የሪፖርተር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ከስድስት ቀን በኋላ በዋስ ተለቀቀ
ሰኞ ጎንደር ፍ/ቤት ይቀርባል
Ethiopia Zare (ዓርብ ነኀሴ 23 ቀን 2000 ዓ.ም. August 29, 2008)፦ ባለፈው ሣምንት ዓርብ ነኀሴ 16 ከቢሮው በፖሊሶች ከአዲስ አበባ የሪፖርተር ጋዜጣ ቢሮ ወደ ጎንደር የተወሰደው ጋዜጣው ባለቤትና ዋና አዘጋጅ አማረ አረጋዊ ረቡዕ ነኀሴ 21 ቀን 2000 ዓ.ም. ምሽት ላይ በስድስተኛ ቀኑ ከእስር በዋስ ተለቅቋል።
ጋዜጠኛ አማረን ከቢሮው አስገድደው የወሰዱት የጎንደር ፖሊሶች ሲሆኑ፣ ማክሰኞ ነኀሴ 20 ቀን ጎንደር ውስጥ በሚገኝ የወረዳ ፍርድ ቤት ቀርቦ የዋስትና መብት ተከልክሎ ነበር።
ረቡዕ ነኀሴ 21 ቀን ጋዜጠኛ አማረ የዋስ መብቱ እንዲከበርለት ማመልከቻ አስገብቶ የነበረ ሲሆን፣ እዚያው ጎንደር ውስጥ በሚገኘው የወረዳው ፍርድ ቤት በሦስተኛ ዳኛ በተሰጠ ትዕዛዝ በሦስት መቶ ብር ዋስ እንዲለቀቅ ተወስኗል። ትዕዛዙን የሰጡት ዳኛ አለበል አየነው ሲሆኑ፣ ረቡዕ አመሻሹ ላይ ጋዜጠኛ አማረ ከእስር ተለቅቋል።
ምንም እንኳን ጋዜጠኛ አማረ በዋስ ቢለቀቅም የፊታችን ሰኞ ነኀሴ 26 ቀን 2000 ዓ.ም. (September 01, 2008) ጎንደር ውስጥ በሚገኘው የወረዳው ፍርድ ቤት በዚሁ በተከሰሰበት የዳሽን ቢራ ጉዳይ የሚቀርብ መሆኑ ታውቋል።
የጋዜጠኛ አማረን መታሰር አስመልክቶ የተለያዩ ዓለም አቀፍ የፕሬስ ነፃነት መብት ተሟጋች የሆኑ ተቋማት ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ቡድን (ሪፖርተርስ ዊዝአውት ቦርደርስ/ሪፖርተርስ ሳንፍሮንቴርስ) እና ዓለም አቀፉ የፕሬስ ኢንስቲትዩት ያላቸውን ተቃውሞ ለኢትዮጵያ መንግሥት በደብዳቤ አሳውቀው ነበር።
ጋዜጠኛ አማረ ለእስሩ ምክንያት የሆነው በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ የዳሽን ቢራ ፋብሪካ አመራር አካላት የሠራተኛ ማኅበራትን ማፍረሳቸውንና የማኅበሩ ሊቀመንበርና ም/ሊቀመንበር ከሥራ ማገዳቸውን የሚመለከት ዘገባ በማውጣቱ ነው።
የሪፖርተር ዋና አዘጋጅ አማረ አረጋዊ ተከስሶበታል ተብሎ የሚገመተውንና የጋዜጣው ሪፖርተር ተሾመ ንቁም ከዚህ በፊት በፖሊስ ከቢሮው ተገድዶ ተወስዶ ጎንደር የታሰረበት የዳሽን ቢራ ዘገባን ከዚህ በታች የሚገኘው ነው።
ከዳሽን ቢራ ፋብሪካ የተባረሩ ሠራተኞች ቅሬታ አሰሙ
እሁድ ግንቦት 17 ቀን 2000 ዓ.ም. (MAY 25, 2008)
በተሾመ ንቁ
ከዳሽን ቢራ ፋብሪካ የተባረሩ ከሰባ በላይ ሠራተኞች የፋብሪካው አመራር ከመመሪያ ውጪ ከሥራችን እንዳፈናቀላቸው ለሪፖርተር ጋዜጣ ቅሬታቸውን አሰሙ።
በተለያየ ጊዜ ከሥራቸው እንዲፈናቀሉ የተደረጉ የፋብሪካው ሠራተኞች፣ የፋብሪካውን አመራር ወንጅለዋል። በሠራተኛ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ሠራተኛ ካጠፋ የቃል፣ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ሊደርሰው እንደሚገባ በመጥቀስ፤ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ሥራቸውን ማጣታቸውን ገልፀዋል።
በዚህም ቅሬታቸውን ለፋብሪካው የሠራተኛ ማኅበር እንዲሁም ለፋብሪካው ቦርድ ማቅረባቸውንና ምላሽ ማጣታቸውን ገልፀዋል። የፋብሪካው አመራር በሠራተኛው ላይ የሚያደርሰውን ጫና በተመለከተ የማስተካከያ እርምጃ ለመውሰድ አለመቻሉን ተናግረዋል።
የፋብሪካው የሠራተኛ ማኅበር ሊቀመንበር አቶ ደጀኔ ታረቀኝ በበኩላቸው “የፋብሪካው አመራር ሠራተኛን በህገወጥ ሁኔታ እያባረረ ሲሆን የሠራተኛ ማኅበሩንም ለመበተን ጥረት እያደረገ ነው” ሲሉ ሁኔታውን አረጋግጠዋል። በዚህም ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ አስራ ሰባት ሠራተኞች ከመመሪያ ውጪ መባረራቸውን ጠቁመዋል።
አመራሩ በሠራተኛ ማኅበሩ ላይ በጀመረው የማፍረስ ተግባር ምክንያት በያዝነው ወር ውስጥ የማኅበሩን ምክትል ሊቀመንበር አቶ ዳንኤል አለማየሁን ጨምሮ ሌሎች ሦስት የማኅበሩ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት መባረራቸውን አቶ ደጀኔ አስረድተዋል።
ከመባረር የቀሩት የማኅበሩ የሥራ አስፈፃሚ አባላት በሙሉ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ የተሰጣቸው መሆኑን አውስተዋል።
የፋብሪካው አመራር የማኅበሩን የመንቀሳቀሻ ገንዘብ ማገዱን አቶ ደጀኔ ጠቁመው፤ “ማኅበሩ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እየተካሄደ ነው” ብለዋል። በዚህም ሠራተኛው በፋብሪካው ቅጥር ግቢ ውስጥ ስብሰባ ማድረግ መከልከሉን አስታውቀዋል።
ሊቀ መንበሩ የፋብሪካው ሠራተኛ በአመራሩ ኢ-ፍትሃዊ አስተዳደር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመነ መሆኑን አስታውቀዋል። ሠራተኛው ሥራውን እንዲለቅ ጐንደር ያለውን ሠራተኛ ወደ አዲስ አበባ ማዛወር አዲስ አበባ ያለውንም ወደ ጐንደር ማዛወር አሳማኝ ባልሆነ ምክንያት እንደሚካሄድ አቶ ደጀኔ አመልክተዋል።
አቶ ደጀኔ የፋብሪካው አመራር በማኅበሩ ላይ የሚያካሂደውን ጫና እንዲያቆም የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፌዴሬሽን፣ የሠራተኛ ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የክልሉ ኢሰማኮ በደብዳቤ ቢያሳስቡም ተጨባጭ የመፍትሔ እርምጃ አለመከናወኑን ገልፀዋል። አመራሩ በሠራተኛው ላይ የሚያካሂደውን ኢፍትሐዊ እርምጃ በተመለከተ የሠራተኛ ፌዴሬሽኑ “ፀረ-ማኅበር” የሚል ደብዳቤ መፃፉን አስታውቀዋል።
ሊቀመንበሩ የአመራሩን ጫና በተመለከተ ለኤፌድሪ የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም አቤቱታ ለማቅረብ መዘጋጀታቸውን አብራርተዋል።
የሠራተኞችን አቤቱታ እንዲሁም የማኅበሩን ቅሬታ በተመለከተ የፋብሪካው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ብርሃኑ አድማሱን በስልክ ለማናገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።



