ዝክረ ክብርት ዶ/ር ስንዱ ገብሩ
Ethiopia Zare (ሰኞ ግንቦት 3 ቀን 2001 ዓ.ም. May 11, 2009)፦ የመጀመሪያዋ ሴት የፓርላማ ተመራጭ፣ የጦር አርበኛ፣ ፀሐፊ- ተውኔት፣ ደራሲ፣ የመጀመሪያዋ ሴት ዲፕሎማት የነበሩት እና ባለፈው ሚያዝያ 12 በ93 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩትን የክብርት የዶ/ር ስንዱ ገብሩን ማንነት የሚዘክር “ዝክረ - ስንዱ ገበሬ”፣ “እናከብሮታለን!” በሚል ዝግጅት ባለፈው አርብ በእቴጌ መነን ት/ቤት ተከናወነ።
ክብርት ዶ/ር ስንዱ ገብሩ ለመላው ኢትዮጵያዊያን ታላቅ ተምሳሌት የሚሆኑ ታላቅ ሴት የነበሩ ቢሆንም፤ የመንግሥት መገናኛ ብዙኀን የቀብራቸውን ሥነሥርዓት ለጥቂት ደቂቃዎች በዜና ከማስተላፍ ውጪ አንድም ዘገባ ባለማቅረባቸው በበርካቶች ዘንድ ቅሬታን ፈጥሯል።
ይህን እሳቸውን የሚዘክረውን ዝግጅትም ያዘጋጁት በኢትየጽያ የሴቶች ማኅበራት ቅንጅት (ኢሴማቅ)፣ ከኢትዮጵያ ሴት ደራሲያን ማኅበር፣ ከኢትዮጵያ ሴት መገናኛ ብዙኀን ማኅበር፣ ከኢትዮጵያ ሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበረና፣ ከጾታዊ ጥቃት መከላከያ ማኅበር ጋር በትብብር እንደሆነ በመድረኩ ላይ ተነግሯል።
በዝግጅቱ ላይ የስንዱ ገብሩ ልጅ የሆኑት በአሜሪካ ሀገር የኢትዮጵያ አምባሣደር ሆነው በማገልገል ላይ ያሉት ዶ/ር ሳሙኤል አሰፋ፣ የወ/ሮ ስንዱ ቤተሰቦች የቀድሞው ተማሪዎቻቸው፣ የስነ-ጽሑፍ አድናቂዎቻቸው፣ አባት አርበኞች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመው ውለዋል።
ዓርብ ዕለት በተከናወነው የማስታወሻ ሥነ-ሥርዓት ላይ ድምፃዊ ፈለቀ ካሣ በክራር የወ/ሮ ስንዱን ትውስት ሲደረድር፣ አባት አርበኞች ከመቀመጫቸው እየተነሱ በቀረርቶ እና በፉከራ መድረኩን እጅግ የተዋበና የደመቀ አድርገውት ውለዋል።
በእቴጌ መነን ት/ቤት የመጀመሪያዋ ሴት ርዕሰ መምህርት ሆነው ስላገለገሉት ወ/ሮ ስንዱ ዘመድ ወዳጆቻቸው እንዲህ በማለት አስታውሰዋቸዋል፤
“… ስንዱ ገብሬ ከእቴጌ ተዋበች እና ከእቴጌ መነን ጋር ነው የሚወዳደሩት። የሚመስሉትም። ተንቀው የነበሩት ቴዎድሮስ ተዋበችን “በይ! አንቺ ወደ ቤተመንግሥት ሂጂ። እኔም ወደ አባቴ ጫካ ልሂድ” ባሉ ጊዜ “ዕድል ካንተ ጋር ናት፤ ታጠቅ!” ብለው በማነሳሳት ያነገሡት ተዋበች አይደሉም። እንዴ? እኔ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ዩኒቨርሲቲ ስማር የእቴጌ መነን ትምህርት ቤትን አጥር ተንጠልጥለን ነበር ወ/ሮ ስንዱን የምናያቸው። ፅጌረዳ የመሳሰሉ ሴት ልጆችን፣ ከእቴጌ መነን ጋር እየተነጋገሩ፣ ለሀገር እንዲበቁ ያደረጉ ውሳኔ ሰጪ ጀግና፣ የሴት አርበኛ፣ የሴት አዋቂ ናቸው። …” አንድ በቅርብ የሚያውቋቸው የታሪክ ምሁር።
“… በደርግ ጊዜ ኢትዮጵያ እንደመጣሁ ልጎበኛቸው ቤታቸው ስሄድ፣ የቤታቸው ውሃ ስልክ ተቋርጦ ነበርና ኑሮዋቸው አልጣመኝም። ተነሱ እንሂድ አልኳቸው። የት ነው የምሄደው? አሉኝ፤ በቃ ከእኛ ጋር አብረን እንኖራለን ስላቸው የተናገሩኘን ቃል አረሳትም። “እናንተ ዳሽቃችኋል፤ ሀገር የሚወደደውኮ በድሎትና በጥሩ ጊዜ ብቻ አይደለም። እናንተ በተራችሁ አሻሸላችሁ እንድንወደድ ማድረግ አለባችሁ” ነበር ያሉኝ። አንዱ ወደዚህ ሀገር ለመምጣት ምክንያት የሆኑኝ የእሳቸው ንግግር ነው” የቅርብ ዘመድ።
“… ለመፅደቅ ሲባል ቁራሽ እንጀራንና ምፅዋት በሚሠጥበት በዚያ ዘመን የእንጀራ ቁራሽ በሚል በ1953 ዓ.ም. አፍንጮ በር አካባቢ አስር የአካል ጉዳተኞችን አሰባስበው በስጋጃ፣ በጥበብ፣ በጥልፍ፣ በመሶበ ወርቅ ሥራ በቀላሉ እንደ የአካል ጉዳታቸው መሥራት እንዲችሉና ሠራተኞች እንዲሆኑ በማድረጋቸው በዓመቱ 460 አካል ጉዳተኞችን ሠራተኛ ያደረጉ ናቸው። የሴቶችን ጉዳይ በፓርላማ ብቻቸውን የተሟገቱ፣ ብቻቸውን በዚያ ዘመን ለአካል ጉዳተኞች የደረሱ ብቸኛ ኢትዮጵያዊት ናቸው። በርሳቸው ሰው መሆናችንን የምናወራላቸው ልጆቻችን ስንዱ ገብሬን ያውቋቸዋል። አልሞቱም …” የጥበብ ለኢትዮጵያ ተወካይ።
“የሴት ወንድ ስትሏት ስሰማ ነበር። እኔ የሴት ሴት እላታለሁ” ልበ ብርሃን፣ የት ነበርሽ ንጉሴ። አድናቂ።
“… የሰባት ዓመት ልጅ ሆኜ እስከ አራተኛ ክፍለ የተማርኩት መነን ነበር። በአስር እና አስራ አንድ ዓመታችን እርሳቸውን የሚያክል የተከበሩ ሴት ጋ ሄደን የግል ጉዳያችንን ስንነግራቸው እንኳን ከነልጅነታችን ያዳምጡን የነበረውን አረሳውም …” ዶክተር ጀምበር ተፈራ።
“… እናቴን አንቱ፣ አባቴን ደግሞ አንተ ነው የምለው። … አባቴን እንጂ እናቴን ወጥ ቤት ውስጥ አይቻቸው አላውቅም። ስሰማም ልጆች ሆነን የሽንት ጨርቅ፣ ምናምን አባታችን ነው የሚያጥበው። የወንዳ ወንድነት ጉዳይ ሳይሆን ቀርቶ አይደለም። እንዲያውም፤ በዚያ ዘመን የቦክስ ሻምፒዮና የነበረ ወንዳ ወንድ ነው። … እናታችን ሁለት ሴት ናቸው። በቤትና በውጪ የተለያየ ፍቅር ስለሚያሳዩን፣ እንደሰው እናት እንቀና ሁሉ ነበር። እርሳቸው ለህዝብ ልጆች ጊዜያቸውን ስለሚያጠፉ፣ ለእኛ የተለየ እንክብካቤ እንደነበራቸው አላስታውስም …” ዶ/ር አምባሳደር ሳሙኤል አሰፋ የወ/ሮ ስንዱ ገበሬ ልጅ።
“… የቤተሰብ ሕጉ በእርሳቸው ጊዜ ሲወጣ፣ የመኖሪያ ስፍራ የመምረጥን መብት በተመለከተ ለባል የተሰጠውን መብት ተከራክረው ተቀባይነት ቢያጡም የፍትሕ ብሔር ሕጉ ላይ ሴቶች ባገቡት ወንድ ስም ይጠሩ የሚለውን በመቃወም እንዳይፀድቅ ያደረጉና ያስቀየሩ ሴት ስለሆኑ ቀዳማይት ታጋይ እላቸዋለሁ። …” ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ፤ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር የቦርድ ሰብሳቢ።
“… የተፈጠሩበትን ዘመን፣ ሁኔታና አካባቢ አልፈው ዓላማቸውን ያሳኩ አንቱ ለተባለላቸው የአገልግሎቶችና የሥራ አይነቶች ከውጊያ እስከ ውሳኔ ሰጪነት በመቀመጥ ፈር ቀዳጅ ናቸው። በተቀመጡበት ሥልጣንም፣ ለተነሱበት ዓላማ ለሴቶች የእኩልነት ጥያቄ የከፈሉት አስተዋጽኦና ተግባራት በታሪክ የዘመኑ ታላቅ ሰው ያደርጋቸዋል …” ወ/ሮ ሳባ ገብረመድህን፣ የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት ዳይሬክተር።
“… ዛሬ ብቻዬን ሆኜ ያነሳሁት ጥያቄ ውድቅ ቢደረግም ወደፊት በርካታ ሴቶች የፓርላማ አባል ይሆናሉ። በዚያን ጊዜ ይሄ ጥያቄዬ ተቀባይነት ያገኛል።” ክብርት ዶ/ር ስንዱ ገብሩ፣ የፓርላማ አባላት በነበሩበት ዘመን ሴቶችን በተመለከተ በአንድ ወቅት ጥያቄ አንስተው ውድቅ ሲሆንባቸው የተናገሩት።
የሕይወት ታሪክ (1908 - 2001 ዓ.ም.)
ወ/ሮ ስንዱ ገብሩ በሸዋ ክፍለ ሀገር በመናገሻ አውራጃ በአዲስ ዓለም ከተማ ጥር 6 ቀን ውስጥ በ1908 ዓ.ም. ተወለዱ። ዕድሜያቸው ለትምህርት በደረሰበት ወቅት እቤታቸው አስተማሪ ተቀጥሮላቸው የአማርኛን ትምህረት ከፊደል መቁጠር እስከ ዳዊት መድገም በቤታቸው ተማሩ። ከዚያም ወደ አዲስ አበባ ሄደው በስዊድን ሚሲዮን ትምህርት ቤት በመግባት እስከ ስምንተኛ ክፍል ተምረዋል።
በ1921 ዓ.ም. ወደ ስዊዘርላንድ ለትምህርት ቢሄዱም ኑሮ ስላልተመቻቸውና ትምህርት ይሰጥበት የነበረውን የጀርመንኛ ቋንቋ ስላልወደዱት ወደ ፈረንሣይ አቅንተው ትምህርታቸውን ቀጠሉ። በመጨረሻም በስዊዘርላንድና በፈረንሣይ ሁለት ትምህርት ቤቶች በመዘዋወር በዲፕሎማ ተመረቁ። እዛው የሕግ ትምህርት ለመቀጠል ጀምረው የነበረ ቢሆንም፤ ፍላጎታቸው ወደ ሥነ-ጽሑፍ በማዘንበሉ በአጠቃላይ ለአምስት ዓመታት እዛው ተምረው ወደ ሀገራቸው ተመለሱ።
ወደ ሀገራቸው እንደተመለሱም በአዲስ አበባ በቅዱስ ጊዮርጊስ ትምህርት ቤት ውስጥ የፈረንሣይኛ ቋንቋን፣ ሃይጅን፣ ቁጥርንና የአማርኛ ድርሰት አጻጻፍን ማስተማር ጀመሩ። በዚህ ሁኔታ አንድ ዓመት እንደቆዩ ለብላታ ሎሬንሶ ትዕዛዝ ተዳሩና ባለቤታቸው የሐረርጌ ክፍለሀገር አስተዳዳሪ ሆነው በመሾማቸው ወደዚያው ከባለቤታቸው ጋር አቀኑ። ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላም ብላታ ሎሬንሶ የፍርድ ቤት ሹምና የዜና ስርጭት ኃላፊ ሆነው በመሾማቸው ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ አብረዋቸው ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ።
ፋሺስቶች ኢትዮጵያን በወረሩ ጊዜ ጃንሆይ (አፄ ኃይለሥላሴ) ወደ እንግሊዝ ሀገር ሲሰደዱ የወ/ሮ ስንዱ ባለቤትም አብረው ከጃንሆይ ጋር ሄዱ። ወ/ሮ ስንዱ ግን ከቤተሰቦቻቸው ጋር እና ሆለታ ውስጥ ከሚገኙ ወደ መቶ የሚጠጉ የጦር መኮንኖች ጋር ተቀላቅለው ፋሺስቶችን ለመፋለም ወደ ቦሬ ሄዱ። እዚያም የመትረየስ አተኳኮስ ትምህርት ተማሩ።
ወደ ነቀምት በመሄድም ህዝብን እየሰበሰቡ ስለነፃነት ማስተማሩን ተያያዙት። በዚህ ወቅት በባንዳዎች ጠቋሚነት በፋሽስት እጅ ከመውደቅ ለጥቂት አምልጠው ጎሬ ላይ ከራስ እምሩ ጦር ጋር ተቀላቀሉ። ከዚያም በጦርነቱ የሚጎዱ አርበኞችን ለማከም የሚሆን ቀይ መስቀል ለማቋም መፈለጋጀውን ለራስ እምሩ ሲያማክሯቸው 500 ብር ስለሰጧቸው አቋቁመው አርበኞችን መርዳት ጀመሩ።
እርሳቸው ተቀላቅለውት የነበረው የጥቁር አንበሳ ጦር ሲመታ በመማረካቸው ጣሊያኖች አስረው ወደ አዲስ አበባ አመጧቸውና የቁም እስረኛ ሆኑ።
የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. ግራዚያኒን ለመግደል በተደረገ ሙከራ ወንድማቸው መሸሻ ገብሩ አሉበት በመባሉ ይታሰሱ ስለነበር ወንድማቸውን ከአደጋ ለማዳን ሲፈልጉ በድጋሚ በፋሺስቶች እጅ ወደቁ። በወቅቱ ግራዚያኒ ይኖርበት የነበረው የጃንሆይ ቤተመንግሥት ታሰሩ። ቀጥሎም ወደ አስመራ፣ ከዚያ ወደ ምጽዋ ተወሰዱ። ከምጽዋ ወደብ ሦስት መቶ ወንዶችና ስምንት ሴቶች ሆነው በመርከብ “አዚናራ” ወደተባለች የኢጣሊያኖች እስር ቤት ተወስደው ዘጠኝ ወራት ታሰሩ።
ከእስር በኋላም ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ በእንደዚህ ያለ ተግባር ላይ እንዳይሰማሩ ከፍተኛ ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም፤ ማስፈራሪያው ሳይበግራቸው አርበኞችን በግጥም፣ በወኔ ቀስቃሽ ጽሑፎች በማበረታታት፣ መረጃ በማቀበል፣ መሣሪያ በማዳረስ የጀግንነት ተግባር ፈጽመዋል።
ከድል በኋላ ወ/ሮ ስንዱ ለሁለት ዓመታት ደሴ ከተማ የሚገኘው የወ/ሮ ስህን ትምህርት ቤት ዳይሬክተር በመሆን፣ ወደ አዲስ አበባ ተመልሰውም እቴጌ መነን ትምህርት ቤት ም/ርዕሰ መምህርነት፣ ከዚያም ዳይሬክተር ሆነው አገልግለዋል።
በእቴጌ መነን ትምህርት ቤት በነበሩበት ወቅት፤ “ኮከብ ያለው ያበራል ገና”፣ “የየካቲት ቀኖች”፣ “የኑሮ ስህተት” የሚሉ ትያትሮችን ሠርተው አቅርበዋል።
ከ1948 ዓ.ም. እስከ 1952 ዓ.ም. ድረስ የመጀመሪያዋ የሴት የፓርላማ የሕግ መምሪያ ምክር ቤት አባልና የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ም/ሊቀመንበር ሆነው አገልግለዋል።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ፕሬዝዳንት፣ የህዝባዊ ኑሮ ዕድገት ዋና ፀሐፊነትና አስተዳዳሪነት፣ በምዕራብ ጀርመን ለሦስት ዓመት የትምህርት አታሼ በመሆን አገልግለዋል። ወ/ሮ ስንዱ ከ10 በላይ መጻሕፍት የጻፉና፣ ስድስት ስክሪፕቶችን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማስቀመጣቸውም ታውቋል።
ወ/ሮ ስንዱ ላበረከቱት አስተዋጾ የወርቅ ሜዳሊያ፣ የንግሥት ሣባ የወርቅ ኒሻን፣ የቀይ መስቀል የወርቅ ሜዳሊያ እና በኢህአዴግ ዘመን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ተሰጥቷቸዋል።
የመጀመሪያዋ የሴት የፓርላማ አባል፣ ቀዳሚዋ የሴት ገጣሚ፣ ተውኔት ፀሐፊ፣ መጽሐፍ ደራሲ፣ ዲፕሎማት፣ የትምህርት ባለሙያ፣ ፖለቲከኛ እና እናት አርበኛ ወ/ሮ ስንዱ ገብሩ (የክብር ዶክተር እና የከንቲባ ገብሩ ደስታ ልጅ) ሰኞ ሚያዝያ 12 ቀን 2001 ዓ.ም. በ93 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም ተለይተዋል። የቀብር ሥነሥርዓታቸው ረቡዕ ሚያዝያ 14 ቀን 2001 ዓ.ም. በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በአርበኞች የቀብር ቦታ ተፈጽሟል።



