PM Meles ZenawiEthiopia Zare (ዓርብ ታህሳስ 3 ቀን 2001 ዓ.ም. December 12, 2008)፦ የኢትዮጵያ ጦር በአስቸኳይ ከሶማሊያ እንዲወጣ ቢወሰንም፤ የሀገሪቱ የመከላከያ ኃይል ጣልቃ በገባበት ወቅት ኢትዮጵያ የወሰደችውን እርምጃ ደግፈው የገቡ የኡጋንዳና የብሩንዲ ወታደሮች እስኪወጡ የኢትዮጵያ ጦር እንደማይወጣ ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ አስታወቁ።

 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትናንትናው ዕለት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ በሰጡበት ወቅት፤ የሶማሊያ የሽግግር መንግሥት ጉዳይ በፖለቲካዊ መንገድ ለመፍታትና አሸባሪዎችን ከኅብረተሰቡ ለመነጠል የሚያስፈልገውን እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ ባልሆነበት ወቅት የውጪ ኃይሎች የሚያደርጉት አስተዋፆ ረጅም ርቀት እንደማይወስድ በመገንዘብና ለሶማሊያ የፖለቲካ ኃይሎች ጉዳዩ በሠላማዊ መንገድ ለመጨረስ በቂ ጊዜ የተሰጣቸው መሆኑን ከግምት በማስገባት የኢትዮጵያ የመከላከያ ኃይል ከሶማሊያ በአፋጣኝ እንዲወጣ መወሰኑን አስታውቀዋል።

 

በዚሁ መሠረት በአሁኑ ወቅት ውሳኔውን ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸው፤ ውሳኔው ተግባራዊ በሚደረግበት ወቅት ግን ”የራሳችን ኃይል ከመቋድሾ ከሌሎች የሶማሊያ አካባቢዎች እንዴት ይወጣል? ለመውጣት ምን ያህል ጊዜ ይወስድበታል?” የሚለው ጉዳይ በሁለተኛ ደረጃ የሚታይ መሆኑን ተናግረዋል።

 

ከኢትዮጵያ ድንበር እስከ መቋዲሾ ድረስ ያለው ርቀት፤ ከአዲስ አበባ እስከ ባህርዳር ያለውን ርቀት እንደሚያንስ ጠቁመው ”ዋናው የመከላከያ ኃይላችን ከመቋዲሾ እንዴት ይወጣል? አይደለም ዋናው ጉዳይ የመከላከያ ኃይላችን ጣልቃ በገባበት ወቅት፣ ኢትዮጵያ የወሰደችውን እርምጃ በመደገፍ ወታደሮቻቸውን ወደ ሶማሊያ የላኩ ሀገሮች ወታደሮቻቸውን እንዴት ያስወጣሉ? የሚል ነው። የመከላከያ ኃይላችን በሚወጣበት ወቅት በአካባቢው ያለ የኡጋንዳና የብሩንዲ ወታደሮች መውጣት እንደሚፈልጉ ገልፀውልናል። በመሆኑም የመከላከያ ኃይላችን የመጀመሪያው እርምጃ እነዚህ ኃይሎች መውጣት እስከቻሉ ድረስ መውጣት ይችሉ ዘንድ አስፈላጊውን የፀጥታና የሕግ ማስከበር ሥራ መሥራት ነው።” ብለዋል።

 

”የኡጋንዳንና የብሩንዲ ወታደሮች በሠላም መቋዲሾን ለቀው ከወጡ በኋላ የመከላከያ ኃይላችን መቋዲሾና አካባቢውን ለቆ የሚወጣበት ሁኔታ ይኖራል።” ሲሉ በውሳኔው ብቻ የኢትዮጵያ ጦር ሶማሊያን ለቆ እንደማይወጣ አስታውቀዋል።

 

እየተጠበቀ ያለውም የኡጋንዳና የብሩንዲ ወታደሮችን ለማስወጣት የሚያስፈልጉ መርከቦችና አውሮፕላኖች መቋዲሾ ደርሰው በሠላም እንዲወጡ ለማድረግ እንደሆነ ተናግረዋል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ