የአሜሪካ የጉዞ ማስጠንቀቂያ

የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት
በትግራይ ያለው ደኅንነት ስላሠጋት ዜጎቼን አወጣለሁ አለች
ኢዛ (እሁድ ሰኔ ፳፯ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. July 4, 2021)፦ አሜሪካ በትግራይ ክልል ካለው ችግር አንጻር ሥጋት ያደረባት መኾኑን በመግለጽ፤ በክልሉ ያሉ ዜጎችዋን ለማስወጣት እየተንቀሳቀሰች መኾኑን አስታወቀች።
የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት እንዳስታወቀው፤ በክልሉ ካለው ደኅንነት ሥጋት ያለባት መኾኑን በመጥቀስ፤ ለዜጎችዋ የጉዞ ማስጠንቀቂያ ሰጥታለች።
የዜጎቿን ደኅንነት ለመጠበቅ ከትግራይ በማስወጣት ደኅንነቱ ወደ ተጠበቀ አካባቢ ለማዛወር እየሠራች ስለመኾኑ የሚጠቅሰው ይህ ማስጠንቀቂያ፤ ደኅንነቱ የተጠበቀ መንገድ ካለ በዚሁ መንገድ ለማስወጣት መታቀዱን ያመለክታል።
ይህ የዲፓርትመንቱ መረጃ በመቀሌ የሚገኙ የአሜሪካ ዜጎች የሳተላይ ስልክ ተጠቅመው አዲስ አበባ ለሚገኘው ኤምባሲ ሪፖርት እንዲያደርጉና ከመቀሌ መውጣት የሚፈልጉ አሜሪካኖችም እዚያ የሚገኙትን የተባበሩት መንግሥታት ወኪሎች ያነጋግሩም ተብሏል። (ኢዛ)