Ethiopia Zare (ዓርብ ኅዳር 26 ቀን 2001 ዓ.ም. December 05, 2008)፦ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ፣ በሶማሊያ ያለውን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሚተካ ጦር እስከሚያዘጋጅ ድረስ፣ ኢትዮጵያ ጦሯን በሶማሊያ ለማቆየት መስማማቷን አንድ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለሥልጣን ገለፁ።

 

የአፍሪካ ሕብረት በበኩሉ በሶማሊያ የሚገኘው የሕብረቱ ሠላም አስከባሪ ተልዕኮ አሚሶም የሰው ኃይሉና ሎጅስቲኩ የተሟላ ባለመሆኑ፣ የኢትዮጵያ ጦር ከመውጣቱ በፊት ድጋፍ እንዲደረግለት ጥሪ አቅርቧል።

 

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ዣን ፒንግና የሠላምና ፀጥታ ኮሚሽን ኃላፊ ራምታኔ ላማምራ፣ የዐረብ ሊግ ሀገራት ለሕብረቱ ሠላም አስከባሪ ድጋፍ በሚሰጡበት ሁኔታ ላይ ለመምከር ወደ ግብፅ ካይሮ አቅንተዋል።

 

ኮሚሽነር ላማምራ በሣምንቱ መጨረሻ ወደ ኒው ዮርክ በማቅናት፣ ከተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊና ከፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ጋር እንደሚመክሩ ይጠበቃል። ኮሚሽነር ላማምራ በሣምንቱ የተጨናነቀ ጉዞ የሚያደርጉት የአፍሪካ ሕብረት የሶማሊያ ሠላም አስከባሪ ተልዕኮ ቁጥርን ለማሳደግ ገንዘብ ለማሰባሰብ ነው።

 

አሚሶም ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጋር በመሆን፣ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዕውቅና ላለው የሶማሊያ ሽግግር መንግሥት ድጋፍ እያደረገ መሆኑ ይታወቃል።

 

የአፍሪካ ሕብረት ባለሥልጣናት እንደገለፁት፣ ኖርዌይ ለሕብረቱ አዎንታዊ ምላሽ የሰጠች ሲሆን፣ በድጋፉ ዙሪያ ምላቯን በቀናት ውስጥ ለማስታወቅ ቃል ገብታለች።

 

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለሥልጣን እንዳሉት፣ ኢትዮጵያ ታህሣስ 22 ቀን 2001 ዓ.ም. ከሶማሊያ ለቃ ለመውጣት ወስና የነበረ ቢሆንም፣ አሚሶምን የሚተካ ኃይል በሶማሊያ እስከሚደርስ ድረስ ግን ጦሩ ለሣምንታት እንዲዘገይ ተስማምታለች።

 

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በሶማሊያ ጉዳይ ላይ ዝምታ በመምረጡ ትዕግስታቸው እንደተሟጠጠ ገልፀዋል።

 

ኢትዮጵያና ሌሎች የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) አባል ሀገራትም፣ በሁኔታው የተሰላቹ መሆናቸውን በቅርቡ የገለፁ ሲሆን፤ የሶማሊያ የሽግግር መንግሥት መዳከም ጽንፈኞች የበቀል እርምጃ እንዲወስዱ ስለሚያደርግ፣ በምሥራቅ አፍሪካ አለመረጋጋት ሊፈጥር ይችላል ብለዋል።

 

ባለፈው ወር ኢጋድ ለሶማሊያ ሠላም እንቅፋት በሚሆኑ አካላት ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ውሳኔ ያሳለፈ ሲሆን፣ እንቅፋት የሚፈጥሩ የተባሉት በስም ባይገለፁም የሽግግር መንግሥቱ ፕሬዝዳንት አብዱላሂ የሱፍ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተገምቷል።

 

የኢትዮጵያ መንግሥት በታህሣስ 2006 እ.ኤ.አ. የሶማሊያን ሽግግር መንግሥት ለመርዳት በሚል ወደ ሀገሪቱ ከገባ በኋላ፣ ከእስላማዊ ጽንፈኛ ቡድኖችና በጎሣ ከተደራጁ ታጣቂዎች ተደጋጋሚ ጥቃት ተሰንዝሮበታል።

 

ራሱን በሞቃዲሾና በባይዶዋ ገድቦ የተቀመጠው ሽግግር መንግሥቱና ተቃዋሚ አንጃዎች፣ የተኩስ አቁም መፈራረማቸው የኢትዮጵያ ጦር ከሶማሊያ ለቆ እንዲወጣ መንገድ እንደጠረገለት ይነገራል።

 

የኢትዮጵያ ጦር ሀገሪቱን ለቆ ለመውጣት በተቃረበበት በአሁኑ ሰዓት፣ በሶማሊያ ሁከት እና የባህር ላይ ውንብድና የነገሰ ሲሆን፣ የተባበሩት መንግሥታትም ሶማሊያን የዓለማችን የከፋ ሰብዓዊ ቀውስ የነገሰባት ብሏታል።

 

የዓለም የምግብ ፕሮግራም እንደተነበየው 3.2 ሚሊየን ሶማሊያዊያን ወይም 40 በመቶ ህዝቧ የአስቸኳይ ምግብ ዕርዳታ ያስፈልገዋል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ