Ethiopia Zare (ማክሰኞ ሚያዝያ 13 ቀን 2001 ዓ.ም. April 21, 2009)፦ በአጼ ኃይለሥላሴ የሥልጣን ዘመን የፓርላማ አባል፣ በሀገር ሸምግሌዎች ህብረት ውስጥ ተካትተው የቅንጅት አመራሮችን ለማስፈታት በተደረገው ጥረት ተሳትፎ የነበራቸው የ89 ዓመቱ ታዋቂው ነጋዴ ፊታውራሪ አመዴ ለማ ዛሬ ማክሰኞ ሚያዝያ 13 ቀን 2001 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።

 

በደርግ ዘመነ መንግሥት የተቀሙት በመርካቶ የሚገኘው “አመዴ ገበያ” በመባል የሚጠራው ትልቁ የገበያ አዳራሽ ባለቤትና “የሀገር ሽማግሌ” ተብሎ ሲጠራ በቀዳሚነት ስማቸው የሚነሳው ፊት አውራሪ አመዴ ለማ፤ በትናንትናው ዕለት በድንገት መታመማቸውንና ሆስፒታል ወስደው እንደመለሷቸው ልጃቸው ገልጾ፤ በዛሬው ዕለት ሐያት ሆስፒታል ወስደዋቸው እዛው ማረፋቸውን ገልጧል።

 

የፊታውራሪ አመዴ ለማ የቀብራቸው ሥነሥርዓትም በነገው ዕለት (ረቡዕ ሚያዝያ 14 ቀን 2001 ዓ.ም.)  ከቀኑ በሰባት ሰዓት ኮልፎ በሚገኘው የሙስሊም መቃብር እንደሚፈፀም ታውቋል።

 

ፊታውራሪ አመዴ ለማ የ89 ዓመት አዛውንት ሲሆኑ፣ 10 ልጆች፣ 34 የልጅ ልጆች እና 6 የልጅ ልጅ ልጆች አሏቸው።

 

በተያያዘም በ1908 ዓ.ም. የተወለዱት የመጀመሪያዋ የሴት ፓርላማ አባል፣ የሴት የሰብዓዊ መብት ተሟጋች፣ ጀግናና ፀረ-ፋሺስት አርበኛ፣ ፀሐፊ ተውኔት፣ የመጽሐፍ ደራሲ፣ እና የመጀመሪያዋ የሴት ዲፕሎማት ስንዱ ገብሩ (የክቡር ዶክተር) ሰኞ ሚያዝያ 12 ቀን 2001 ዓ.ም. ሕይወታቸው ማለፉ ታውቋል።

 

ዲፕሎማት ስንዱ ገብሩ የ93 ዓመት ዕድሜ ባለፀጋ የነበሩ ሲሆን፣ የቀብራቸው ሥነሥርዓት በነገው ዕለት (ረቡዕ ሚያዝያ 14 ቀን 2001 ዓ.ም.) በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተክርስቲያን ይፈጸማል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ