ጋዜጠኛ አማረ ራሱን ከሳተበት ነቃ
የመግደል ሙከራውን የፈፀሙት ቅጥር ነፍሰገዳዮች እንደሆኑ ይጠረጠራል
Ethiopia Zare (ቅዳሜ ጥቅምት 22 ቀን 2001 ዓ.ም. November 1, 2008)፦ በትናንትናው ዕለት በሀገር ውስጥ የሚታተመው የአማርኛው ”ሪፖርተር” እና የእግሊዝኛው ”The Reporter” ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ፣ ባለቤትና አሣታሚ ጋዜጠኛ አማረ አረጋዊ ላይ የመግድል ሙከራ ያደረጉበት ሦስት ግለሰቦች ቅጥር ነፍሰ ገዳዮች እንደሆኑ ተጠርጥራል። እስከዛሬ ማምሻውን ከፍተኛ ጥበቃ እየተደረገለት በሕክምና ላይ እንደሚገኝና ራሱን ስቶ ከነበረበት መንቃቱን የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገለጡ።
የኢትዮጵያ ዛሬ ታማኝ ምንጮች እንደገለፁት ከሆነ የሕክምና ባለሙያዎቹ በምርመራ እንዳረጋገጡት ከሆነ የመግደል ሙከራውን ያደረጉት ሰዎች የግድያ ሙከራቸውን ያደረጉት በድንጋይ ወይንም በስለት መሣሪያ ሳይሆን በጠንካራ ብረት መሳይ ሲሆን፣ ፌሮ ብረት እንደሆነ ታውቋል።
ትናንት በግድያ ሙከራው ወቅት ከተያዙት ሁለቱ ግለሰቦች በተጨማሪ ሌሎች ተጠርጣሪዎችን ፖሊስ መያዙን ለማረጋገጥ ችለናል። ትናንት በፌሮ ብረት ከኋላው ጭንቅላቱ ላይ የመታውና ያመለጠው ግለሰብ በቅጥር ነፍሰ ገዳይነት የተጠረጠረ ሲሆን፣ የተያዙት ሁለቱ ግለሰቦች (ግብረአበር እና የታክሲ ሹፌሩ) በቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው ያደሩ ሲሆን፣ ዛሬ ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ጣቢያ መዛወራቸውን የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገልጠዋል።
ጋዜጠኛ አማረ ትናንት የመግደል ሙከራ ተደርጎበት ራሱን ስቶ ሐያት ሆስፒታል ገብቶ የሕክምና ዕርዳታ ከተሰጠው በኋላ ሪከቨሪ ከፍል ገብቶ የነበረ ሲሆን፣ ዛሬ ከሰዓት ረፋዱ ላይ መንቃቱንና ራሱን ማወቁን ለመረዳት ችለናል። ለጋዜጠኛ አማረ ሕይወት ስጋት ስለነበር ልዩ ጥበቃ እየተደረገለት ሲሆን፣ ዛሬ ራሱን ካወቀ በኋላ ቤተሰቦቹ ብቻ እንዲጠይቁት ተፈቅዶላቸዋል። ሌሎች ወገኖች ግን እንዳይገቡ ተደርጓል።
ጋዜጠኛ አማረ የዛሬ 13 ዓመት ሪፖርተር ጋዜጣን ማሳተም መጀመሩ ይታወቃል። በቅርቡ ሪፖርተር ጋዜጣ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና ሜድሮክ ላይ ጠንካራ ትችት ሲሰነዝር እንደነበር አይዘነጋም። በተለይም የሼህ መሐመድ አል አሙዲን ንብረት የሆነውን ሜድሮክ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውንና ስር የሰደደውን ችግር አስመልክቶ በርዕሰ አንቀጽ ጭምር የሰላ ሂስ ቀርቦ እንደነበር አይዘነጋም። በሜድሮክ ውስጥ ያሉትን ”ባለሥልጣናት” ጋዜጣው ”ትናንሽ መንግሥታት” ብሏቸዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ቅዳሜ የሚታተመውና የአቶ ሣምሶን ማሞ ጋዜጣ በሆነው ”ኢትዮ ቻናል” ላይ በተለይም ላለፉት ሦስት ተከታታይ ሣምንታት ሰፋ ያሉ ስድብ የተቀላቀለባቸው ትችቶች በጋዜጠኛ አማረ ላይ ሲሰነዘር ቆይቷል። ባለፈው ቅዳሜ ጋዜጣው ዛሬ ቀጣይ ጽሑፍ እንደሚያቀርብ ቃል ገብቶ የነበረ ቢሆንም በዛሬው ዕለት ዕትሙ ጽሑፉን ሳያወጣ ቀርቷል። አቶ ሣምሶን ጋዜጣውን የጀመሩት ከአቶ አብነት ገብረመስቀል ባገኙት የገንዘብ ድጋፍ እንደሆነ ይነገራል። አቶ አብነት ደግሞ በኢትዮጵያ የሼህ መሐመድ አል አሙዲን ቀኝ እጅ እንደሆኑ ይታወቃል።
ጋዜጠኛ አማረ የመግደል ሙከራው የተደረገበት ትናንት ዓርብ ጥቅምት 21 ቀን 2001 ዓ.ም. ወደ 10 ሰዓት አካባቢ ቦሌ ክፍለ ከተማ ከዲ.ኤች.ገዳ. ሕንፃ ጎን ከሚገኘው አንድነት ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት ከተሰኘውና ከልጁ ት/ቤት ወጥቶ ወደ መኪናው በመሄድ ላይ እንደነበር ነው። በፌሮ ብረት የመታው ሰው ያመለጠ ሲሆን፣ ባለታክሲውና አንድ ግብረ አበሩ ወዲያው በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለዋል።
ጋዜጠኛ አማረ ባለትዳርና የሦስት ልጆች አባት ነው። ቀደም ብሎ የወለዳት ዕድሜዋ ወደ 20 የምትጥጋ ሴት ልጅ እና አብሯት ከሚኖረው ባለቤቱ የወለዳቸው አንድ ወንድ እና አንድ ሴት ልጅ አሉት።



