በአራቱ የሀገሪቱ ማዕዘናት አንድነት 35 ቢሮዎችን ከፈተ
Ethiopia Zare (ዓርብ ጥቅምት 28 ቀን 2001 ዓ.ም. November 7, 2008)፦ አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ፣ በአራት የተለያዩ የሀገሪቱ ማዕዘናት ለሁለት ሣምንታት ተንቀሳቅሶ 35 ጽ/ቤቶችን መክፈቱንና አባላት ማደራጀቱን አስታወቀ። ከከፈታቸው ቢሮዎች አምስቱ በህዝቡ ግፊት ነው።
የፓርቲው የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የህዝብ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ ም/ሰብሳቢ፣ አቶ እንዳልካቸው ሞላ እንደገለፁት፤ አንድነት ፓርቲ ለአንድ ዓመት ይዞት በነበረው ዕቅድ መሠረት፣ 117 ጽ/ቤቶችን ለመክፈትና አባላቶች ለማደራጀት አስቦ የነበረ መሆኑን ጠቅሰው፣ በሁለት ሣምንታት ውስጥ በአራቱ የሀገሪቱ ማዕዘናት የተሠማሩ ቡድኖች 35 ጽ/ቤቶችን መክፈታቸውን አስታውቀዋል።
ፓርቲው ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፈቃድ ከተሰጠው በኋላ፣ በተለያዩ ክልሎች ጽ/ቤት ለመክፈት በጀመረው እንቅስቃሴ፣ የመጀመሪያውን ጉዞ ያደረጉት የፓርቲው ሊቀመንበር ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳና፣ የፓርቲው ም/ሊቀመንበርና የፋይናንስ ኃላፊ አቶ ተመስገን ዘውዴ እንዲሁም በሌላ ቡድን ም/ሊቀመንበርና የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ ኢንጂንየር ግዛቸው ሽፈራውና አቶ አዕምሮ አወቀ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ባደረጉት ጉዞ በጎንደር፣ ደብረታቦር፣ ደብረማርቆስ፣ ባህርዳር፣ ደሴ፣ ወልዲያ፣ ከሚሴ፣ አጣዬ እና ሌሎች ከተሞች ወደ 15 የሚጠጉ ጽ/ቤቶችን መክፈታቸውን ገልፀዋል።
በሌላ በኩል የፓርቲው ም/ሊቀመንበርና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ዶ/ር ኃይሉ አርኣያ በደቡብና በኦሮሚያ ክልል ባደረጉት እንቅስቃሴ ጽ/ቤቶችን ከፍተው፣ አባላትን አደራጅተው፣ አመራር መርጠው ተልዕኳቸውን ማጠናቀቃቸውን አቶ እንዳልካቸው ገልጸዋል። በምሥራቁ ክፍል የተሠማሩት አቶ ብሩ ቢርመጂ በአርሲና አካባቢው እንዲሁም በጎባ አካባቢ ቢሮ ማደራጀታቸውን ገልፀዋል።
ፓርቲው በአጠቃላይ ለጽ/ቤቱ ሥራ የላካቸው አመራሮች 35 ጽ/ቤቶችን ከፍተውና አደራጅተው አጠናቀው መመለሳቸውን ተናግረዋል።
በጉዞአቸው ወቅት አብዛኞቹ አባላት ባልተጠበቀ ሁኔታ ሰብሳቢ ሳያስፈልጋቸው፣ ራሳቸው ተሰባስበው፣ ተደራጅተው፣ ቢሮ ፈልገውና ተከራይተው መጠበቃቸው ለቀጣይ ሥራዎች አበረታች እንደሆኑ አቶ እንዳልካቸው ጠቁመዋል።
በተለይ አምስቱ ቢሮዎች የተከፈቱት ፓርቲው ከያዘው ዕቅድ ውጪ ህዝቡ በራሱ ተነሳሽነት ባደረገው ጥሪ መሰረት መሆኑን ታናግረዋል።
ከገጠሟቸው ችግሮች መካከልም፣ በአማራ ክልል ደምበጫ ወረዳ ውስጥ እነ ኢንጂንየር ግዛቸው ባደረጉት ጉዞ፣ ሕጋዊ ደብዳቤ ይዘው እያለ እስክናጣራ በሚል ለሦስት ሰዓታት አስረው እንደለቀቋቸው አስረድተዋል።
በሌላ በኩል በመቱ የእነ ዶ/ር ኃይሉ አርኣያ መኪና ባልታወቁ ሰዎች መስታወቱ መሰባበሩን ገልፀው፣ ከዚህ ውጭ የከፋ ችግር እንዳላጋጠማቸውና ቡድኑ ሥራውን በሠላም አጠናቆ መመለሱን አቶ እንዳልካቸው አብራርተዋል።
በተያያዘ የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳና፣ የፓርቲው የጥናትና ምርምር ኮሚቴ ኃላፊ አቶ አክሉ ግርግሬ፣ የፓርቲው የአውሮፓ ድጋፍ ሰጪ ኮሚቴ ባደረገላቸው ጥሪ መሠረት ዛሬ ወደ አውሮፓ ተጉዘዋል።
በአውሮፓ የሚገኙ የድርጅቱ ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች፤ በአውሮፓ ከሚገኙ የፓርቲው ደጋፊዎች ጋር ግንኙነት እንዲያደርጉና ድጋፍ እንዲያሰባስቡ ባቀረቡት ጥሪ መሠረት፣ ጉዞው እንደተደረገና ሥራቸውን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ አጠናቀው ይመለሳሉ ተብሏል።



