ኦባማ ከአልቃይዳ ማስጠንቀቂያ ደረሳቸው
Ethiopia Zare (ቅዳሜ ኅዳር 13 ቀን 2001 ዓ.ም. November 22, 2008)፦ ባራክ ኦባማ አሜሪካ በኢራቅ ያላትን ጦር አስወጥተው ትኩረታቸውን ወደ አፍጋኒስታን የሚያደርጉ ከሆነ ወንጀለኛ በሚሏቸው አሜሪካኖች ላይ ጥቃታቸውን እንደሚቀጥሉ የአልቃይዳ ምክትል መሪ አልዛዋሂር አስታውቀዋል።
አልዛዋሂር ኅዳር 10 ቀን 2001 ዓ.ም. በኢንተርኔት ባስተላለፉት መልዕክት፣ ባራክ ኦባማ የጆርጅ ቡሽን ፖሊሲ የሚከተሉ ከኾነ ውድቀት ይከተላቸዋል ብለዋል። ኦባማ አፍጋኒስታን ላይ ያላቸውን አቋም ሳይቀይሩ የአሜሪካንን ጦር ወደ አፍጋን የሚልኩ ከኾነ ቡሽና የቀድሞው የፓኪስታን መሪ የደረሰባቸውን ሽንፈት ለኦባማም እንደማይቀርላቸው አስታወቀዋል። ኦባማ ይህን ከማድረጋቸው በፊት እንግሊዝና ሶቪየት ሕብረት በአፍጋን የደረሰባቸውን አሳዛኝ ነገር ማስተዋል ይጠበቅባቸዋል በማለት ዛቻ አዘል መልዕክት አስተላልፈዋል።
ኦባማ መመረጣቸው በአሜሪካ ፖሊሲ ላይ ለውጥ አያመጣም ያሉት አልዛዋሂር እንዲያውም ሙስሊሞች እና ሌሎች አካላት ላይ ጫና ያሳድራል ብለዋል።
የኦባማ የሽግግር ቡድን የአልዛዋሂርን አስተያየት ”ከሽብርተኞች የሚጠበቅ ሠይጣናዊ ምክር ነው” በማለት ተችተውታል። አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን እንዳሉት፣ ”እኛ አሜሪካውያንና ምዕራባዊያን በዲሞክራሲ ፅንሰ ሃሳብ አንድ ላይ ተነስተናል እነዚህ ሽብርተኞች ግን እንዲህ ዓይነት አስተያየት ለመስጠት ካልሆነ በቀር፣ ለምን ሊነሱ ይችላሉ” ሲሉ ጠይቀዋል።



