የአሜሪካ የጦር ዕዝ በሶማሊያ የባህር ላይ ወንበዴዎች
![]() |
“ዩ.ኤስ.ኤስ. ሐዋርድ” የተሰኘችው የዩናይትድ ስቴትስ የአሜሪካ ባህር ኃይል የጦር መርከብ (በግራ)፣ የሩሲያ “ኑስትራሺሚ” የተሰኘችው ሚሳይል ተሸካሚ የጦር መርከብ (በቀኝ) (ፎቶ AP) |
ጄኔራል ዊልያም እንደሚናገሩት አሜሪካ በአፍሪካ እዚህም እዚያም የጦር ዕዝ የማቋቋም ፍላጎት የላትም፤ ከአፍሪካ አህጉር ላይቤሪያ “አፍሪካም” (Africom) እንዲቀመጥባት የተስማማች ብቸኛ ሀገር ስትሆን፣ የ”አፍሪካም” (Africom) ዋና መስሪያ በጀርመን እስቱት ጋርት ሆኖ 1,300 ወታደራዊና ሲቪል ሠራተኛ እንደሚኖሩት ይነገራል።
አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት የ(Africom) መቋቋም አሜሪካ የአፍሪካ የፀጥታ ጉዳይ ዋንኛ አጀንዳዋ መሆኗን ያሳያል። በተለይም የእስልምና አክራሪዎች መበራከት፣ በነዳጅ ማውጫ አካባቢዎች የፀጥታ መጥፋት፣ በአፍሪካ ስር እየሰደደ የመጣው የቻይና የበላይነትን መወዳደር የአሜሪካ ተቀዳሚ ፍላጐቶች ናቸው። የአሜሪካ ባለሥልጣናት የ(Africom) በአፍሪካ መመሥረት ምንም ድብቅ አጀንዳ የለውም ቢሉም፤ ሃሳባቸው በህዝቡ ዘንድ ጥርጣሬ ከመፍጠር አላመለጡም። የተረጋጋች አፍሪካን መመሥረት፣ ሰብዓዊ ዕርዳታ በአግባቡ እንዲደርስ ማድረግ፣ የ(Africom) ዓላማ መሆኑ በአፅንዖት ቢገለጽም፤ በአፍሪካውያን ዘንድ በግልፅ ሊመከርበት ይገባል የሚለው ሃሳብ እየጎላ መጥቷል።
የ(Africom) ዕዝ እንዲከፈት አሜሪካ ከላይቤሪያ ይሁንታ ካገኘች በኋላ በደቡብ አፍሪካም ዕዙን ለማቋቋም ፍቃድ ለማግኘት ደፋ ቀና ማለት ጀምራለች። በነገራችን ላይ አሜሪካ በአፍሪካ ውስጥ ያላት ዋንኛ ማዘዣ በጅቡቲ ካምፕ ሊሞኒየር የሚገኘው ሲሆን፣ 1,800 ወታደሮች ዝግጁ ሆነው ተቀምጠውበታል።
አፍሪካ ወደፊት የዓለም ነዳጅ ገበያ እምብርት የመሆኗ ጉዳይ የአሜሪካን ትኩረት ከሳቡት ጉዳዮች ቀዳሚው ሲሆን፣ በአህጉሪቱ ሦስት ዋነኛ ወታደራዊ የማዘዣ ጣቢያዎች (Military commands) የመክፈት ዕቅድ አላት።
ማዕከላዊ ዕዝ (Centcom)፦ ይህ ዕዝ ግብፅን፣ ሱዳንን፣ ኤርትራን፣ ኢትዮጵያን፣ ጅቡቲን፣ ሶማሊያንና ኬንያን የመቆጣጠር ኃላፊነት ይኖረዋል።
የአውሮፓውያን ዕዝ (Eucom)፦ ይህ ዕዝ የአፍሪካን አብዛኛውን ክፍል የመቆጣጠር ኃላፊነት ይኖረዋል።
የፓስፊክ ዕዝ (Pacom)፦ ይህ ዕዝ ማደጋስካርን፣ ሲቪልስንና የሕንድ ውቅያኖስ አካባቢዎችን የመቆጣጠር ኃላፊነት ይኖረዋል።
የእነዚህ ማዘዣዎች መመሥረት ከምንም በላይ አሜሪካ በሽብርተኝነት ላይ ለከፈተችው ጦርነት መሳካት እንደግብአት ሊያገለግሉ ይችላሉ። በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ የአሜሪካ ዋነኛ ትኩረት የሶማሊያ ጉዳይ ሆኗል። በተለይ ደግሞ የአልቃይዳ አባል የሚጠለሉበትና የሚሰለጥኑበት መሆኑ አካባቢውን በትኩረት እንዲመለከቱ አስገድዷቸዋል። በሶማሊያ ባህር ዳርቻዎች የባህር ላይ ወንበዴዎች ወይም ዘራፊዎች መበራከታቸውን ለመግታት አሜሪካ እየወሰደች ያለችው እርምጃ ከዚሁ ካነሳነው ነጥብ ጋር ይያያዛል።
በሶማሊያ ባህር ዳርቻዎች በሕንድ ውቅያኖስ ላይ የባህር ላይ ዘራፊዎች ብቅ ብቅ ማለት የጀመሩት ዛሬ ሳይሆን ሶማሊያ መንግሥት አልባ በነበረችባቸው ባለፉት 20 ዓመታት ነው። በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ የሰብዓዊ ዕርዳታ የጫኑ በርካታ መርከቦች ታግደዋል፣ ሠራተኞቻቸው ተገድለዋል፣ መርከቦቹንም ለማስለቀቀ ገንዘብ ጠይቀዋል። የሶማሊያ የባህር ላይ ወንበዴዎች ከሌሎች የባህር ላይ ዘራፊዎች የሚለያቸው ጉዳይ በደንብ የተደራጁና የታጠቁ መሆናቸው፣ ስለመርከብ የጠለቀ ዕውቀት ያላቸው መሆናቸው ሲሆን፤ አንዳንድ ጊዜ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው በመምሰል የድረሱልኝ ጥሪ አሰምተው በርካታ መርከቦችን አግተው ዘርፈዋል።
ዓለም አቀፉ የባህረተኞች ቢሮ እንዳስታወቀው በሰማሊያ የባህር ዳርቻዎች በ2007 ብቻ 21 የእገታ ሙከራዎችና እገታዎች ተፈፅመዋል። በተያዘው የአውሮፓውያን ዓመትም በርካታ የእገታ ድራማዎች ተከናውነዋል። በቅርቡ የተከናወነው የእገታ ድራማ ግን አሜሪካ እና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ፊታቸውን ወደ አጋቾቹ እንዲያዞሩ አስገድደዋቸዋል።
በቅርቡ የታገተችው “ፋይና” የተሰኘቸው የዩክሬይን መርከብ 33 ሩሲያ ሠራሽ T-72 ታንኮችን፣ ጥይቶችን፣ መለዋወጫዎችንና ትልልቅ ላውንቸሮችን እንደጫነች በሕንድ ውቅያኖስ ላይ መታገቷ በርካታ ሀገራት በጉዳዩ እጃቸውን እንዲያስገቡ አስገድዷቸዋል። አጋቾቹ መጀመሪያ 35 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር፣ በመቀጠል 20 ሚሊዮን ዶላር ከተሰጣቸው መርከቧንና ሠሪተኞቿን እንደሚለቁ ሲገልጹ፤ የተጫነውን የጦር መሣሪያ የመውሰድ ፍላጎት ግን እንደሌላቸው አስታውቀዋል። ይህ ሁኔታ የሽብርተኝነት ስጋት በአፍሪካ ቀንድ እያንዣበበ ነው፤ አልቃይዳን የመሳሰሉ ቡድኖች በሶማሊያ ሊንቀሳቀሱ ይችላሉ ለምትለው አሜሪካ የአጋቾቹ ማስተባበያ ቦታ የሚሰጠው አልሆነም። ይልቁንም የጦር መሣሪያው ካልተጠበቁ ወገኖች እጅ እንዳይገባ በሚል ራሷን ለወታደራዊ እርምጃ አዘጋጅታለች። የሶማሊያ የባህር ላይ ወንበዴዎች ያገቱዋት የዩክሬይንዋ የጭነት መርከብ “ፋይና” (ፎቶ AP)
በሕንድ ውቅያኖስ ዳርቻ የሚገኘው የአሜሪካ ባህር ኃይል 5ኛ ግብረኃይል መርከቦቹን ወደታገተችው መርከብ በማስጠጋት የአጋቾቹን ሁኔታ በ8 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ሆነው ለመቆጣጠር ቢችሉም ለጊዜው ጥቃት ለመሰንዘር የመዘጋጀታቸው ሁኔታ ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል። ይሁን እንጂ የአሜሪካ ባህር ኃይል በአጋቾቹ ላይ የሚወሰደው እርምጃ የአክራሪዎችንና የሽብርተኞችን የተሳሳተ አካሄድ ለማረም የሚያስችል መሆኑን እየገለፀ ነው። የአሜሪካ ባህር ኃይል የፈረጠመ ክንዱን ለአጋቾቹ ቢያሳይም አጋቾቹ ግን “ፍንክች የአባ ቢላዋ ልጅ” ብለው የማስጠንቀቂያ ዛቻ እየሰነዘሩ ነው። አጋቾቹ በዙሪያቸው የአሜሪካ ባህር ኃይል መርከቦችና የሌሎች ሀገራት መርከቦች የመታየታቸው ሁኔታ መርከቧን ለመልቀቅ እንደሚያስገድዳቸው፣ ገንዘብ ከመጠየቅም እንደማይገታቸው እየገለጹ ነው። ከማንኛውም ወገን ጥቃት የሚሰነዝር ከሆነም ጥቃቱን እስከመጨረሻው ለመመከት ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልፀዋል። “ዩ.ኤስ.ኤስ. ሐዋርድ” የተሰኘችው የዩናይትድ ስቴትስ የአሜሪካ ባህር ኃይል የጦር መርከብ (በግራ)፣ የሩሲያ “ኑስትራሺሚ” የተሰኘችው ሚሳይል ተሸካሚ የጦር መርከብ (በቀኝ) (ፎቶ AP)
በታገተችው መርከብ ዙሪያ የሚታዩት የአሜሪካ የጦር መርከቦች ብቻ አይደሉም፤ የሩስያ መርከቦች እንዲሁም የየትኛው ሀገር እንደሆኑ በውል ያልተለዩ ሌሎች መርከቦችም ጭምር እንጂ። ይህ ደግሞ እንደተንታኞች ገለፃ የተጫነው የጦር መሣሪያ ለማይገባቸው ወገኖች እንዳይደርስ የሁለም ወገኖች ፍላጎት ነው። የሰሜን ሶማሊያ የፑንት ላንድ ራስ ገዘ አስተዳዳር አየል (EYL) በተባለው ወደቡ አካባቢ ዝርፊያ የሚፈፅሙትን የተደራጁ ወንበዴዎች ተግባር ለመግታት አቅም የለኝም እያለ ነው። ለሁለት አስርት ዓመታት ያህል ማዕከላዊ መንግሥት አልባ የነበረችው ሶማሊያ የሽግግር መንግሥትም የወንበዴዎቹን እንቅስቃሴ ለማቆም አቅም እንደሌለው እየታየ ነው። ይህ ሆነ ማለት ደግሞ የአብዛኛዎቹ መርከቦች በኤደን ሠላጤ በኩል ወደ አውሮፓና እስያ የሚያደርጉት ጉዞ ተሰናከለ ማለት ነው። ይህ ደግሞ አሜሪካም ሆነች ሌሎች ሀገራት የሚፈልጉት ጉዳይ አይደለም። የአሜሪካ የባህር ኃይል ኦፊሰር የታገተችውን የዩክሬይንዋን “ፋይና” መርከብ ሲቃኝ (ፎቶ AP)
የተደራጁ የባህር ላይ ወንበዴዎች የሚንቀሳቀሱባት የአየር ወደብ በአብዛኛው የመርከብ እገታና ዝርፊያ ይፈፀምባታል። በአካባቢው ይህን መሠል የውንብድና ተግባር ስለሚፈፀምም በአካባቢው የሚተላለፉ መርከቦች እስከ አስር እጥፍ የኢንሹራንስ ክፍያ ለመክፈል መገደዳቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ። አንድ መርከብ የሚታገት ከሆነም ከ300 ሺህ የአሜሪካ ዶላር እስከ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለመክፈል ይገደዳል። አስገራሚ የሚሆነው ግን ጥቃት የሚፈፅሙት ሰዎች ቁጥር አነስተኛ የመሆናቸው ጉዳይ ነው። ነገር ግን በዘመናዊና ፈጣን ጀልባ የሚጓዙ ከባድ መሣሪያ የታጠቁ ሰዎች መሆናቸውን የዓይን እማኞች ይገልፃሉ። አንድ ጊዜ መርከቧን ከተቆጣጠሩ በኋላ ቁጥራቸው ወዲያውኑ ጨምሮ ከ50 በላይ ሰዎች ሊሰበሰቡ ይችላሉ። የባህር ላይ ወንበዴዎች ቁጥራቸው ከፍተኛ እንደሆነ ለማስመሰልም የታገቱ ሰዎችን እንደሚጠቀሙ ይነገራል። የሶማሊያ የባህር ላይ ወንበዴዎች ያገቷትን “ፋይና” መርከብ በትናንሽ ጀልባዎች ከበዋት (ፎቶ AP)
የፈረንሣይ የጦር ኃይል በዚህ መልኩ በታገተች መርከብ ላይ በቅርቡ እርምጃ በመወሰድ ታጋቾችን አስለቅቋል። አጋቾቹ ወደ አየር ወደብ መፈርጠጣቸው አሳሳቢ መሆኑ ተገልጿል። ይህም አካባቢው ምቹ ገነታቸው መሆኑን እንደሚያሳይ እየተነገረ ነው። እንደ አንዳንድ ወገኖች ገለፃ አጋቾቹ የሶማሊያ የሽግግር መንግሥት ፕሬዝዳንት የአብዱላሂ የሱፍ ጐሣ (የማጃርቴን ጎሣ) አባላት ናቸው። መርከቦችን ካገቱ በኋላ ከፍተኛ ገንዘብ ስለሚቀበሉም በኢኮኖሚ የደረጁ ናቸው። ለዚህ ነው የፑንትላንድ መሪዎች እነርሱን ለመቋቋም አቅም የለንም የሚሉት። እና እነርሱ ሊቋቋሟቸው ካልቻሉ ማን ይመክታቸው? የሚለው አንገብጋቢ ጥያቄ ሆኗል። የአሜሪካ ባህር ኃይልና የሌሎች ሀገራት ጦሮች ጣልቃ ገብነትስ እስከመቼ መቀጠል አለበት የሚለውም እንዲሁ ሊታሰብበት የሚገባ ጥያቄ ነው። በርካታ አፍሪካውያን እንደሚያምኑበት (Africom) ብዙ በአፍሪካ ውስጥ መመሥረቱ ከጠቀሜታው ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል። ለምሣሌ ያህል የሶማሊያን የባህር ላይ ውንብድና የመግታት አቅም ቢኖረው እንኳ አፍሪካን በዘላቂነት የመቆጣጠርና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞቿን የመጠቀም ሁኔታን ሊፈጥር ይችላል፤ እንዲያውም የአፍሪካን ጥቅም ከማስጠበቅ ይልቅ የአሜሪካን ጥቅም የማስጠበቁ ሁኔታ ሊያመዝን እንደሚችል የሚናገሩ አፍሪካውያን አሉ። የታገቱት የመርከቧ ተሳፋሪዎች (ፎቶ AP)
የ(Africom) በአፍሪካ ውስጥ መመሥሪት የአፍሪካን ፖለቲካዊ ቀውሶች በመፍታት በኩል በአፍሪካውያን ዘንድ ያለው ግንዛቤ የተዛባ መሆኑን የ(Africom) አዛዥ ጄኔራል ዊልያም ዋርድ ይገልጻሉ። የ(Africom) ዓላማ የአፍሪካውያንን አቅም በመገንባት፣ በምግብ ዋስትናና በሠላም ማስከበር ረገድ ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ ነው። አፍሪካውያን በወታደራዊ ሥልጠና፣ በሠላም ማስከበርና በዕርዳታ ሥራ መርዳት መሆኑን ቢገልፁም፤ ይህ ሁሉ በአፍሪካውያን ዘንድ በጥርጣሬ እየታየ ነው። የሶማሊያ አጋቾችን እንቅስቃሴ ለመከላከል እያደረገችው ያለችው ዝግጅት አሜሪካ በአፍሪካ የጀመረችው የፀረ-ሽብር ተግባር አንድ አካል ነው።
በሶማሊያ የባህር ላይ ወንበዴዎች ዙሪያ አንድ ጉዳይ እናክል። የባህር ላይ ዘራፊዎቹ ቁጥርና የእገታ ተግባር እየተበራከተ መምጣቱ ኢትዮጵያን ከማንም በላይ የሚያሳስባት ጉዳይ መሆኑን ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ገልፀዋል። የሚያሳስበው ጉዳይ ደግሞ የእገታው መበራከት ብቻ ሳይሆን እገታው ከሶማሊያ አለመረጋጋት ጋር በቀጥታ የተሳሰረ መሆኑ ነው። በቅርቡ የታገተችው የዩክሬይን መርከብ የጫነችው የጦር መሣሪያን አክራሪው የአልሸባብ እጅ ቢገባ አካባቢውን ከማተራመስ አልፎ በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት መሠንዘሩ የተቃረበ አደጋ (Imminent danger) መሆኑ ይመስላል ጠቅላይ ሚኒስትሩን ያሳሰባቸው።
ይህ ሁሉ ሆኖ ፈረንሣይ እና አሜሪካ እያረቀቁት ያለው የውሳኔ ሃሳብ በፀጥታው ጥበቃ ም/ቤት የሚፀድቅ ከሆነ የባህር ላይ ወንበዴዎችን አባሮ ለመምታት ሀገራት መብት ይኖራቸዋል። ይህ ደግሞ የሶማሊያን የባህር ክልል እንደፈለጉ የሚፈነጩበትን የባህር ላይ ወንበዴዎች አቅም ያላቸው ሀገራት ሁሉ ክንዳቸውን እንዲሰነዝሩ ዕድል ይሰጣል።