ጠ/ሚ/ር መለስ ሹም ሽር አካሄዱ
አምስት ሚኒስትሮች ከሥልጣን ተነሱ፣ 3ቱ ተቀያየሩ
ማስታወቂያ ሚኒስቴርን አፈረሱት
Ethiopia Zare (ኀሙስ ጥቅምት 20 ቀን 2001 ዓ.ም. October 30, 2008)፦ ጠቅላይ ሚ/ር መለስ ዜናዊ በዛሬው ዕለት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 9 ሚኒስትሮችን የሾሙ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 5ቱን ከሥልጣናቸው ሲያነሷቸው፣ ሦስቱን ደግሞ ቦታ አቀያይረዋቸዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሹም ሽር እና የሥልጣን ቅይይር የቀረበለት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአብላጫ ድምፅ አጽድቆታል። ሹመት የተሰጣቸው ባለሥልጣናትም ቃለ መሃላ መፈፀማቸው ታውቋል።
የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች የማስታወቂያ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ፈርሶ በአዲስ ስምና መልክ እንዲቋቋም እንዲደረግ የተወሰነ ሲሆን፣ ሣይንስና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ ወደ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት እንዲያድግ መደረጉን ገልጸዋል። መጠሪያውም ”ሣይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር” ሆኗል።
በዛሬው የጠ/ሚኒስትሩ ሹመት መሠረት፤
1. አቶ ሲራጅ ፈጌሳ የመከላከያ ሚኒስትር፣
2. አቶ ጁነዲን ሳዶ የሣይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር፣
3. አቶ ብርሃን ኃይሉ የፍትህ ሚኒስትር፣
4. አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር፣
5. ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር፣
6. አቶ ደመቀ መኮንን የትምህርት ሚኒስትር፣
7. አቶ ድሪባ ኩማ የትራንስፖርትና መገናኛ ሚኒስትር፣
8. አቶ ተፈራ ደርበው የግብራናና ገጠር ልማት ሚኒስትር እንዲሁም
9. ወ/ሮ ሚፈሪያት ካሚል የሴቶች ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል።
ባለፈው ዓመት ግንቦት 12 ቀን 2000 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ከንቲባ ተደርገው የተሾሙት አቶ ኩማ ደመቅሳ ከመከላከያ ሚኒስቴር ሚኒስትርነት ተነስተው እንደነበር አይዘነጋም። ከአምስት ወራት ከሃያ አምስት ቀናት በኋላ አቶ ሲራጅ ፈጌሣን የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል። አቶ ሲራጅ ፈጌሣ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር ነበሩ።
አቶ ሲራጅ ፈጌሣን ተክተው የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም ሲሆኑ፣ ዶ/ር ሽፈራው የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዲኤታ ሆነው ሲያገለግሉ ነበር። በዶ/ር ሽፈራው ቦታ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዲኤታ ተደርጎ የተሾመ ባለመኖሩ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዲኤታ ሥልጣን ክፍት ቦታ እንደሆነ ታውቋል።
የፍትህ ሚኒስትር በነበሩት በአቶ አሰፋ ከሲቶ ምትክ አቶ ብርሃኑ ኃይሉ የተሾሙ ሲሆን፣ አቶ ብርሃኑ የማስታወቂያ ሚኒስትር ነበሩ። አቶ አሰፋ ከሲቶ ከሥልጣናቸው የተነሱ ሲሆን፣ እስካሁን የት እንደተመደቡ አልታወቀም።
የትራንስፖርትና መገናኛ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ጁነዲን ሳዶ ከሥልጣናቸው ተነስተው የሣይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል። የሣይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ከዚህ ቀደም ያልነበረና አዲስ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ነው።
በአቶ ጁነዲን ሳዶ ምትክ፣ አቶ ድሪባ ኩማ የትራንስፖርትና መገናኛ ሚኒስትር ሆነው መሾማቸው ታውቋል።
በዚህ ሹም ሽር ከሥልጣናቸው ከተነሱት ውስጥ አቶ ሽፈራው ጃርሶ ሲሆኑ፣ የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር እንደነበሩ ይታወቃል። በአቶ ሽፈራው ጃርሶ ምትክ የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተደርገው የተሾሙት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ሲሆኑ፣ አቶ ኃይለማርያም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የህዝብ አደረጃጀት አማካሪ የነበሩ ናቸው።
ከሥልጣናቸው ከተነሱትና በሥልጣን ቅይይሩ ውስጥ ያልተካተቱት የትምህርት ሚኒስትር የነበሩት ዶ/ር ስንታየሁ ወልደሚካኤል አንዱ ናቸው። በአቶ ብርሃኑ ኃይሉ ቦታ የትምህርት ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት አቶ ደመቀ መኮንን ሲሆኑ፣ አቶ ደመቀ የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት ናቸው።
የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነቱ እና የግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስትርነት ሥልጣኑን ይዘው የነበሩት አቶ አዲሱ ለገሠ መሆናቸው የሚታወቅ ሲሆን፣ የግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስትርነት ሥልጣናቸው በዛሬው ሹም ሽር ተቀንሶባቸዋል። በዚህም መሠረት የግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስትር ተደርገው የተሾሙት አቶ ተፈራ ደርበው መሆናቸው ታውቋል።
በዛሬው ዕለት ከሥልጣናቸው ከተነሱት ውስጥ የሴቶች ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ወ/ሮ ሒሩት ዴሌቦ ሲሆኑ፣ በምትካቸው ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል የሴቶች ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል። ወ/ሮ ሙፈሪያት የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ አባል እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል።
በዛሬው ሹም ሽር ከሚኒስትርነት ሥልጣናቸው የተነሱት አምስት ባለሥልጣናት አቶ አሰፋ ከሲቶ ከፍትህ ሚኒስትርነት፣ አቶ ሽፈራው ጃርሶ ከየመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትርነት፣ ዶ/ር ስንታየሁ ወልደሚካኤል ከትምህርት ሚኒስትርነት፣ አቶ አዲሱ ለገሠ ከግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስትርነት እንዲሁም ወ/ሮ ሒሩት ዴሌቦ ከሴቶች ጉዳይ ሚኒስትርነት መሆኑ ታውቋል።