ሦስት ሰዎች ታሰረዋል፤ ከግንቦት 7 ጋር ይጠረጠራል

Ethiopia Zare (እሁድ ግንቦት 23 ቀን 2001 ዓ.ም. May 31, 2009)፦ የአዲስ ብሮድካስቲንግ ኤጀንሲ ንብረት የነበረ የ7 ሚሊዮን ብር የራዲዮ ስቱዲዮ መሣሪያ ከትናንት በስቲያ በመንግሥት ኃይሎች ውርስ ተደረገ። ግንቦት 20 ማታ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በተሠራጨ ዜና ንብረቱ የተወረሰው “በሕገ ወጥ መንገድ የገባ በመሆኑ ነው” ተብሏል።

 

የድርጅቱ የቅርብ ሰው እንዳስረዱት፤ የድርጅቱ ንብረት ሊወረስ የቻለው የመንግሥት ተቃዋሚ በሆኑ ሰዎች የተቋቋመ በመሆኑ ሲሆን፣ “መንግሥት ድርጅቱን በቅርብ እየከሰሰ ካለው የግንቦት 7 ድርጅት ጋር አያይዞ የፕሮፖጋንዳ ፍጆታ ሊያደርገው ይሆናል” ብለዋል።

 

ድርጅቱ ፕሮፌሠር መስፍንን ጨምሮ በዶ/ር ብርሃኑ፣ በዶ/ር በፍቃዱ ደግፌ፣ በዶ/ር ሽመልስ ተ/ፃዲቅ እና 30 በሚሆኑ ባለአክሲዮኖች ተቋቁሞ ለ7 ዓመታት የሚዲያ ፍቃድ ሳይሰጠው ቆይቷል። ድርጅቱን በአደራ ይመራው የነበረው የቪኦኤ ዘጋቢ መለስካቸው አምሃ ሲሆን፣ ሥልጣኑን በቅርቡ ለወ/ሮ አመለወርቅ ታደሰ አሳልፎ ነበር።

 

ንብረቱ በተወረሰበት ዕለት ግን ሁለቱ ኃላፊዎችና የንብረት ክፍል ሠራተኛ የሆነው አቶ ደመቀ ጌቱ በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ተደርገዋል። ወ/ሮ አመለወርቅ የአዲስ ፊልም ፕሮዳክሽን ሥራ እስኪያጅ ከመሆናቸው ባሻገር በኤቢሲ ቢሮ ውስጥ ዶክመንተሪ ፊልሞችን በመሥራት ለህዝብ ያቀርቡ ነበር። በአሁን ወቅት ቢሮው በታጣቂዎች መከበቡንና የአዲስ ፊልም ፕሮዳክሽን ንብረቶችንም ማውጣት እንዳልተቻለ ሠራተኞቹ ገልጸዋል።

 

ኤቢሲ 3.5 ሚሊዮን ብር የባንክ ዕዳ ያለበት ሲሆን፣ ሥራውን ሠርቶ ገንዘቡን መክፈል አልቻለም። ከኖርዌይ ባለሙያዎች መጥተው የተከሉትን የስቱዲዩ መሣሪያ ያለዕውቀት ታጣቂዎች ፈታተው በፌዴራል መኪና ጭነው ወስደውታል፤ ያሉ የፊልም ፕሮዳክሽን ሠራተኞች፤ “ንብረቱ በጥንቃቄ ጉድለት ከአገልሎት ውጪ መሆኑ አይቀርም” በማለት ስጋታቸውን ገልጸዋል።

 

በሕጋዊ መንገድ የገባውን ንብረት ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ፈታተው መውሰዳቸው ሳያንስ ያለ ሕጋዊ ማስረጃና ድጋፍ በመንግሥት ቴሌቪዥን ንብረቱ “በሕገወጥ መንገድ የገባ ነው” ማለታቸው ግምት ውስጥ ይጥላቸዋል ያሉ አንድ ሠራተኛ “ከ7 ዓመት በኋላ ሕገ ወጥ ነው ማለት ለምን አስፈለገ?” በማለት ምላሽ የሌለው ጥያቄ ጠይቀዋል።

 

ይህ በእንዲህ እንዳለ በጠበቃ አበበ ወርቄ የሚመራው የኤቢሲ ቦርድ ማምሻውን ስብሰባ ያደረገ መሆኑ ታውቋል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ