ኦዴጎች ምን ነካቸው?
ግርማ ካሳ
አንዳንድ በተለይም በውጭ ያሉ የኦሮሞ ብሔረተኞች፣ የአክራሪውን እና የብዙ ወገኖች ደም በእጁ ያለበትን የኦነግን ባንዲራ እያውለበለቡ፣ የጭቁን ኦሮሞ ወገኖቻችንን ተቃውሞ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም እና እንቅስቃሴውን ሃይጃክ በማድረግ፣ የኦሮሚያ ሪፑብሊክን ለመመስረት ያላቸውን ሕልም ለመተግበር ደፋ ቀና እያሉ ነው።
አራት ለኦሮሞ ማኅበረሰብ ቆመናል የሚሉ ድርጅቶች በሜኔሶታ ያወጡትን አንድ መግለጫ አነበብኩ። አዘንኩ። እነዚህ ደርጅቶች የኦሮሞ ነጻነት ግንባር፤ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (የተባበሩት)፣ የኦሮሚያ ነጻነት ግንባር (Front for Independence of Oromia) እና በነ አቶ ዮሐነስ (ሌንጮ) ለታ የሚመራው የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ግንባር (ኦዴግ/ODF) ናቸው። (መግለጫውን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ!)
የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ግንባር አመራሮች ያለኝን አክብሮት በመግለጽ፤ እነርሱንም በመደገፍ ብዙ ጽፊያለሁ። “የመገንጠል ጥያቄ አይሰራም፣ የኦሮሞ ጥያቄ እንደሌላው ኢትዮጵያዊ የመብትና የዲሞክራሲ ጥያቄ ነው” በሚል ሁሉም ዜጎች እኩል የሆኑባት አንዲት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን በጋራ ለመገንባት ከሌሎች የኢትዮጵያ ኃይሎች ጋር ለመሥራት ፍላጎት እንዳላቸው ብዙ ጊዜ ሲናገሩ ይሰማሉ። አንድ ወቅት እንደውም ዶ/ር በያን አሴቦ፣ አሁን ያለው የፌዴራል አወቃቀር ሳይቀር ጠረጴዛ ላይ ተቀምጦ፣ ውይይቶች ተደርገው፣ ሁሉንም በሚያስማማ መልኩ መዋቀር እንዳለበት ሲናገሩ አስታወሳለሁ። አቶ ሌንጮ ባቲ ደግሞ “ኦዴግ ለኦሮሞዎች ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ኢትዮጵያውያንም መብት ይታገላል። ከሌሎች ኃይሎች ጋር በመነጋገርም ሀገር አቀፍ የሆነ ደርጅት እናቋቁማለን” ብለው ነበር። በብዙዎች ዘንድ፣ ኦዴግ በርግጥም፣ ያሉ ልዩነቶችን በማጥበብ አንጻር ትልቅ ሚና ሊጫወት ይችላል የሚል ትልቅ ግምትና ተስፋ ነበር።
ሆኖም ኦዴግ ወደፊት መሄድ እየፈለገ ወደኋላ መጎተትን የመረጠ ይመስላል። የኦዴግ አመራሮች የኦነግ አመራሮች የነበሩ ጊዜ የነበራቸውን እና “አይሠራም፤ አያዋጣም” ብለው የተዉትን አቋም መልሰው የያዙ ይመስላል።
ኦዴግ ከሌሎች አክራሪዎች ጋር ሆኖ ያወጣው መግለጫ “እኛ፣ ለኦሮሞ ህዝብ ነጻነትና ለኦሮሚያ ነጻነት (መገንጠል) ቆርጠን የተነሳን የአራት ደርጅቶች ተወካዮች (We, the representatives of four organizations which are committed to the liberation of the Oromo people and the independence of Oromia”)“ ብሎ ነው የሚጀመረው። የኦሮምሚያን ነጻነት (መገንጠል) የሚለው ቃል አስምሩበት።
ሌሎቹ አቋማቸው የታወቀ ነው። ከነ ዳዑድ ኢብሳ አይነቶቹ ዘረኞችና ጠባቦች ብዙም የሚጠበቅ ነገር የለም። “ኦሮሞ፣ ኦሮሞ” ይላሉ እንጂ፣ ቅንጣት ያህል የኦሮሞ ማኅብረሰብን የማይወክሉ፣ ፖለቲካቸው የተሸነፈና የከሰረ እንደሆነ የሚታወቅ ነው። ሆኖም ኦዴግ የዚህ መግለጫ ፈራሚና አካል መሆኑ ግን አስደንጋጭና በጣም አሳዛኝ ነው። ምን ነካቸው የሚያስብል ነው። ታጥቦ ጭቃ መሆን ነው።
በኦሮሚያ በተነሳው ሠላማዊና ህዝባዊ ተቃውሞ፣ ህዝቡ የግፍ አገዛዝን በመቃወም ተቃውሞውን አሰምቷል። ፕሮፌሠር ህዝቄል ጋዲሳ እንዳሉት፤ የህዝቡ ጥያቄ የመብት፣ የዴሞክራሲና የልማት ጥያቄ ነው። የኦሮሞዎች ጥያቄና የሌላው ኢትዮጵያዊ ጥያቄ አንድ እንደሆነ ነው በግልጽ በኦሮሞ ሜዲያ ኔትዎርክ እኝህ ምሁር ለማስረዳት የሞከሩት። ሆኖም በዚህ መግለጫ፣ እነ ኦዴግ የኦሮሞዎች ተቃውሞ ለኦሮሚያ መገንጠል መሰረት ይሆናል ሲሉ ያናገራሉ። “We believe that your blood that was shed and the bodily harm you sustained because of EPRDF/TPLF action will become the building blocks for constructing a free and democratic Oromia.“ ይላል መግለጫው። ክቡር እና ታሪካዊ የሆነውን የኦሮሞዎችን ትግል እንዲሁም በኦሮሚያ የተከፈለውን መስዋዕት አሳንሶና አራክሶ፣ በድሃውና የተገፋው የኦሮሞ ወጣት ጀርባ ላይ በመጠንጠልጠል፣ የራሳቸውን አጀንዳ ለማራገብ መሞከራቸው ግን ተገቢ አይደለም።
አቶ ሌንጮ ባቲ፣ በቅርብ እንደተናገሩት፣ በኦሮሚያ ውስጥ አሥራ አንድ ሚሊዮን ኦሮሞ ያልሆነ ህዝብ እንደሚኖር ገልጸዋል። ከኦሮሚያ አንድ ሦስተኛ የሚሆነው ህዝብ የሚኖረው በሸዋ ነው። አዲስ አበባን ጨምሮ በሸዋ 44% የሚሆነው ህዝብ ኦሮምኛ ተናጋሪ አይደለም። በኦሮሚያ ባሉ ትላልቅ ከተሞች አብዛኛው ነዋሪ multi-ethnic ነው። በኦሮሚያ ባሉ አምስት ትላልቅ ከተሞች አዲስ አበባ፣ አዳማ፣ ጂማ፣ ሻሸመኔና ቢሾፍቱ የሚኖረው ህዝብ አብዛኛው የተዋለደ multi-ethnic ነው።
ታዲያ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚክ እምብርት የሆኑት እንደ ምስራቅና ሰሜን ሸዋ ዞን ባሉ ቦታዎች፣ እንዲሁም አዲስ አበባን ጨምሮ፤ በክልሉ ትላልቅ ከተሞች የሚኖረው ህዝብ የማይደግፈውና አጥብቆ የሚቃወመውን፣ የሚጸየፈውን፣ በታሪክ ያልነበረና ትላንት በህወሓትና ኦነግ ተፍጥሮ በህዝቡ ላይ በኃይል የተጫነውን ኦሮሚያ የሚባል አርቴፊሻል ክልል ስለመገንጠል ወይንም ነጻ ስለማውጣት ማውራት ምን ይባላል? እነርሱ ኦሮሚያን እንገንጥል ሲሉ የአዲስ አበባ፣ የአዳማና የሸዋ ህዝብ ከኦሮሚያ እንገነጠላለን እንደሚል ረሱትን? ነው ወይስ ጦርነት ገጥመው ሸዋን በሙሉ አዲስ አበባን ጨምሮ፣ በሞጋሳ ከአራት መቶ ዓመታት በፊት እንዳደረጉት፣ ሙሉ ለሙሉ ኦሮሞና ከአማርኛ የጸዳ ለማድረግ ነው የሚያስቡት? ሸዋ ለብቻ ሆኖ፣ ምዕራብ ያለው እና ምስራቅ ያለው የኦሮሚያ ክፍል እንዴት ነው የሚገናኘው? እንደ አዲስ አበባ፣ አዳማ፣ ቢሾፍቱ፣ ሻሸመኔ የመሳሰሉት ሳይኖሩ ምን ተይዞ ነው ነጻ ሀገር የሚመሰረተው? ምን አለ ከጠባብነት ወጣ ብለው በሜዳ ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ቢረዱ?
የነኦዴግ መግለጫ የኦሮሞ ማኅበረሰብን ጥቅም ያስጠበቃል ብዬ አላምንም። የኦሮሞ ዕጣ ፈንታ ከተቀረው ኢትዮጵያዊ ጋር የተቆራኘ ነው። ኦሮሞው ከሌላው ጋር ተዋልዷል። ተጋብቷል። ገዢዎች ኦሮሞውን ከሌላ ነጥለው ለመምታት እየሞከሩ ነው። ሌላው ኦሮሞውን፣ ኦሮሞው ሌላውን እንዳያምን በማድረግ፣ በከፋፍለህ ግዛ የሥልጣን ዘመናቸውን እያራዘሙ ነው። ይህ የነኦዴግ መግለጫ፣ ህዝብን ከህዝብ የሚያቀራርብ ሳይሆን፤ ህዝብን ከህዝብ የሚያራርቅ ነው። የተሸነፈ አስተሳሰብ ያንጸባረቀ መግለጫ ነው።
ያለ ኢትዮጵያ ኦሮሞ የለም። ያለ ኦሮሞ ኢትዮጵያ የለም። ኦሮሞነት ኢትዮጵያዊነት ነው። የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄና የሌላው ማኅበረሰብ ጥያቄ ተመሳሳይ እንደመሆኑ፣ የመብትና የፍትህ እንደመሆኑ፣ ከጎጥና ከዘውግ በዘለለ መልኩ ለጋራ ጥቅም ሁሉም ዜጎች መሰባሰብ አለባቸው። በዚህ መግለጫ እንዳየነው አይነት ወደ ኋላ የሚጎትት፣ ዘረኛ የኋላቅ ቀር አመለካከቶች ማባበልና መታገሥ የሚያስፈለግ አይመስለኝም።
የኦሮሞ ማኅበረሰብ እንደ ሌላው ኢትዮጵያዊ ወንድሙ በደልና ግፍ እየተፈጸመበት ያለ ማኅበረሰብ ነው። ኦነግ እየተባሉ ኦሮሞዎች እንደሚታሰሩትም፣ ሌሎችም ደሚት፣ ግንቦት ሰባት እየተባሉ እየታሰሩ ነው። በአምቦ፣ በሐረርጌ ደም እንደፈሰሰም፣ በአዲስ አበባ፣ በባህር ዳር፣ በጎንደር፣ በቴፒ ደም ፈሷል። ከአዲስ አበባ አካባቢ የኦሮሞ ገበሬዎች እንደተፈናቀሉትም ከኦሮሚያ “አማራ” ናችሁ ተብለው፣ ከአዲስ አበባ ከጋማቤላ … ለልማት ይፈለጋል ተብለው ሌሎችም በኃይል ተፈናቅለዋል። ሁላችንንም ነው ይህ አሁን ያለው አገዛዝ እያሰቃየ ያለው። በኦሮሞ ማኅበረሰብ ላይ ከሌላው የተለየ ደረሰ የሚባል ጉዳት የለም። ከአንድ ነገር በስተቀር። እርሱም ኦሮምኛ ብቻ በሚለው የቋንቋ ፖሊሲ ምክንያት፣ ብዙ ኦሮሞዎች አማርኛ ማንበብና መጻፍ አለመቻላቸው ነው። ከዚህም የተነሳ የኢኮኖሚክ ማዕከል በሆኑ፣ ብዙ ሥራ በሚገኝባቸው እንደ አዲስ አበባ፣ አዋሳ፣ ድሬዳዋ፣ ባህር ዳር ባሉ ቦታዎች የመሥራት፣ በፌዴራል መንግሥት የመቀጠር ዕድላቸው በጣም የመነመነ ነው። አዳማ እንኳን ቢሄዱ በአዳማ ባሉ የግል መስሪያ ቤቶች የሥራ ቋንቋ አማርኛ ስለሆነ መቀጠር አይችሉም። ውጤቱ ምንድን ነው? እጅግ በጣም ትልቅ የሥራ አጥነት። ኮሌጅ ተመርቀው ሥራ የለም። ለሌላውም ሥራ የለም፤ ግን የኦሮሞዎች በጣም ይብሳል። ይሄም በተለየ ሁኔታ በኦሮሞው ማኅበረሰብ ላይ እየደረሰ ያለ፣ ትልቅ የኢኮኖሚክ በደልና ግፍ ነው።
ኦሮሞው መሻሻል ነው የሚፈልገው። የኦሮሞው ጥያቄ የመብትና የኢኮኖሚ ጥያቄ ነው። ከሌላው እኩል ሆኖ ማንም የደረሰበት ደረጃ መድረስ ነው የሚፈልገው። ለዚህ ደግሞ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ አማራ ማለት ሳይሆን፣ ለሁሉም ዕድሎች እኩል የሚከፈትበት፣ ሁሉም ኃይማኖት፣ ዘር ሳይባል በእኩልነት የሚኖርባት አንዲት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት በጋራ መነሳት ነው። በተናጥል የትም አይደረስም።
ላለፉት አምስት ወራት ብዙ ዋጋ ተከፍሏል። ያ ሁሉ እንቅስቃሴ ታይቶ ለውጥ ካልመጣ መቼ ነው ታዲያ ሊመጣ የሚችለው? በዘውግ ፖለቲካ ረገድ መጫወት ያለብንን ካርዶች በሙሉ አውጥተን ተጫወተናል። ከዚህ በኋላ በእጃችን የቀረ ምንም ነገር የለም። አሁን እጅ ለእጅ ተያይዘን፣ ከዘር አስተሳሰብ እልፍ ብለን፣ በአንድነት ለጋራ ጥቅማችን በጋራ መታገል ነው የሚያስፈልገን።
ይሄንን ጽሁፍ የምታነቡ የኦሮሞ ወገኖቼ፤ ከስሜት በጸዳ መልኩ በሜዳ ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ በማሰብ፤ ለነዚህ ሜኔሶታና አስመራ ለተቀመጡ፣ የህዝቡ የኢኮኖሚ ችግር ለማይሰማቸው፣ ኦሮሞን እንወክላለን ለሚሉና በኦሮሞውና በሌላው መካከል ህወሓት የገነባውን አጥር የበለጠ ለሚያጠናክሩ ደካማ መሪዎች ጆሮ ሳትሰጡ እንድታነቡ በአክብሮት እጠይቃለሁ። የኦሮሞ ደም የሌለበት ኢትዮጵያ የለም። ኢትዮጵያ ማለት ኦሮሞ ነው። ሌላውን ኢትዮጵያዊ እየገፉ፣ ሌላውን ኢትዮጵያዊ እንደ ጠላት እያዩ፣ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ለመለየት መሞከር ፀረ-ኦሮሞነት ነው።