በወቅታዊ የትግራይ ጉዳይ ኢዜማ አቋሙን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ
ሥጋቶቹንና መፍትሔ ያላቸውን ሐሳቦች አስቀምጧል
ኢዛ (ቅዳሜ ሰኔ ፳፮ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. July 3, 2021)፦ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በወቅታዊው የትግራይ ሁኔታ ላይ በመምከር የፓርቲውን አቋም ያለመከተበትን ሰፊ መግለጫ ዛሬ አውጥቷል።
በትግራይ ያለውን ወቅታዊ ችግር መነሻና ችግሩን ለመፍታት የተሔደበትን መንገድ በመጥቀስ ጭምር ሰፊ ትንታኔ የሚሰጠው የዛሬው የኢዜማ መግለጫ በመንግሥት መደረግ ሲገባው ያልተደረገ ያለውንም ያሰፈረበት ነው።
መግለጫው የትግራይ ክልል ሁኔታና ይበልጡኑም ደግሞ ይህ የተፈጠረው አዲስ ሁኔታ በአጠቃላይ ለአገሪቱ ሰላም፣ የፖለቲካ መረጋጋት፣ አገራዊ አንድነት እንዲሁም በቀጠናው የወደፊት ሰላም ላይ ሊያስከትል የሚችለውን አገራዊ ፈተናዎች የሚያስከትላቸው እንደምታዎች በመገምገም የደረሰበትን መደምደሚያ የቢኾንስ ግምቶችና መውጫ መንገዳቸውን ማስቀመጡን ያመለክታል።
ፓርቲው ዛሬ ያወጣው መግለጫ ሙሉ ቃል የሚከተለው ነው። (ኢዛ)
አገርን እና ሕዝብን ለመታደግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ ሊሰሩ የሚገባበት ወሳኝ ወቅት ላይ ደርሰናል!
ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) የተሰጠ መግለጫ
አገራችን ኢትዮጵያ በለውጥ ሒደት ውስጥ ከገባች ከሦስት ዓመታት በላይ አስቆጥራለች። በእነዚህ ሦስት ዓመታት በርካታ የአገርን ህልውና እና ቀጣይነት የተፈታተኑ ችግሮች አጋጥሟታል። ከነዚህ ችግሮች መካከል በዋነኛነት የሚጠቀሰው ባለፈው ጥቅምት ወር በአገራችን ሰሜናዊ ክፍል በትግራይ ውስጥ የተከሰተው ግጭት ነው። የሕወሓት አመራሮች የለውጡ ሒደት ከመጀመሩ በፊት የነበራቸውን ድርጅታዊ የበላይነት እየሸረሸረ በመምጣቱ ወደ ትግራይ ክልል በማፈግፈግ አቅማቸውን ማጎልበትና የለውጡ አመራርን በመፈታተን በለውጡ አካሄድ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ሲዘጋጁ ነበር።
በለውጡ አመራርና በሕወሓት መሪዎች መካከል ያለው ውጥረት በአደባባይ ወጥቶ መታየት የጀመረው ኢሕአዴግ የሚባለው ግንባር ፈርሶ ብልጽግና በሚባል ፓርቲ ሲተካ ሕወሓት የብልጽግና አካል ሳይሆን በቀረ ጊዜ ነበር። የድርጅቶቹ ትንቅንቅ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰው ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ የተነሳ የ2012 ዓ.ም ምርጫ መራዘሙን ተከትሎ ነው።
ሕወሓት የምርጫውን መራዘም ሕገ ወጥ ተግባር ነው በማለት በአደባባይ አቋሙን አሳውቆ በራሱ ክልል የፓርላማው የአምስት ዓመት ዘመን ከማለቁ በፊት ምርጫ እንደሚያደረግ ሲያሳውቅ የሕወሓትን በክልሉ ምርጫ የማድረግ ውሳኔ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ሕጋዊ አይደለም ብሎ ነበር። የሕወሓት መሪዎች ደግሞ የትግራይን ሕዝብ ምርጫ የማድረግ መብት የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ሊያግድ አይችልም፣ የምርጫ ቦርድ ምርጫን ለማስፈጸም የተቋቋመ ተቋም እንጂ የሕዝቦችን በመረጧቸው መሪዎች ለመተዳደር በሕገ መንግሥቱ የተሰጣቸውን መብት ለመከልከል ወይም ለመፍቀድ አይደለም በማለት በጳጉሜን ወር 2012 ዓ.ም የራሳቸውን ምርጫ አድርገው መንግሥት መስርተናል አሉ። የምርጫውን እወጃ ተከትሎ የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ በትግራይ ክልል የተደረገው ምርጫ ሕጋዊነት እንደሌለው በማሳወቅ ለትግራይ ክልል ከማዕከላዊ መንግሥት የሚሰጠው የበጀት ድጎማ ተመረጥኩ ላለው የክልሉ አመራር አካላት በማይደርስበት ሁኔታ ለሕዝቡ እንዲደርስ ውሳኔ አሳለፈ።
የሕወሓት መሪዎች ከመስከረም 30 በኋላ በብልጽግና ፓርቲ የሚመራውን የማዕከላዊ መንግሥት ሕጋዊነት ስለማይኖረው ከማዕከላዊ መንግሥት የሚመጣን ምንም ዐይነት ውሳኔ እንደማይቀበል አስታወቀ። ከዚሁ ውሳኔ ጋር በተያያዘ ለተለያዩ ጉዳዮች ከማዕከላዊ መንግሥት ወደ ትግራይ ክልል የሚላኩ ኃላፊዎችን ማጉላላት ሲፈልገውም ትግራይ ክልል አትገቡም በማለት መመለስ ጀመረ። ይህ የሕወሓት ተግባር በሕወሓትና በማዕከላዊ መንግሥት መካከል የተካረረ የሔደው ውጥረት ወደ መጨረሻ ደረጃ መድረሱን ያመላከተ ነበር። በመጨረሻም ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የትግራይ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ሠራዊት በትግራይ ክልል በሚገኘው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሰሜን እዝ በሰፈረባቸው በተለያዩ ቦታዎች ላይ ጥቃት በመፈጸም ከፍተኛ ጉዳት አደረሰ። ይህ ተግባር ሕወሓት በ2010 ዓ.ም የፌደራል መንግሥት ውስጥ የነበረውን የበላይነት ካጣ በኋላ አጠቃላይ አገራዊ አለመረጋጋት እንዲፈጠር ሌሎች ፅንፈኛ ኃይሎችን ጭምር በተለያዩ መንገዶች በመደገፍ ሲያደርግ የነበረው ሙከራን ወደሙሉ ውጊያ የወሰደ ነበር።
ሕወሓት የመከላከያ ሠራዊታችን ላይ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ የፌደራል መንግሥት የሕግ የበላይትን የማስከበር እርምጃ መውሰድ የጀመረ ሲሆን ከሦስት ሳምንት ውጊያ በኋላ የኢፌደሪ መከላከያ ሠራዊት መቐለ ከተማን ተቆጣጥሮ ነበር። መከላከያ ሠራዊቱ መቐለን ከመቆጣጠሩ በፊት የሕወሓት አመራሮች ወደበረሃ የገቡ ሲሆን የመከላከያ ሠራዊት የመቐለ ከተማን ከተቆጣጠረ በኋላ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 62/9 እና የፌደራል መንግሥት በክልል ጣልቃ የሚገባበትን አሠራር ለመደንገግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 359/1995 መሰረት ጊዜያዊ መንግሥት ክልሉን እንዲያስተዳደር ተቋቁሞ ነበር።
የተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ላለፉት ስምንት ወራት የክልሉን ሕዝብ ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል ምንም ዐይነት የፖለቲካ ማረጋጋት ሥራ ያልሠራ እና ለችግሩ መባባስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገ መኾኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡ እንደዚሁም ጊዜያዊ አስተዳደሩ ሕዝቡን ከማረጋጋት እና ችግሩን ከመቅረፍ ይልቅ ብልጽግና ፓርቲን ለመትከል የተደረገው መፍጨርጨር ችግሩን አወሳስቦታል። የሕግ ማስከበር እርምጃው ከተጀመረ በኋላ በክልሉ ውስጥ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን እና ዜጎች ወደመደበኛ ሕይወታቸው በተቻለው አጭር ጊዜ እንዲመለሱ ለማስቻል ሕወሓት ላይ እርምጃ ከመውሰድ ባሻገር ታስቦበት እና ታቅዶ የተተገበረ የተቀናጀ ግልፅ ተግባር አለመኖሩ፣ ግጭቱን በተበታተነ መልኩ ወደሚደረግ ሽምቅ ውጊያ ስልት የቀየረው ሕወሓት ውጊያ መቀጠሉ፣ በክልሉ ውስጥ ያለው ሰብዓዊ ቀውስ እየጨመረ ከመሄዱ ጋር ተደማምሮ በክልሉ ሰላምን ማረጋገጥ እና ዜጎችን ወደመደበኛ እንቅስቃሴ መመለስ ሳይቻል ቆይቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ችግሩ ተባብሶ በቀጠለበት ሁኔታ ውስጥ የፌደራል መንግስት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የተናጠል የተኩስ ማቆም ጥያቄን በመቀበል መከላከያ ሠራዊቱን በቅጽበት ካብዛኛው የክልሉ ክፍል አስወጣ። ይህ ሲሆንም በክልሉ ውስጥ የሚኖሩ ሰላማዊ ዜጎችን (ተማሪዎችን፤ የጊዜያዊ መንግሥት የታችኛው መዋቅር ሰራተኞችን...ወዘተ) እና የአገሪቱ ሰላምና ሉዓላዊነት ላይ ሊያመጣ የሚችለውን ችግር በቅጡ ከግምት ባላስገባ እና በተቻኮለ መልኩ መኾኑ በትግራይ ክልል የደረሰው ቀውስ ከክልሉም በላይ እንድምታ ወዳለው ከፍተኛ ምዕራፍ ሊሸጋገር ችሏል፡፡
ከዚህ አንጻር የኢዜማ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በወቅታዊ የትግራይ ክልል ሁኔታና ይበልጡንም ደግሞ ይህ የተፈጠረው አዲስ ሁኔታ ባጠቃላይ በአገሪቱ ሰላም፤ የፖለቲካ መረጋጋት፤ አገራዊ አንድነት እንዲሁም በቀጠናው የወደፊት ሰላም ላይ ሊያስከትል የሚችለውን አገራዊ ፈተናዎችንና የሚያስከትላቸውን እንድምታዎች ከገመገመ በኋላ የሚከተሉትን የቢሆንስ ግምቶች እና መውጫ መንገዳቸውን አስቀምጧል።
1. ቢሆንስ 1፤ አንደኛውና ከአገሪቱ ዘላቂ ጥቅም አንጻር ጥሩ ሊባል የሚችል የቢሆንስ ግምት (scenario)፤ መንግሥት እንደሚለው ይህ የተናጠል የተኩስ ማቆም በክልሉ ያለውን የሰብአዊ ቀውስ ለመታደግና የእርሻ ጊዜው እንዳያልፍና ወደ ከፋ የችጋር ሁኔታ ውስጥ እንዳይገባ በማሰብ የተደረገ እርምጃ መኾኑን በትግራይ ያሉት ታጣቂዎችም ሆነ ማኅበረሰቡ ተረድቶና አምኖበት በክልሉ ምንም ዐይነት የኃይል እንቅስቃሴ ቆሞና ሁሉም አካላት (የፌደራል መንግሥት፤ እርዳታ ሰጪ ተቋማት፤ የትግራይን አስተዳደር የተረከበው አካል...ወዘተ) ትኩረታቸውን ወደዚያ አድርገው በተቻለ መጠን በአጭር ጊዜ ችግሩን መቅረፍ የሚችሉበት፤ ከዚያም በኋላ ቀጣይ የፖለቲካ ጉዳዮችን በውይይት ለመፍታት ፍላጎት የሚታይበትና ወደ ሰላማዊ መፍትሔ የሚኬድበት ቢሆንስ ነው።
ምንም እንኳን ይህ ቢሆንስ ባጠቃላይ ሰላምን ከማንገሥና የሰብዓዊ ቀውሱን ለመታደግ ጥሩ የሚባል ቢሆንስ ቢሆንም እስከዛሬ በተለይም ባለፉት ሦስት ዓመታት ካየናቸው የባለድርሻ አካላት ባሕርይ አንጻር ሲታይ (ከመንግሥት፤ ከሕወሓት፤ ከእርዳታ ሰጪ አካላት...ወዘተ) በተለይም ደግሞ ሕወሓት በነኝህ ሦስት ዓመታትም ሆነ ከዚያ በፊት ለ27 ዓመታት በማዕከላዊ መንግሥት ሥልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ ጭምር ሲጫወት የነበረውን አፍራሽ ሚና በቅርብ ለተመለከተ፤ እውን የመኾን እድሉ እጅግ የመነመነ ነው፡፡ ከሕወሓት ባለፈ ግን በትግራይ ውስጥ ሕወሓት ለረጅም ጊዜ ያሰረጸው ያስተዳደር ሥርዓት ነፃ አስተሳሰብ እንዲሰፍንና ይህንን መሸከም የሚችል ጠንካራ የሲቪክ ማኅበረሰብ ሊፈጠር አለመቻሉ፤ ይህ ቢሆንስ እውን እንዲሆን የሚያስፈልገው ማኅበራዊ ግፊት እንዲኖር ሁኔታው ስለማይፈቅድለት ከሕወሓት በተቃርኖ ለዚህ ቢሆንስ የሚሠራ ኃይል ለማየት አስቸጋሪ ያደርገዋል።
2. ቢሆንስ 2፤ በትግራይ ያለው ያልጠራ ሁኔታ እንደቀጠለና የትግራይ አማጺዎች ከትግራይ ውጭ ሊያደርጉ የሚሞክሩት ግጭቱን የማስፋት ሙከራ (ወደ አጎራባች ክልሎች ወይም ከዚያም ዘልቆ ለመግባት) በፌደራል መንግሥቱ እየተመከተና እየከሸፈ የሚቀጥልበት፤ ግልጽ አሸናፊ የማይኖርበት ሁኔታ።
ሁለተኛውና ከመጀመሪያው የተሻለ የመኾን እድል ያለው የቢሆንስ ግምት ሕወሓት በአማራና በአፋር ክልሎች እና በኤርትራ በኩል መጠነኛ ትንኮሳዎችን የሚፈጽምበት፣ በትግራይ ውስጥም ከፍተኛ ቀውስ የሚፈጥርበት ሁኔታ ከተፈጠረ የፌደራል መንግሥት መከላከያ ሠራዊት ተመልሶ ለመግባት ሊገደድ ይችላል፡፡
ይህ ሁኔታ ከሕውሃት ባሕሪ እና ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር የመኾን እድሉ የማይናቅ ነው፡፡
በዚህ ሁኔታ፡-
- በአንዳንድ ከተማዎች ሕግና ሥርዓት የማስከበሩ ደረጃ ዝቅተኝነት የሚፈጥረውን አጋጣሚ በመጠቀም ዘረፋዎች ሊካሄዱ ይችላሉ።
- የእለት እርዳታ የሚያስፈልጋቸው የክልሉ ነዋሪዎች በሚፈለገው ደረጃ እርዳታ ሳያገኙ ቀርተው ለከፍተኛ አደጋ ሊጋለጡ ይችላሉ፣
- መሰረታዊ ለኑሮ የሚያስፈልጉ አገልግሎቶች፣ የውሃ፣ የመብራት፣ ህክምና፣ ግብዓቶች ማግኘት የማይቻልበት ሁኔታ ሊፈጠር የሚችልበት እድል ከፍተኛ በመኾኑ፣ የክልሉ ሕዝብ ለችግር የሚጋለጥበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል፣
- የክልሉን አስተዳደር እንደገና ለማቋቋም ጊዜ የሚወስድና አስቸጋሪ ሊሆን ስለሚችል የክልሉ ሕዝብ ለረጅም ጊዜ ምንም ዐይነት አስተዳደራዊ አገልግሎት ሊያገኝ የማይችልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል።
- የዚህ ዐይነት የማያቋርጥ ግጭት ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ብዙ ችግሮችን ስቦ የሚመጣ (ኢንቬስትመንት ይቀንሳል፤ ቱሪዝም ይቀንሳል፤ በዚህም የሥራ አጥ ቁጥር ይጨምራል፤ በሌላው የአገሪቱ ክፍልም አለመረጋጋትን ያስከትላል።
- ሕወሓት ታጣቂዎችን እና አባላቱን መመገብ ስለማይችሉ ህዝቡን ሊያስጨንቁና ሊዘርፉ ይችላሉ፣
- መንግሥት የወሰደውን ክልሉን ለቆ የመውጣት እርምጃ የሚቃወሙና ተመልሶ እንዲገባ ጫና የሚያደርጉ አገራት ሊኖሩ ይችላሉ፣
ይህ ቢሆንስ የመኾን እድሉ የተሻለ ይሁን እንጂ በክልሉና ባጠቃላይ በአገሪቱ ከብሄር ፖለቲካ ጋር ተያይዞ የመጣውን አደጋ በዘላቂነት የማይፈታ፤ አገሪቱን ቀስ እያለ ውስጧን እንደሚበላ በሽታ ከመግደሉ በፊት መፍትሔ የሚፈልግ ስለሆነ ለአገሪቱ የተሻለ መፍትሔ በፍጹም ሊሆን አይችልም። የተረጋጋ (stable) ሁኔታ ስላልሆነ የግዜ ጉዳይ ነው እንጂ ወደ ከፍተኛ ግጭት ማምራቱ አይቀርም። ከዚህ የቢሆን ግምት በመነሳት የመፍትሔ ሃሳብ ይሆናሉ ያልናቸው ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው፡-
• በብዝሃነት ዙሪያ የሚነሱም ሆኑ ሌሎች ችግሮችን ለማስተናገድና ተረጋግቶ ወደፊት ለመጓዝ በመጀመሪያ አገር በጠንካራ መሰረት ላይ መቆም እንዳለባት ሁሉም ባለድርሻ አካላት አምነው የሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች በሙሉ ይህን ከግንዛቤ ያስገባ መኾን ይገባዋል።
• በአንድ አካባቢ ሕዝብ ኪሳራ አገርም ሆነ ሌላው ሕዝብ ተጠቃሚ በመኾን የሚገኝ ሰላምና ጥቅም እንደሌለ ይህ ሁኔታ አገሪቷን ወደ የማያልቅ ግጭትና ውድመት እንደሚመራ ኢዜማ በጥብቅ ማስገንዘብ ይሻል፡፡
• ሕወሓት ትግራይ የራሷን መንግሥት ማቋቋም አለባት በማለት ሊያነሳ የሚፈልገው ሀሳብ የትግራይን ሕዝብ ፍላጎትና ጥቅም እንደማያስጠብቅ ኢዜማ ያሳስባል።
• በዜግነት ላይ የተመሰረት ዴሞክራሲያዊ ፊዴራሊዝም አገርን ማስቀጠልም ሆነ የብዝሃነትን ጥያቄ በአግባቡ ሊያስተናግድ የሚችል አገራዊ የፖለቲካ ሥርዓት መኾኑ ኢዜማ ያስገነዝባል።
• ለሁሉም ችግሮች መፍትሔ የሚሆነው፣ ሁሉንም ዜጎች በእኩልነት የሚያስተናግድ፤ ተጠያቂነት ያለበት እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት የመመስረቱ ጥረት ላይ ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት ብርቱ ርብርብ ሲያደርጉ ብቻ ነው።
3. ሦስተኛውና እጅግ የከፋው የቢሆንስ ግምት ሕወሓት ክልሉን፣ አገሪቱንና ቀጠናውን ለማተራመስ ከሌሎች አክራሪ ሃይሎች ጋር ጥምረት የሚፈጥርበት ሁኔታና አልፎም ለአገሪቱ የውጭ ጠላቶች መሳሪያ በመኾን በአገሪቱም ሆነ ባካባቢው ፍጹም አደገኛ የሆነ ሁኔታ ሊፈጠር የሚችልበት ሁኔታ ነው፡፡
ኢዜማ የአገርን ህልውና እና ቀጣይነት ችግር ውስጥ የጨመረው በትግራይና በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች በየጊዜው የሚከሰተው ግጭት ዋነኛው መንስኤ፣ ማንነትን መሰረት ያደረገ የፍትሕና የእኩልነት ጥያቄ በሒደት ወደ ዘር የጥላቻና የግጭት ፖለቲካ በመቀየሩ መኾኑን ያምናል፡፡ ምንም እንኳን ለ30 ዓመታት ሲሰበክ የከረመ፤ በዚህ እንጠቀማለን ብሎ የሚያምን የዘር ልሂቅ በተፈጠረበት አገር እንዲህ ዐይነት አመለካከት ባጭር ጊዜና በቀላሉ ይጠፋል ማለት ባይቻልም፤ የአደጋውን እምቅ አስከፊነት በመመልከት ድርጅታችን ከዚህ አደጋ ኅብረተሰቡን እንዲጠነቀቅ ሲያሳስብ ቆይቷል።
ይህ ሁኔታ ከሕወሓት የፀብ አጫሪነት ባሕሪ የተነሳ፣ አሁን ክልሉ፣ አገሪቱና ቀጠናው ካሉበት ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ሲታይ እና ከዚህም በተጨማሪ የውጭ አገራት፣ የአገራት ማኅበራት ሁኔታውን ባላገናዘበ መልኩ እያደረጉ ያሉት ጣልቃ ገብነት ሲታከልበት የመፈጠር እድሉ አነስተኛ እንኳን ቢሆን፤ «የተሻለውን ተስፋ አድርግ ግን ለመጥፎው ተዘጋጅ» እንደሚባለው አባባል የኢትዮጵያ መንግሥት፤ የኢትዮጵያ ሕዝብም ሆነ በፖለቲካ ጉዳይ ከመንግሥት ጋር ልዩነት ያላቸው ግን የአገሪቱን ሰላምና አንድነት የሚፈልጉ ኃይሎች ሁሉ በመተባበርና ያለ የሌለ አቅማቸውን በማሰባሰብ ችግሩ ከመፈጠሩ በፊት ሊቀጩት የሚገባ ፍጹም አደገኛ ቢሆንስ ነው። የዚህን አደጋ ተጨባጭ አመላካች አንኳር ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው።
- በአገሪቷ ሌሎች ክልሎች የሚገኙ አክራሪ ብሄርተኞች የሕወሓት ተመልሶ ክልሉን መቆጣጠር እነሱም ለማሳካት ለሚፈልጉት አክራሪ ብሄረተኛ አጀንዳ የመንፈስ ጥንካሬ ስንቅ በመኾን የአመጽ ትግላቸውን አጠንክረው እንዲቀጥሉ ሊያበረታታ ይችላል፣ ይህ ምልክት በማኅበራዊ ሚዲያው አሁንም እየተንጸባረቀ ነው፤
- ሕወሓት ተወሰዱብኝ የሚላቸውን የወልቃይትና የራያ አካባቢ በኃይል ለማስመለስ ሊሞክር ይችላል። ይህ ግምት ሳይሆን መቀሌ ከተለቀቀ ጀምሮ ሕወሃቶች ቀጣይ ሥራቸው እንደሆነ እየተናገሩ ነው። ይህ ሁኔታ ከደህንነት አስከባሪ ተቋማት አልፎ ሕዝብ ለሕዝብ የሚጋጭበትና ከፍተኛ ጉዳት ሊደርስ የሚችልበትን ሁኔታ ሊያስከትል ይችላል፣
- በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች በአመጽ ለሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ሕወሓት እገዛ በማድረግ የአመጽን ደረጃ ሊያሳድገው፤ አገራችንን ባጠቃላይ ለማተራመስ ሊጠቀምበት ይችላል፣ (ይህንን ባለፉት 3 ዓመታትም ያየነው ነው)
- ውጭ አገር የሚገኙ የሕወሓት ደጋፊዎችን በመጠቀም፣ እንደተለመደው የተዛባ መረጃ በማቅረብ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ላይ የሚያደርጉትን ጫና አጠናክረው ሊቀጥሉ ይችላሉ፣
- ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች በእርዳታ ስም ሁኔታውን የሚያባብስ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ፣
- የኤርትራ መንግሥት በራሱ ምክንያትም ሆነ ከህወሃት በሚደርስበት ትንኮሳ ከትግራይ ታጣቂዎች ጋር ግጭት ውስጥ ሊገባ ይችላል፣
በዚህ እጅግ ፈታኝ በሆነ ወቅት ላይ በአገራችን ላይ የተደቀነውን አደጋ ለማለፍ ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት የሚያስፈልጋቸውን ትዕግስት፣ ጥበብ፣ አርቆ አሳቢነትና ቁርጠኝነት ከግምት ማስገባት ያስፈልጋል፡፡ በዚሁ መሠረት ኢዜማ የሚከተሉት ባለ ድርሻ አካላት መወጣት የሚገባቸውን ኃላፊነት እና ሚና ማስገንዘብ ይሻል፡፡
1. የመንግሥት ኃላፊነት
1.1 መንግሥት አገርን በመምራት ሒደት ውስጥ በየቦታው የሚዝረከረኩ አሠራሮችን መስመር በማስያዝ ጥበብ በተሞላበት መልኩ አገርን ማስተዳደር ይጠበቅበታል፡፡ ከዚህ አንጻር ሁሉንም ባለ ድርሻ አካላትን ያካተተ ፖለቲካዊ መፍትሔ በሚያስፈልጋቸው አጀንዳዎች ላይ ለአገራዊ ውይይት በሩን ክፍት ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ለዚህም እንዲረዳ ከሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ጋር የሚታዩትን ልዩነቶች በማጥበብ በመቀራረብና በመመካር አገር የመምራት ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ በጥብቅ ማሳሰብ እንወዳለን፡፡
1.2 ከሁሉ በፊት አገር እየመራ ያለው መንግሥት ቅድሚያ መስጠት የሚገባው ለአገር ሕልውና እና ለዜጎች ደህንነት መኾኑን በሚገባ ማጤን ይኖርበታል፡፡
1.3 መንግሥት ለዜጎች መግለጽ የሚገባውን ወቅታዊና አገራዊ ሁኔታዎች በየጊዜው እየተከታተለ በግልጽነት ማሳወቅ ይገባዎል።
1.4 መንግሥት አገራዊ ጉዳዮችን በሚገልጽበት ጊዜ አገርን የመምራት ኃላፊነት እንዳለበት አካል የሚመጥን ቋንቋ መጠቀም አለበት፣
2. የፖለቲካ ፓርቲዎች ኃላፊነት
2.1 የገዢውን ፓርቲ ጨምሮ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖለቲካ ፉክክር ሊኖር የሚችለው የአገር ህልውና ሲረጋገጥ አና የሕዝብ ደህንነት ሲጠበቅ በመኾኑ ለዚህ አላማ ሁሉም በጋራ እና በመቀራረብ መንቀሳቀስ ይጠበቅብናል፡፡
2.2 በትግራይ የተፈጠረው ችግር የሁላችንም አገራዊ ችግር በመኾኑ ችግሩን በጋራ ከመወጣት ውጭ የዘር ማንነትን መሰረት ያደረገ የችግሩ አፈታት ችግሩን ከማማባስ በቀር መፍትሔ ሊሆኑ እንዳማይችሉ መገንዘብ ይኖብናል፣
3. ሕዝብ ኃላፊነት
አገራችንን አሁን የገጠማት ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ እና በብርቱ የሚፈትነን በመኾኑ ለከፋ አደጋ ተላልፈን እንዳንሰጥ በጥንቃቄ የምንራመድበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ በዚህ ወቅት የአገሪቱ ባለቤት እና የችግሩ ገፈት ቀማሽ ሕዝቡ በመኾኑ፡-
3.1 መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በያለበት መሠረቱን ዜግነት ባደረገ መልኩ ተደራጅቶ ራሱን፣ ቤተሰቡን፣ አካባቢውንና አገርን ከተለያዩ ጥቃቶች መጠበቅ ግድ ይለዋል፡፡
3.2 አገርን ከመበታተን ለመታደግ ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የሚያደርገውን ብሔራዊ ጥሪ ተቀብሎ በመከላከያ፣ በፖሊስ እና በሌሎች የፀጥታ ተቋማት በመሳተፍ የዜግነት ድርሻውን ሊወጣ ይገባዋል፡፡
3.3 ከምን ጊዜውም በላይ ይህንን እጅግ ፈታኝ ወቅት በጥበብ ለማለፍ መላው የአገራችን ሕዝብ ጥቃቅን ልዩነቶችን አስወግዶ ከቀድሞ በበለጠ ተሳስቦ እና ተከባብሮ በአንድ እንዲቆም አገራዊ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
በመጨረሻም በየደረጃው የምትገኙ የኢዜማ አባላትና ደጋፊዎች በዚህ እጅግ ፈታኝ በሆነ ወቅት ከፓርቲያችን የሚጠበቀው የተለየ ኃላፊነት ከምንጊዜውም ይልቅ የገዘፈ መኾኑን ልብ ልንል ይገባል፡፡
ከዚሀ አንጻር ኢዜማ የአገር አና የሕዝብን ሰላምና ደህንነት ባስቀደመ መልኩ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተጨማሪ ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ መኾኑን እና አገርንና ሕዝብን ከሚያስቀድሙ ማናቸውም አካላት ጋር ተባብሮ ለመሥራት የአንበሳውን ድርሻ ለመውሰድ ቃል የምንገባበት ይሆናል፡፡
ሰኔ 26 ቀን 2013 ዓ.ም
አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ