የሞባይል ካርድ ከ25 ብር በታች ይቀርባል

Ethiopia Zare (እሁድ ጥቅምት 23 ቀን 2001 ዓ.ም. November 2, 2008)፦ የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን፣ በተያዘው በጀት ዓመት (2001 ዓ.ም.) የተለያዩ አዳዲስ አገልግሎቶችን ለደንበኞቹ ለማቅረብ በዝግጅት ላይ መሆኑን አስታወቀ።

 

የኮርፖሬሽኑ የሥራ ኃላፊዎች ባለፈው ረቡዕ በጽ/ቤታቸው በሰጡት መግለጫ፣ የኮርፓሬሽኑ ደንበኞች በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚያሰሙት ቅሬታን የሚቀርፍና፣ ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀ የቴሌኮም አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ የተለያዩ ፕሮግራሞች፣ በዚህ ዓመት ውስጥ ተጠናቅቀው እንደሚቀርቡ ተናግረዋል።

 

በዘንድሮው ዓመት ለተጠቃሚው ይቀርባሉ ተብለው ከሚጠበቁት አገልግሎቶች መካከል፣ ከዚህ በፊት በ25፣ በ50 እና በ100 ብር ተዘጋጅተው ለሽያጭ የሚቀርቡት የሞባይል ካርዶች፣ የሁሉንም ደንበኞች ፍላጎት በጠበቀ መልኩ ከ25 ብር በታች እና ደንበኛው በፈለገው ዋጋ የሚያገኝበትን ሁኔታ የሚያመቻች ነው።

 

ኮርፖሬሽኑ በአዲስ መልክ የሚያቀርባቸው የሞባይል ካርዶች፣ ለገበያ ዝግጁ የሚሆኑት ከውጪ ተሠርተው በሚመጡ ካርዶች ብቻ ሳይሆን፣ አቅርቦቱን የተቀላጠፈ በማድረግ 15 ሺህ የኢ-ካርድ አገልግሎቶችን ለማቅረብ በሙከራ ላይ ነው።

 

15 ሺህ የኢ-ካርድ አገልግሎቶች የሚሠራጩት፣ ከኮርፓሬሽኑ የአየር ጊዜ ገዝተው ማከፋፈል በሚችሉ የግል ንግድ በተሰማሩ ተቋማት አማካኝነት ሲሆን፣ ከነዚህ ተቋማት ደንበኛው በሚችለው ዋጋ መግዛት እንዲችል የሚያደርግ መሆኑ ተገልጿል።

 

የአየር ጊዜ በመግዛት አገልግሎቱን የሚሰጡ ተቋማት ሥራቸውን የሚያከናውኑት፣ እንደ በፊቱ የሞባይል ካርድ በመሸጥ ሳይሆን፣ ደንበኛው መግዛት በሚፈልገው ዋጋ ልክ የተወሰነ መጠንን አትሞ በወረቀት በመስጠት ነው።

 

አገልግሎቱ ሲጀምር ኮርፖሬሽኑ በውጪ ምንዛሬ የሚያሠራቸው ካርዶችን ወጪ ከመቆጠቡ በላይ፣ ተገልጋዩ በሚፈልገው የዋጋ መጠን ማግኘት የሚችልበት ዕድል የሚፈጥር መሆኑ ታውቋል።

 

ከዚህም በተጨማሪ የስልክ መደወያ ማዕከል (call center) በመገንባት 750 መቀመጫ ያለው ማዕከል ዝግጅት መጠናቀቁን፣ የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አማረ አምሣሉ ገልፀዋል።

 

እንደ አቶ አማረ ገለፃ በአዲስ መልክ ሥራ የሚጀምረው የስልክ መደወያ ማዕከል፣ 16 ሚሊዮን የሚሆኑ ደንበኞች የተቋሙን አገልግሎት ለማግኘት የሚያስችልና በአገልግሎቱ ለመጠቀም የሚፈልጉ ድርጅቶች፣ ማዕከሉን በመከራየት ወይም ሥራውን ለኮርፖሬሽኑ በመስጠት መጠቀም ይቻላል ብለዋል።

 

የስልክ መደወያ ማዕከል ፕሮጀክት የመሣሪያ ተከላ፣ የሙከራ ሥራና የቢዝነስ ሞዴል እየተዘጋጀ በመሆኑ በዘንድሮው ዓመት ማዕከሉ ሥራ እንደሚጀምር ተገልጿል።

 

አነስተኛ ገቢ ለሚያገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጠቃሚ አገልግሎት ሊሰጥ የሚችል የህዝብ ስልክ አቅርቦትን ለማሻሻል፣ ኮርፖሬሽኑ በያዘው ዕቅድ ከዚህ በፊት ይሠራባቸው ከነበሩ ልምዶች በተለየ ሁኔታ፣ በግል አገልግሎት መስጠት ከሚፈልጉ ወገኖች ጋር ስምምነት በመፍጠር፣ የህዝብ ስልክ አገልግሎትን በመደበኛና በገመድ አልባ ስልኮች የሚሰጥበት ሁኔታ ለመፍጠር ነው። በአሁኑ ወቅት በአገልግሎት ላይ የሚገኙት የህዝብ ስልኮች የሚሠሩት ከየአካባቢው መስመር ጋር ተገናኝተው ሲሆን፣ አዲሱ አገልግሎት የሚቀርበው ግን ተርሚናልን መሠረት ባደረገ መንገድ ሳይሆን፣ አገልግሎት ሰጪው በሚመቸው ሁኔታ ማቅረብ እንደሚችል ተጠቁሟል። የዚህ ፕሮጀክት አቅም 60 ሺህ የህዝብ ስልኮችን ማስተናገድ የሚችል ተደርጎ መሠራቱን የጠቆመው ኮርፖሬሽኑ፣ ለመጀመሪያ ሙከራ በሣንቲም የሚደወልባቸው 5 ሺህ ስልኮችን ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባቱ ተገልጿል።

 

በሌላ በኩል እስካሁን ካሰራጨው 2 ሚሊዮን የሞባይል መስመር 6 ሚሊዮን ተጨማሪ ሞባይል መስመር በመልቀቅ አዲስ ደንበኞች የማፍራት ዕቅድ እንዳለው ገልጻል።

 

ሆኖም ለሞባይል ስልክ አገልግሎት የሚተከሉት የኔትወርክ ምሰሶዎች በታሰበላቸው ፕላንና ቦታ ስለማይተከሉ አዲስ ከመጣው ቴክኖሎጂ ጋር የመናበብ ችግር እንደገጠማቸው በዚሁ መግለጫ ላይ ለማወቅ ተችሏል።

 

ኮርፖሬሽኑ የመደበኛ፣ የሞባይልና የኢንተርኔት አገልግሎትን ለማሻሻል በርካታ ፕሮጀክቶችን እያካሄደ መሆኑን ገልፆ፣ በቀጣይ ከታሪፍና ከአገልግሎት ጥራት ጋር የተዛመዱ ማሻሻያዎችን እንደሚያደርግ አስታውቋል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ