የፊታውራሪ አመዴ ለማ እና የወ/ሮ ስንዱ ገብሩ (የክብር ዶ/ር) የቀብር ሥነሥርዓት ተፈጸመ
የአንጋፋው አርቲስት ጥላሁን ገሠሠን (የክብር ዶክተር) የቀብር ሥነሥርዓት ሐሙስ ይፈጸማል
Ethiopia Zare (ረቡዕ ሚያዝያ 14 ቀን 2001 ዓ.ም. April 22, 2009)፦ በአንደበተ ርዕቱነታቸው እና በሀገር ሽማግሌነታቸው የሚታወቁት የፊታውራሪ አመዴ ለማ የቀብር ሥነሥርዓት በዛሬው ዕለት ኮልፌ በሚገኘው የእስላም መስጅድ ተፈጸመ። በተያያዘም እናት አርበኛ፣ የመጀመሪያዋ የሴት የፓርላማ አባልና የደራሲ ወ/ሮ ስንዱ ገብሩ (የክብር ዶክተር) የቀብር ሥነሥርዓት በዛሬው ዕለት በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በአርበኞች የቀብር ቦታ ተፈጽሟል።
ፊታውራሪ አመዴ በወሎ ክፍለ ሀገር በወረይመኑ አውራጃ ከአባታቸው ከአቶ ለማ እንድሪስና ከእናታቸው ከወይዘሮ ደስታ ገመች መጋቢት 30 ቀን 1913 ዓ.ም. ተወለዱ። እስከ 10ኛ ክፍል ድረስ በተወለዱበት አካባቢ የተማሩት ፊታውራሪ አመዴ ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ዲፕሎማ ያላቸው ሲሆን፣ በ1949 ዓ.ም. የፓርላማ አባል ሆነው በመመረጥ ሠርተዋል። ለ16 ዓመታትም በሕግ መምሪያና በሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ውስጥ አገልግለዋል።
ፊታውራሪ አመዴ የኢትዮጵያ ውሃ ዋና ፌዴሬሽን መስራችና ሥራ አስኪያጅ፣ የአክሱም ሀውልት አስመላሽ ኮሚቴ አባል፣ የፈጣን ሙያ ማሠልጠኛ ተቋም መስራችና ፕሬዝዳንት፣ የወሎ ትራንስፖርት መስራችና ሥራ አስኪያጅ፣ የኢትዮጵያ የባህል ስፖርት ፌዴሬሽን አባል በመሆንም ሠርተዋል።
በተጨማሪም የመቅደላ አፄ ቴዎድሮስ ሀውልትና የቱሪስት መስህብ ግንባታ ኮሚቴ አባል፣ የታሪካዊው የጀማ ንጉሥ የልማትና የግንባታ ኮሚቴ የበላይ ጠባቂ፣ የኢትዮ ኤርትራ የግጭት አስወጋጅ የሽምግልና ኮሚቴ አባል፣ የአላማጣ አውራጃ አስተዳዳሪ፣ የወሎ አውቶብስ ማኅበር ፕሬዝዳንት እንደነበሩና በ1997 ዓ.ም. በመንግሥትና በቅንጅት የላዕላይ ምክር ቤት ተመራጮች መካከል ተፈጥሮ በነበረው ችግር ተቋቁሞ በነበረው የሀገር ሽማግሌዎች ሕብረት ውስጥ በመሳተፍ ዕርቅ እንዲወርድ የበኩላቸውን ጥረት ካደረጉት ሽማግሌዎች መካከል አንዱ ናቸው።
ፊታውራሪ አመዴ ከትናንት በስቲያ በምግብ መመረዝ ምክንያት በመታመማቸው ወደ ቅዱስ ያሬድ ሆስፒታል ተወስደው ሕክምና ቢደረግላቸውም ሊሻላቸው ባለመቻሉ ትናንት ማክሰኞ ሚያዝያ 13 ቀን 2001 ዓ.ም. ጠዋት ወደ ሐያት ሆስፒታል ከተወሰዱ ከግማሽ ሰዓት በኋላ ከጠዋቱ አራት ሰዓት ላይ ሕይወታቸው በማለፉ የቀብር ሥነሥርዓታቸው በዛሬው ዕለት (ረቡዕ ሚያዝአ 14 ቀን 2001 ዓ.ም.) ኮልፌ በሚገኘው የእስላም መስጅድ ተፈጽሟል።
በፊታውራሪ አመዴ ለማ የቀብር ሥነሥርዓት ላይ የሣይንስና ቴክኒዮሎጂ ሚኒስትር ጁነዲን ሳዶ፣ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ሐሰን አብደላ፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታደሰ ኃይሌ፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ አህመዲን ሼህ አብዱላሂና የጠቅላይ ምክር ቤቱ የሥራ አስፈጻሚዎች እንዲሁም ፕሮፌሠር ኤፍሬም ይስኃቅን ጨምሮ ሌሎችም ታላላቅ ሰዎች ተገኝተዋል። ፊታውራሪ አመዴ ለ60 ዓመታት በኖሩበት የጋብቻ ዕድሜ በአንድ ሚስት ተወስነው 10 ልጆች፣ 34 የልጅ ልጆችና ስድስት የልጅ ልጅ ልጆች አፍርተዋል።
በተያያዘ ዜና የመጀመሪያዋ የሴት የፓርላማ አባል፣ ቀዳሚዋ የሴት ገጣሚ፣ ተውኔት ፀሐፊ፣ መጽሐፍ ደራሲ፣ ዲፕሎማት፣ የትምህርት ባለሙያ፣ ፖለቲከኛ እና እናት አርበኛ ወ/ሮ ስንዱ ገብሩ (የክብር ዶክተር እና የከንቲባ ገብሩ ደስታ ልጅ) የቀብር ሥነሥርዓት በዛሬው ዕለት (ረቡዕ ሚያዝአ 14 ቀን 2001 ዓ.ም.) በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በአርበኞች የቀብር ቦታ ተፈጽሟል።
ወ/ሮ ስንዱ ገብሩ በሸዋ ክፍለ ሀገር በመናገሻ አውራጃ በአዲስ ዓለም ከተማ ጥር 6 ቀን ውስጥ በ1908 ዓ.ም. ተወለዱ። ዕድሜያቸው ለትምህርት በደረሰበት ወቅት እቤታቸው አስተማሪ ተቀጥሮላቸው የአማርኛን ትምህረት ከፊደል መቁጠር እስከ ዳዊት መድገም በቤታቸው ተማሩ። ከዚያም ወደ አዲስ አበባ ሄደው በስዊድን ሚሲዮን ትምህርት ቤት በመግባት እስከ ስምንተኛ ክፍል ተምረዋል።
በ1921 ዓ.ም. ወደ ስዊዘርላንድ ለትምህርት ቢሄዱም ኑሮ ስላልተመቻቸውና ትምህርት ይሰጥበት የነበረውን የጀርመንኛ ቋንቋ ስላልወደዱት ወደ ፈረንሣይ አቅንተው ትምህርታቸውን ቀጠሉ። በመጨረሻም በስዊዘርላንድና በፈረንሣይ ሁለት ትምህርት ቤቶች በመዘዋወር በዲፕሎማ ተመረቁ። እዛው የሕግ ትምህርት ለመቀጠል ጀምረው የነበረ ቢሆንም፤ ፍላጎታቸው ወደ ሥነ-ጽሑፍ በማዘንበሉ በአጠቃላይ ለአምስት ዓመታት እዛው ተምረው ወደ ሀገራቸው ተመለሱ።
ወደ ሀገራቸው እንደተመለሱም በአዲስ አበባ በቅዱስ ጊዮርጊስ ትምህርት ቤት ውስጥ የፈረንሣይኛ ቋንቋን፣ ሃይጅን፣ ቁጥርንና የአማርኛ ድርሰት አጻጻፍን ማስተማር ጀመሩ። በዚህ ሁኔታ አንድ ዓመት እንደቆዩ ለብላታ ሎሬንሶ ትዕዛዝ ተዳሩና ባለቤታቸው የሐረርጌ ክፍለሀገር አስተዳዳሪ ሆነው በመሾማቸው ወደዚያው ከባለቤታቸው ጋር አቀኑ። ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላም ብላታ ሎሬንሶ የፍርድ ቤት ሹምና የዜና ስርጭት ኃላፊ ሆነው በመሾማቸው ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ አብረዋቸው ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ።
ፋሺስቶች ኢትዮጵያን በወረሩ ጊዜ ጃንሆይ (አፄ ኃይለሥላሴ) ወደ እንግሊዝ ሀገር ሲሰደዱ የወ/ሮ ስንዱ ባለቤትም አብረው ከጃንሆይ ጋር ሄዱ። ወ/ሮ ስንዱ ግን ከቤተሰቦቻቸው ጋር እና ሆለታ ውስጥ ከሚገኙ ወደ መቶ የሚጠጉ የጦር መኮንኖች ጋር ተቀላቅለው ፋሺስቶችን ለመፋለም ወደ ቦሬ ሄዱ። እዚያም የመትረየስ አተኳኮስ ትምህርት ተማሩ።
ወደ ነቀምት በመሄድም ህዝብን እየሰበሰቡ ስለነፃነት ማስተማሩን ተያያዙት። በዚህ ወቅት በባንዳዎች ጠቋሚነት በፋሽስት እጅ ከመውደቅ ለጥቂት አምልጠው ጎሬ ላይ ከራስ እምሩ ጦር ጋር ተቀላቀሉ። ከዚያም በጦርነቱ የሚጎዱ አርበኞችን ለማከም የሚሆን ቀይ መስቀል ለማቋም መፈለጋጀውን ለራስ እምሩ ሲያማክሯቸው 500 ብር ስለሰጧቸው አቋቁመው አርበኞችን መርዳት ጀመሩ።
እርሳቸው ተቀላቅለውት የነበረው የጥቁር አንበሳ ጦር ሲመታ በመማረካቸው ጣሊያኖች አስረው ወደ አዲስ አበባ አመጧቸውና የቁም እስረኛ ሆኑ።
የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. ግራዚያኒን ለመግደል በተደረገ ሙከራ ወንድማቸው መሸሻ ገብሩ አሉበት በመባሉ ይታሰሱ ስለነበር ወንድማቸውን ከአደጋ ለማዳን ሲፈልጉ በድጋሚ በፋሺስቶች እጅ ወደቁ። በወቅቱ ግራዚያኒ ይኖርበት የነበረው የጃንሆይ ቤተመንግሥት ታሰሩ። ቀጥሎም ወደ አስመራ፣ ከዚያ ወደ ምጽዋ ተወሰዱ። ከምጽዋ ወደብ ሦስት መቶ ወንዶችና ስምንት ሴቶች ሆነው በመርከብ “አዚናራ” ወደተባለች የኢጣሊያኖች እስር ቤት ተወስደው ዘጠኝ ወራት ታሰሩ።
ከእስር በኋላም ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ በእንደዚህ ያለ ተግባር ላይ እንዳይሰማሩ ከፍተኛ ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም፤ ማስፈራሪያው ሳይበግራቸው አርበኞችን በግጥም፣ በወኔ ቀስቃሽ ጽሑፎች በማበረታታት፣ መረጃ በማቀበል፣ መሣሪያ በማዳረስ የጀግንነት ተግባር ፈጽመዋል።
ከድል በኋላ ወ/ሮ ስንዱ ለሁለት ዓመታት ደሴ ከተማ የሚገኘው የወ/ሮ ስህን ትምህርት ቤት ዳይሬክተር በመሆን፣ ወደ አዲስ አበባ ተመልሰውም እቴጌ መነን ትምህርት ቤት ም/ርዕሰ መምህርነት፣ ከዚያም ዳይሬክተር ሆነው አገልግለዋል።
በእቴጌ መነን ትምህርት ቤት በነበሩበት ወቅት፤ “ኮከብ ያለው ያበራል ገና”፣ “የየካቲት ቀኖች”፣ “የኑሮ ስህተት” የሚሉ ትያትሮችን ሠርተው አቅርበዋል።
ከ1948 ዓ.ም. እስከ 1952 ዓ.ም. ድረስ የመጀመሪያዋ የሴት የፓርላማ የሕግ መምሪያ ምክር ቤት አባልና የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ም/ሊቀመንበር ሆነው አገልግለዋል።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ፕሬዝዳንት፣ የህዝባዊ ኑሮ ዕድገት ዋና ፀሐፊነትና አስተዳዳሪነት፣ በምዕራብ ጀርመን ለሦስት ዓመት የትምህርት አታሼ በመሆን አገልግለዋል። ወ/ሮ ስንዱ ከ10 በላይ መጻሕፍት የጻፉና፣ ስድስት ስክሪፕቶችን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማስቀመጣቸውም ታውቋል።
ወ/ሮ ስንዱ ላበረከቱት አስተዋጾ የወርቅ ሜዳሊያ፣ የንግሥት ሣባ የወርቅ ኒሻን፣ የቀይ መስቀል የወርቅ ሜዳሊያ እና በኢህአዴግ ዘመን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ተሰጥቷቸዋል።
የወ/ሮ ስንዱ ገብሩ የቀብር ሥነሥርዓት ዛሬ ረቡዕ ሚያዝያ 14 ቀን 2001 ዓ.ም. በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በአርበኞች የቀብር ቦታ ተፈጽሟል።
በሌላ በኩል የሙዚቃው ንጉሥ ጥላሁን ገሠሠ ሥርዓተ ቀብር ነገ ሐሙስ ሚያዝያ 15 ቀን 2001 ዓ.ም. በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ከቀኑ በ9 ሰዓት ይፈጸማል። የቀብር ሥነሥርዓቱን አስመልክቶ በወጣው ፕሮግራም መሰረት፤ ዛሬ ሌሊቱን በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ፀሎተ ፍታት ሲደረግለት ያድርና አስከሬኑ ነገ ጠዋት ወደ መኖሪያ ቤቱ ይመለሳል።
ከዚያም ከ5፡30 ሰዓት ጀምሮ አስከሬኑ ከመኖሪያ ቤቱ ወደ መስቀል አደባባይ በህዝብ አጀብ በማርሽ ባንድ ታጅቦ ይጓዛል። እስከ 8፡00 ድረስም በመስቀል አደባባይ ይቆያል። በመስቀል አደባባይ ቆይታ በማድረግ በዚያ ለሚሰበሰበው ህዝብ የሕይወት ታሪኩ የሚነበብበት፣ የሙዚቃ ሥራዎቹ ክሊፕ አደባባዩ ላይ በሚገኘው ታላቅ ስክሪን ለዕይታ የሚበቃበት ነው። በተጨማሪም የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊና የፕሬዝደንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ መልዕክቶችም ይሰማሉ። ከዚያም ከመስቀል አደባባይ ወደ ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በሠረገላ ይጓዛል። በመጨረሻም ከ9፡30 እስከ 10 ሰዓት ባለው ጊዜ ቀብሩ ይፈፀማል።
አንጋፋው ድምፃዊ ጥላሁን በ14 ዓመቱ ሙዚቃን በጀመረበት በሀገር ፍቅር ትያትር ቅጥር ግቢም በስሙ በተሰየመው አፀድ በተዘጋጀው የኀዘን መግለጫ መዝገብ ላይ በዛሬው ዕለት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች መልክቶቻቸውን ሲያሰፍሩና የአበባ ጉንጉን ሲያስቀምጡ የዋሉ ሲሆን፣ በብሔራዊ ትያትርም ማምሻውን በተዘጋጀ ፕሮግራም የሻማ ማብራት ሥነሥርዓት ተካሂዷል።



