ወ/ት ብርቱካን የምትፈታበት ተስፋ እንዳለ የሀገር ሽማግሌዎቹ ገለጹ
Ethiopia Zare (አርብ ሚያዝያ 23 ቀን 2001 ዓ.ም. May 1, 2009)፦ የሚመራው የሀገር ሽማግሌዎች ቡድን ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በታሰረች በአራት ወር ከአራት ቀናቸው ዛሬ ማምሻውን ከ10፡10 ሰዓት በኋላ በአዲስ አበባ በሸራተን ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጠ። በመግለጫቸው ላይ የሽምግልና ዝርዝር ሂደቱን ለመግለጽ ፈቃደኞች ያልነበሩ ሲሆን፤ ወ/ት ብርቱካን የምትፈታበት ተስፋ እንዳለ ገልጸዋል።
በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ከአስር በላይ የሚሆኑ የሀገር ሽማግሌዎች ቡድኑ አባላት የተገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ ፕ/ር ኤፍሬም፣ አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴ፣ አቶ ታምሩ ወንድማገኘሁና ሌሎችም ተገኝተዋል። ፓስተር ዳንኤል ግን አለመገኘታቸውን የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገልጸዋል።
የቡድኑ አባላት ትናንት በጽሑፍ ያወጡትን መግለጫ አንብበው እንደጨረሱ በስፍራው የተገኙ ቁጥራቸው ከስምንት የማይበልጡ ጋዜጠኞችን ሊያሰናብቱ የነበረ ቢሆንም፣ ጋዜጠኞቹ ጥያቄ ለመጠየቅ እንደሚፈልጉ በመግለፃቸው፤ የሽማግሌዎቹ ቡድን የጋዜጠኞቹን ጥያቄዎች ለማስተናገድ ተገድዷል።
“ይሄ ከሁለት ዓመት በፊት የተፈጠረ ነገር ነው፤ እኛ ወደፊት ነው መሄድ የምንፈልገው፤ ወደ ኋላ መሄድ አንፈልግም። ሁሉንም ነገር በዚህ መግለጫ ላይ ገልፀናል። ያኔም ቢሆን ሽምግልናውን እንደፈፀምን በቴሌቭዥን መግለጫ ሰጥተናል፤ ያንን ማየታችሁ በቂ ነው። እኛ አሁን ምንም የምንለው ነገር የለንም። ሁሉንም በዚህ በመግለጫችን ላይ ያልነው ነገር ነው። እሷን ለማስፈታት ጥረት እያደረግን ነው። ጥረታችንን እንቀጥላለን።” በማለት የሀገር ሽማግሌዎቹ በጋዜጣዊ መግለጫው ለመግለጽ ሞክረዋል።
የነበረውን ሂደት ለምን በግልጽ አትናገሩም? በሚል ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱም፤ “እኛ ወሬኞች አይደለንም፤ በሽምግልና ሂደት ውስጥ የነበረውን ነገር ወጥተን የምናወራው። ወደኋላ ተመልሰን ከመናገር ይልቅ፤ ወደፊት አሁን የተፈጠረው ችግር የሚፈታበትን መንገድ መፈለግ ነው የሚሻለው፤ እናም ወደሱ ነገር ነው የምንሄደው። ...” ሲሉ መልስ ሰጥተዋል።
“ወ/ት ብርቱካን በተናገረችው ነገር ጥፋተኛ ነች አይደለችም የሚለውን ነገር በግልጽ ንገሩን፤ ምክንያቱም እናንተ በሽምግልናው ሂደት ውስጥ ነበራችሁና” በማለት ከአንድ ጋዜጠኛ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ “እኛ ዳኛ አይደለንም፤ “እገሌ ጥፋተኛ ነው፣ አይደለም” የምንለው። እኛ ሥራችንንና የግል ነገራችንን ትተን እዚህ ውስጥ የገባነው ለኢትዮጵያ ሠላም ብለን ነው። አሁንም ቢሆን እሷ የምትፈታበትን መንገድ እንፈልጋለን እንጂ፤ “እገሌ ጥፋተኛ ነው አይደለም” አንልም።” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።
“እናንተ ትልልቅ ሰዎችና የሀገር ሽማግሌዎች ናችሁ፤ በዕድሜም የገፋችሁ ናችሁ፤ አባቶቻችን ትሆናላችሁ። የሀገር ሽማግሌ ማለት ሁለት ወገኖችን አስማምቶ የሚያስታርቅ ነው። ካስታረቀም በኋላ በነበረው የሽምግልና ሂደት ችግር ቢፈጠር አለመስማማቶች ሲፈጠሩ ግልጽ አውጥቶና ወደኋላ ተመልሶ የሚያስማማ ነው። እናንተ ደግሞ የያዛችሁት የባልና ሚስት ጉዳይ ሳይሆን የሀገር ጉዳይ ነው። ፖለቲካዊ ጉዳይ ነው። የሀገር ጉዳይ ደግሞ ህዝብንም ይመለከተዋል። ስለዚህ በዚያ ሂደት እናንተ ገብታችሁ ያዋጣናል ብላችሁ ሄዳችሁ መጨረሻ ላይ እንዲህ ያለ ችግር ሲፈጠር የነበረው የሽምግልና ሂደት እንደዚህ ነበር ብላችሁ ብትሉ፤ “ማነው ትክክል? መንግሥት ነው ወይስ ወ/ት ብርቱካን?” የሚለውን ነገር በግልጽ ማየት ይቻላል። ወ/ት ብርቱካን አስተባብይ ሲባሉ፤ “ቃሌ” በሚለው ጽሑፍ የሽምግልና ሂደቱን ገልጸዋል። እገሌ ትክክል ነው አይደለም ለማለት ይከብደናል የምትሉ ከሆነ የነበረውን የሽምግልና ሂደት ብትገልጹት ማን ትክክል እንደሆነ ህዝቡ ማወቅ ይችላል።” በማለት ተብራርቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ “... እኛ የሀገር ሽማግሌዎች እንጂ ወሬኞች አይደለንም። “እንዲህ ነበር እንዲህ ነበር አንልም፤ ሁልጊዜም ጥረታችን ለሠላም ነው። ...” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።
“በሽምግልናው ሂደትስ ልትፈታ ትችላለች ብላችሁ ታስባላችሁ? ተስፋ እናድርግ?” በሚል ከአንድ ጋዜጠኛ ለተሰነዘረ ጥያቄ፤ አዎ! ተስፋ ማድረግ ይቻላል ሲሉ የሀገር ሽማግሌዎቹ ምላሽ ሰጥተዋል።
የሀገር ሽማግሌዎቹ ትናንት በጽሑፍ በሰጡት መግለጫ ላይ “ወ/ት ብርቱካን እንዲያስተባብሉ ለምነናቸው ነበር” የሚለውን በመንተራስ ከጋዜጠኞች አንዱ፤ “እንዲያስተባብሉ የተባሉት ወ/ት ብርቱካን የተናገሩት ውሸት ነው ማለት ነው ወይ?” ሲል ላቀረበው ጥያቄ፤ “እኛም እንግዲህ እናንተ እንደሰማችሁት መታሰራቸውን ከሰማን በኋላ፤ ከመንግሥት ወገን እንዲያስተባብሉ አናግሯቸው አሉን፤ አናገርናቸው ... በቃ ይሄንን ነው የምናውቀው” በማለት አጥጋቢ ያልሆነ ምላሽ ሰጥተዋል።
የሀገር ሽማግሌዎቹ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የተድበሰበሱና ያልተፍታቱ ምላሾችን ሲሰጡ የነበረ ሲሆን፤ ለጋዜጠኞቹ “እናንተ የምትሉትን ዝርዝር ጉዳይ ወደፊት ልንገልጽ እንችላለን” ብለዋል።
የሀገር ሽማግሌዎቹ እኛ ሽማግሌዎች ነን፤ እናንተ ጋዜጠኞች ናችሁና፤ እናንተም የምትሉትን እንቀበላለን በማለት፤ ጋዜጠኞቹ አስተያየት እንዳላቸው ጠይቀዋል። ይህንን ተከትሎ አንድ ጋዜጠኛ “ከዚህ በኋላ የምታደርጉት የሽምግልና ሂደት ግን የአንዱን ወገን ብቻ የበላይነት ያረጋገጠ መሆን የለበትም። ሁለቱንም ወገኖች እኩል ነው ማስተናገድ ያለባችሁ።” በማለት ማሳሰቢያ አዘል አስተያት ሰጥቷል።
በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ብዙውን ንግግር የተናገሩት፣ ለተሰነዘሩት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የሞከሩት ፕ/ር ኤፍሬም ይስኃቅ የነበሩ ሲሆን፣ የሕግ ባለሙያው አቶ ታምሩ ወንድማገኘሁም ጥቂት ተናግረዋል። አትሌት ኃይሌ ወደ መጨረሻ ላይ “ጋዜጠኞችም ኃላፊነት አለባችሁ፤ የምታስተካክሉት ነገር እንዳለ ሁሉ የምታበላሹትም ነገር ስላለ፤ ኃላፊነት ባለው ሁኔታ ሥሩ” ማለቱን የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገልጸዋል።
በዚህ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የሀገር ሽማግሌዎቹ መሪ የሆኑት ፕ/ር ኤፍሬም ጋዜጠኞቹን “ወሬ ለማሻሻጥ ነው የምትፈልጉት” በሚል ለመውረፍ መሞከራቸውን የገለጹት የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች፤ ከጋዜጠኞቹ አንዷ “እንዲህ እያላችሁ በተደጋጋሚ ጋዜጠኞችን መወረፋችሁ ተገቢ አይደለም። እኔ በግሌ ፕሮፌሽናል ጋዜጠኛ ነኝ፤ የሙያ ሥነምግባሩም ይህንን እንድናደርግ አይፈቅድልንም። ሙያዬን አክብሬ ነው የምሠራው። እንደዚህ በተደጋጋሚ ማለታችሁ ክብራችንን የሚነካና ሙያችንን የሚያዋርድ ነው። እናም ከዚህ ተግባራችሁ እንድትታቀቡ!” ማለቷን ገልፀዋል።
እንደ ምንጮቻችን ገለጻ ከሆነ፤ ፕ/ር ኤፍሬም “ሌሎች ሲሉ ሰምቼ ነው፤ ለምዶብኝ ነው ... ይቅርታ! ... ይቅርታ! ...” በማለት ጋዜጠኞቹን በተደጋጋሚ ይቅርታ ጠይቀዋቸዋል። በመጨረሻም ፕሮፌሠሩ ጋዜጣዊ መግለጫው በተጀመረ 40ኛው ደቂቃ ላይ በስፍራው የተገኙትን ከመቀመጫቸው እንዲነሱ በመጠየቅ ጋዜጣዊ መግለጫውን በፀሎት መዝጋታቸውን የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገልፀዋል።



