሊወስድ እንደሚገባ ገለጸ። በክልሉ የተቋረጡ መሠረታዊ አገልግሎቶችን መመለስና በትግራይ ክልል ስላለው ተጨባጭ የጸጥታ ሁኔታና የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት በቂ መረጃ መስጠት፣ በዚህ ረገድ ያሉ ክፍተቶችን ለማረምና የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ትብብር ለመፍጠር ቀዳሚ እርምጃዎች ናቸው።

ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትሔ ለማፈላለግ የሚደረገው ጥረት አስፈላጊነት እንደተጠበቀና በክልሉ ለሚደረጉ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦቶች ጥበቃና ለተደራሽነቱ ትብብር እንደሚቀጥል መገለጹ የሚበረታታ ኾኖ፣ የሲቪል ሰዎች ደኅንነትና ሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል። በአሁኑ ወቅት በአብዛኛዎቹ የትግራይ አከባቢዎች የመብራት፣ የስልክ እና የውኃ አገልግሎት በመቋረጡ በክልሉ ነዋሪዎች ላይ ከባድ የኑሮ ጫና እያስከተለ ይገኛል። የባንክ አገልግሎት መቋረጥና የጤና አገልግሎት አቅርቦትና ተደራሽነት ውሱንነት ችግሩን አባብሶታል።

በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ አገራዊና ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች የኤሌክትሪክ እና የስልክ አገልግሎት መቋረጥን ጨምሮ የሌሎች አቅርቦቶች እጥረት የሰብአዊ ድጋፉን በከፍተኛ ደረጃ እንደጎዳውና በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ነዋሪዎች፣ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና ስደተኞች ስለሚገኙበት ሁኔታ ማወቅ አስቸጋሪ እንዳደረገው ይገልጻሉ።

በአዲስ አበባ ከተማ የትግራይ ክልል ተወላጅ የኾኑ ነዋሪዎችና የሚዲያ ሰዎችን ጨምሮ፣ ሌሎች ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል ተጠርጥረው የታሰሩ ሰዎችን ሁኔታ ኮሚሽኑ በመከታተል ላይ ይገኛል። ይህም በነዋሪዎች ላይ ማንነትን በመለየት ለጥርጣሬ እና መድልዎ የሚያጋልጥ ተግባር እንዳይኾን ሥጋት የሚያሳድር ነው።

በተጨማሪም፣ በክልሉ ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩ ወጣቶች ወላጆችና ቤተሰቦች ተማሪዎቹ በአሁኑ ወቅት ስለሚገኙበት ሁኔታ ተገቢው ምላሽ እና ማብራሪያ እንዲሰጣቸው የሚመለከታቸውን የመንግሥት አካላት በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ የነዋሪዎችን ደኅንነት ማረጋገጥ ቀዳሚው የመንግሥት ግዴታ መኾኑን አስታውሰው፣ “በክልሉ የሚገኙ ነዋሪዎች ስላሉበት ሁኔታ የተገቢው መረጃ ማነስ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ከሚደመጡ ዘገባዎችና ንግግሮች ጋር ተዳምሮ ነዋሪዎችን ሥጋት ላይ የሚጥል ነው። የተኩስ አቁሙ በሁሉም በግጭቱ ተሳታፊ በነበሩ ወገኖች ሁሉ በቁርጠኝነት መከበር እና የመሠረታዊ አገልግሎቶች በአፋጣኝ መመለስ፣ አጠቃላይ ሁኔታውን ለማሻሻል፣ በትግራይ ክልል ለተፈጠረው ችግር ዘላቂ መፍትሔ ለማፈላለግ፣ እንዲሁም ሰብአዊ አቅርቦቱ እንዳይቋረጥ የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ነው። በተጨማሪም ማንኛውም ዐይነት እስር ሁልጊዜም ሕጋዊ ሥርዓትን የተከተለ ሊኾን ይገባል” ብለዋል። ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል የሚገኙ የመንግሥት እና መንግሥታዊ ያልኾኑ አካላት ሁሉ ሁኔታውን የሚያባብሱ፣ በሕዝቦች መካከል ጥላቻና ጥርጣሬን ሊፈጥሩ ከሚችሉ ንግግሮች እንዲቆጠቡ ጥሪ አቅርበዋል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ