Harmony Hotel, Addis Ababa

ሐርመኒ ሆቴል፣ አዲስ አበባ

ለሁለት ቀን ተዘግተው የነበሩ ሆቴሎችና የምሽት ክለቦች ወደ ሥራ ተመልሰዋል

ኢዛ (ማክሰኞ ሐምሌ ፮ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. July 13, 2021)፦ በሽብርተኝነት የተፈረጀው የሕወሓት ቡድን በመደገፍ በአዲስ አበባ በተለያዩ እንቅስቃሴዎች ሲያደርጉ ነበሩ የተባሉ የትግራይ ክልል ተወላጆች በጸጥታ አካላት ተይዘው እየታሰሩ መኾኑ እየተገለጸ ነው። በአንዳንድ አካባቢዎች ለሁለት ቀን ተዘግተው የነበሩ ሆቴሎችና የምሽት ክለቦች ወደ ሥራ ተመልሰዋል።

በተለይ የኢትዮጵያ መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም በማድረግ ከትግራይ መከላከያ ሠራዊቱ መውጣቱ ከተገለጸበት ምሽት ጀምሮ፤ በአዲስ አበባ ያሉ የቡድኑ ደጋፊዎች በተለያዩ ምሽት ክበቦች የደስታ ጭፈራ በማድረግና የኢትዮጵያን ባንዲራ በመርገጥና በማቃጠል የፈጸሙት ድርጊት ደጋፊዎቹን በቁጥጥር ሥር ለማዋል እንደ አንድ ምክንያት እየተጠቀሰ ነው። መረጃዎች እንደሚጠቁሙትም የሕወሓትን ቡድን በመደገፍ በተለያዩ ጭፈራ ቤቶች ጭምር በሽብርተኝነት የተፈረጀውን ቡድን በመደገፍ ሲያደርጉ ከነበረው ድርጊት ባሻገር በሌሎች ተያያዥ እንቅስቃሴዎች ተሰማርተዋል የተባሉ እነዚህ ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል አስገድዷል።

ሰሞኑን ከባለሀብቶች ጋር ስብሰባ ተቀምጠው የነበሩት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እንደገለጹትም፤ እነዚህ ግለሰቦች መኻል አዲስ አበባ ላይ የፈጸሙት ድርጊት ብዙዎችን ያስቆጣ መኾኑን ነው።

እንደ ከንቲባዋ ገለጻ፤ በሽብር የተፈረጀውን የሕወሓት ቡድን በመደገፍ ሲጨፍሩ እንደነበር አረጋግጠዋል።

የአገር መከላከያ ሠራዊትን ያጠቃ እና ሽብርተኛ ተብሎ የተፈረጀ ቡድንን በመደገፍ አዲስ አበባ ላይ መጨፈራቸው ሳያንስ፤ ድርጊታቸው የኢትዮጵያን ባንዲራ እስከ መረጋገጥ የደረሰ መኾኑንም ከንቲባዋ መግለጻቸው ታውቋል።

አሁንም እንዲህ ባለው ተግባር የተጠረጠሩ ግለሰቦች እየተያዙ ስለመኾኑ እየተነገረ ሲሆን፣ ምሽት ላይ ሽብርተኛውን ቡድን የሚያንቆለጳጵሱ ዜማዎችን በመክፈት ጭምር ጭፈራ ሲካሔድባቸው የነበሩ የምሽት ቤቶችም ታሽገዋል ተብሏል።

በብዙዎች ዘንድ ተቃውሞ ያስነሳውን የሕወሓት ቡድንን በመደገፍ ጭፈራ ሲደረግባቸውና ሲፎከርባቸው ነበሩ ከተባሉት ውስጥ ሐርመኒ እና ካሌብ ሆቴሎች በተመሳሳይ መንገድ መታሸጋቸው ታውቋል። በእነዚህ ሆቴሎች ሲደረግ የነበረው ድርጊት ፀብ የሚያስነሳ ጭምር በመኾኑ በአካባቢው ሕብረተሰብ ጥቆማ እንዲታሸግ ተደርጓል። አንድን በሽብርተኝነት የተፈረጀ ቡድን መደገፍ በሕግ የሚያስጠይቅ ኾኖ ሳለ፤ ከሰሞኑ እንደተሰማው ለቡድኑ ድጋፍ ያላቸው ግለሰቦች እንዲህ በማድረጋቸው በጸጥታ ኃይል የተወሰደው እርምጃ ንጹኀንን እንዳይነካ በጥንቃቄ መካሔድ ይኖርበታል ከሚለው አስተያየት ውጪ፤ የድርጊቱ ተሳታፊዎች በሕግ ሊጠየቁ ይገባል ተብሏል።

ከሰሞኑ እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ በአዲስ አበባ ከተማ ከትግራይ ተወጆች ጋር በተደረገ የውይይት መድረኮች ላይ እንደተንጸባረቀውም፤ በሕገወጥ ድርጊት የተሰማሩ እንዲጠየቁ ንጹኀንን በመለየት ባልሠሩት ተግባር እንዳይጠየቁ ማድረግ ይገባል የሚል አስተያየት ተሰንዝሯል።

በአንዳንድ አካባቢዎች ከዚሁ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ተዘግተው የነበሩ ሆቴሎችና የምሽት ከለቦች ተመልሰው ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርገዋል። በጀሞ አካባቢ ለሁለት ቀን ተዘግተው የነበሩና አሁን ወደ ሥራ ከተመለሱት ውስጥ ጽዮን ሆቴል፣ ቤናዞ ሆቴል፣ ግራንድ ኮርነር ጭፈራ ቤት፣ ቤላ ሆቴል እና ሚኪ ሆቴል ይገኙበታል።

ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ ከትግራይ ተወላጆች ጋር በተደረገ በአንድ የውይይት መድረክ ላይ መድረኩን ሲመሩ የነበሩ የክልሉ ተወላጆች የሕወሓትን ቡድን እንቅስቃሴ ከመደገፍ እንዲቆጠቡ አሳስቧቸዋል።

ሰሞኑን ሽብርተኛውን ቡድን በመደገፍ ሲጨፍሩ ነበሩ የተባሉ ግለሰቦችና በተያያዥ እንቅስቃሴ ላይ የነበሩ ግለሰቦች በጥቆማ ቤታቸው ሲፈተሽ የጦር መሣሪያ ጭምር የተገኘባቸው እንደነበሩ አመልክተዋል።

ቡድኑ ሽብር እንዲፈጥሩ አንድ ሺህ ወጣቶች አሰማርቶ እንደኾነም ገልጸዋል። ስለዚህ የክልሉ ተወላጅ ሕወሓት ይመጣል ብለው የሚያስቡ ከኾነ ይህንን ሐሳባቸውን እንዲተዉና በሰላማዊ መንገድ እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ መብታቸውን አስከብረው መኖር የሚችሉ መኾኑን ገልጸውላቸዋል።

ኾኖም በሕገወጥ መንገድ የተፈረጀ ቡድንን መደገፍ በሕግ የሚያስጠይቅ እንደሚኾን በመጥቀስ ማብራሪያ ሰጥተዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!