Prof. Mesfin WoldemariamW/t Birtukan Mideksaድርጊቱ የተፈጸመው ከፓስተር ዳንኤል ጽ/ቤት ሲወጡ ነው

Ethiopia Zare (ሰኞ ታህሳስ 20 ቀን 2001 ዓ.ም. December 29, 2008)፦ ዛሬ በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከሰዓት በኋላ ወደ 8፡30 ሰዓት አካባቢ ቦሌ ከሚገኘውና ከሽማግሌዎቹ አንዱ ከሆኑት ፓስተር ዳንኤል ጽ/ቤት ለአራት ሰዓታት ቆይተው የወጡት የ78 ዓመቱ ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም ተደብድበው ወደ ሆስፒታል ሲወሰዱ፣ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ደግሞ ታስረው ወዴት እንደተወሰዱ ለጊዜው ለማረጋገጥ አልተቻለም።

 

የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ሊቀመንበር የሆኑት ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ እና የፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት አባል ሆኑት ፕሮፌሠር መስፍን ወልደማርያም ከጠዋቱ አራት ሰዓት አካባቢ ጀምሮ “ፕሪዝነርስ ፌሎሺፕ” በተሰኘውና ቦሌ አካባቢ ከሚገኘው መስሪያ ቤት ነበሩ። “ፕሪዝነርስ ፌሎሺፕ” የሚመራው በፓስተር ዳንኤል ሲሆን፣ ፓስተሩ ምርጫ 97ትን ተከትሎ ታስረው የነበሩትን የቀድሞው የቅንጅት ከፍተኛ አመራሮች ለማስፈታት በተቋቋመው የሽማግሌዎች ቡድን ውስጥ አባል ናቸው።

 

ሁለቱ የአንድነት ፓርቲ መሥራቾችና ከፍተኛ አመራር አባላት ወደ ፓስተሩ መሥሪያ ቤት ያመሩት ከወ/ት ብርቱካን ጋር በተያያዘ ለሚፈረም ሰነድ ጉዳይ እንደነበር የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገልጸዋል።

 

ከአራት ሰዓት ቆይታ በኋላ ፓስተር ዳንኤል ፕ/ር መስፍንን እና ወ/ት ብርቱካንን ከጽ/ቤታቸው ሸኝተዋቸው እንደተመለሱ፤ የአንድነት ፓርቲ አመራሮቹ ወደመኪናዎቻቸው ያመራሉ። በዚህን ሰዓት ወ/ት ብርቱካንን ደህንነቶች እንደሆኑ የተገመቱ ሰዎች ይከቡዋቸዋል። ይህን ጊዜ ፕሮፌሠር መስፍን ወልደማርያም ወደ ወ/ት ብርቱካንና ወደከበቧቸው የደህንነት ሰዎች በማምራት ነገሩን ለማጣራት ጥረት ያደርጋሉ።

 

ከባቢዎቹ ወ/ት ብርቱካንን ለመውሰድ እንደመጡ ሲናገሩ፤ ፕ/ር መስፍን ደግሞ “ይሄ ሁሉ ወታደር ለአንድ ሰው ምን ያደርጋል፤ በአንድ ወረቀት በሕጋዊ መንገድ መጥሪያ ብትልኩላት ልትመጣላችሁ ትችል ነበር” በማለት ሲናገሩ፤ “ምን አገባህ!” በማለትና አፀያፊ ንግግር በመናገር በእርግጫና በጥፊ ይደበድቧቸዋል።

 

በአካባቢው የነበሩ የዓይን ምስክሮች ለኢትዮጵያ ዛሬ እንደገለጹት ከሆነ ፕ/ር መስፍን ወደ ሆስፒታል ሳይወሰዱ እንዳልቀረና ወ/ት ብርቱካን ደግሞ ለጊዜው የት እንደሆነ ባይታወቅም ታስረው ተወስደዋል።

 

እነፕ/ር መስፍን ፓስተር ዳንኤል ጽ/ቤት የነበሩት ወ/ት ልትፈርመው ከነበረ ሰነድ ጋር መሆኑን ምንጮቻችን ቢገልጹም፤ ሰነዱ ወ/ት ብርቱካን በአውሮፓ ካደረጉት ንግግር ጋር በተያያዘ በዚህ ሰሞን የኢህአዴግ ባለሥልጣናትና የመገናኛ ብዙኃን “ይቅርታ አልጠየቅሁም ብለሻል” በሚል ሊቀመንበሯ ላይ እየደረሰ ካለው ወከባ፣ ጫናና ማስፈራራት ጋር ስለመያያዙ ሙሉ ለሙሉ የተረጋገጠ ነገር ባይኖርም፤ ሊሆን እንደሚችል ግን ሰፋ ያለ ግምት ተሰጥቶታል።

 

በዚህ ሰሞን በተለይም በወ/ት ብርቱካን ላይ እየደረሰ ያለውን እንግልት፣ ጫናና ማስፈራራት አስመልክቶ አስተያየት እንዲሰጡን የጠየቅናቸው የኢትዮጵያ ዛሬ የዘወትር ተባባሪ የሆኑ አንድ የፖለቲካ ተንታኝ፤ “የሰሞኑ የኢህአዴግ ድርጊቶች በተለይም በሠላማዊ ትግል አምነው በሀገር ውስጥ እየተንቀሳቀሱ ያሉትን ፖለቲከኞችና በሠላማዊ ትግል የሚያምኑትን ኢትዮጵያውን ተስፋ ለማስቆረጥ የሚደረግ እንቅስቃሴ አድርጌ ነው የምመለከተው” ብለዋል።

 

እኝኑ ተንታኝ አክለውም “ከኢህአዴግ ባህሪ አንፃር ያየነው እንደሆነ ደግሞ፤ በአንድነት ፓርቲ አመራሮች ውስጥ ክፍተት ለመፍጠርና የተረጋጋ የፖለቲካ አየር ንብረት እንዳይኖር ለማድረግ እንደሆነ መገመት ይቻላል። በዚህም ምክንያት የአንድነት አመራሮች በውስጣቸው ያለውን ጥንካሬ እርስ በእርሳቸው የሚፈትኑበት አጋጣሚ ነው የሚል ግምት አለኝ። ለዚህም ነው የ78 ዓመት ዕድሜ ባለፀጋ የሆኑትን ፕ/ር መስፍን ወልደማርያምን ደብድቦ ለሆስፒታል ለመዳረግ የተፈለገው።” ሲሉ ገልጸዋል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ