ፕሬዝዳንት ባራክ ሁሴን ኦባማ ሥልጣን ተረከቡ
ያሬድ ክንፈ (ከዋሽንግተን ዲሲ)

Ethiopia Zare (ማክሰኞ ጥር 12 ቀን 2001 ዓ.ም. January 20, 2009)፦ በዋሽንግተን ዲሲ ሰዓት አቆጣጠር ከቀኑ ስድስት ሰዓት ከአምስት ደቂቃ (12:05 P.M.) አካባቢ ሴናተር ባራክ ኦባማ ቃለ መኀላ በመፈጸም አርባ አራተኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነዋል።
የፕሬዝዳንታዊ ሥልጣን ሽግግሩ በሠላማዊ መንገድ ተከናውኗል። የመጀመሪያው ጥቁር አፍሪካ አሜሪካዊ ፕሬዝዳንቷን ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ ተረክባለች።
ፕሬዝዳንት ባራክ ሁሴን ኦባማ ቃለ መኀላ የፈፀሙት 16ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት አብርሃም ሊንከን በ1861 እ.ኤ.አ. የዛሬ 148 ዓመት ቃለ መኀላ በፈፀሙበት መጽሐፍ ቅዱስ ነው። አንዳንድ የመገናኛ ብዙኀን ቃለ መኀላ የሚደረገው በቅዱስ ቁርዓን ነው ሲሉ መዘገባቸው አይዘነጋም። ዘገባው ሐሰት መሆኑ ተረጋግጧል። ባራክ ኦባማ ቃለ መኀላውን ሲፈጽሙ መጽሐፍ ቅዱሱን ይዘውላቸው የነበሩት ባለቤታቸው ሚሼል ኦባማ ነበረች።
ፕሬዝዳንታዊ ቃለ መኀላውን ያስፈፀሙት የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሹም የሆኑት ጆን ሮበርትስ ናቸው።
47ኛው የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንም ቃለ መኀላውን የፈፀሙት ከፕሬዝዳንቱ በፊት ሲሆን፣ ባለቤታቸው ጂል ባይደን መጽሐፍ ቅዱሱን ይዘውላቸው ነበር። ቃለ መኀላውን ያስፈፀሙዋቸው የጠቅላይ ፍርድ ቤት ተባባሪ ሹም ጆን ፖል ስቴቨንስ ነበሩ።
ምክትል ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የ66 ዓመት አዛውንት ሲሆኑ፣ ለ36 ዓመታት የዴልዌር ሴናተር በመሆን አገልግለዋል።
ይህንን ዜና ባጠናከርኩበትና ለንባብ ባበቃሁበት ደቂቃ ላይ ፕሬዝዳንት ባራክ ሁሴን ኦባማ ቃለ መኀላቸውን ፈጽመው ለአሜሪካንና ለዓለም ህዝብ የመጀመሪያውን ፕሬዝዳንታዊ ንግግር በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
የዛሬውን የሥልጣን ሽግግር ውሎ አስመልክቶ የኢትዮጵያ ዛሬ አዘጋጅ ያሬድ ክንፈ ከዋሽንግተን ዲሲ ሰፋ ያለ ዘገባ ለማቅረብ በዝግጅት ላይ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ለአንባብያን ለመግለጽ እንወዳለን።
ቃለ መኀላውን እና የመጀመሪያውን ፕሬዝዳንታዊ ንግግር በቪዲዮ ለመመልከት ማጫወቻውን ይጫኑ!



