ከግንቦት 7 ጋር በተያያዘ ከ46ቱ ተከሳሶች በእስር የሚገኙት 32ቱም ይከላከሉ ተባሉ፣

በሌሉበት ከተከሰሱት 13ቱ ጥፋተኛ ተባሉ

Ethiopia Zare (ሐሙስ ሐምሌ 30 ቀን 2001 ዓ.ም. August 6, 2009)፦ ዛሬ ሐሙስ ሐምሌ 30 የዋለው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 2ኛ ወንጀል ችሎት፤ ከግንቦት 7 ጋር በተያያዘ ክስ የተመሰረተባቸው ተከሳሾች ውስጥ የግንቦት 7 መሥራቾችና መሪዎች በሆኑት በእነ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ እና በአቶ አንደርጋቸው ጽጌ ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ ሰጠ። በእስር ላይ ከሚገኙት 32 ተከሳሾች ውስጥ 29ኙን በቀረቡባቸው 5ቱም ክሶች እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል።

 

ከግንቦት 7 ንቅናቄ ጋር በተያያዘ ግንቦት 25 ቀን 2001 ዓ.ም. ዓቃቤ ሕግ ክስ ከመሰረተባቸው 46 ግለሰቦች ውስጥ ጉዳያቸው በሌሉበት እየታየ ካሉት 14 ግለሰቦች ውስጥ 13ቱን ፍርድ ቤቱ በተከሰሱበት 5ቱም ክሶች የጥፋተኝነት ፍርድ ሰጥቷል። ከእነዚህም ውስጥ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ እና አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ይገኙበታል። ዓቃቤ ሕግ የቅጣት ሃሳቡን ለነሐሴ 7 ቀን 2001 ዓ.ም. እንዲያቀርብ ውሳኔ የሰጠው ፍርድ ቤቱ፤ በ13ቱ ግለሰቦች ላይ ፍርድ ለመስጠትም የፊታችን ነሐሴ 19 ቀን 2001 ዓ.ም. ቀጥሯል።

 

አቶ አማኑኤል የተባሉና በሌሉበት የተከሰሱት ግለሰብ ደግሞ በቂ ማስረጃ ስላልቀረበባቸው መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ እንዲሰናበቱ ሲል ፍርድ ቤቱ በይኗል።

 

ፍርድ ቤቱ በእስር ቤት ሆነው ጉዳያቸው እየታየ ካሉት 32 ግለሰቦች ውስጥ ብርጋዴር ጄነራል ተፈራ ማሞ፣ ሌተናል ኮሎኔል ደምሰው አንተነህ እና የ80 ዓመቱ አዛውንት አቶ ጽጌ ኃብተማርያምን ጨምሮ 29ኙ ተከሳሾች በተመሰረቱባቸው 5ቱም ክሶች በእስር ሆነው እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል። ፍርድ ቤቱ ዓቃቤ ሕግ ያቀረባቸውን 88 የሰው ምስክሮች፣ የተለያዩ የድምፅና የቪዲዮ ማስረጃዎች፣ 1556 ገጽ የሰነድ ማስረጃ፣ ለፖሊስ እና ለፍርድ ቤት በሰጡት የእምነት ክህደት ቃል መርምሮ ብይኑን መስጠቱን በዝርዝር አሰምቷል።

 

በእስር የሚገኙትን ቀሪዎቹን ሦስቱ ተከሳሾች በማስረጃ ተረጋግጦባቸዋል ብሎ ፍርድ ቤቱ ባመነውና ቀለል ያለ ቅጣት ሊያስቀጣቸው በሚያስችል ወንጀል እንዲከላከሉ በይኖባቸዋል። የሦስቱ ግለሰቦች ጠበቆች የደንበኞቻቸው የዋስትና መብት እንዲከበርላቸው በጠየቁት መሰረት፤ እያንዳንዳቸው ሦስት - ሦስት ሺህ ብር ለዋስትና አስይዘው ከእስር ነፃ ሆነው እንዲከላከሉ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

 

ፍርድ ቤቱ በእስር ሆነው እንዲከላከሉ የበየነባቸው 29ኙ ግለሰቦችና ሦስቱ በዋስትና ከእስር ቤት ውጭ ሆነው እንዲከላከሉ የበየነባቸውን፣ በድምሩ  32ቱን ተከሳሾች መከላከያዎቻቸውን ከነሐሴ 19 ቀን ጀምሮ እንዲያቀርቡ ቀጥሯቸዋል።

 

“በኅቡዕ በመሰባሰብና ከግንቦት 7 ሕገ ወጥ ቡድን ጋር ግንኙነት በመፍጠር ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ላይ አደጋ ለመጣል፣ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ለመግደል፣ ተቋማትን ለማውደም፣ በመከላከያ ኃይል ላይ ጉዳት ለማድረስ፣ …” በሚሉት አምስቱም ክሶች እንዲከላከሉ የተፈረደባቸውና በእስር የሚገኙት ግለሰቦች የሚከተሉት ናቸው።

 

ብርጋዴር ጄነራል ተፈራ ማሞ፣ ሌተናል ኮሎኔል ደምሰው አንተነህ፣ ሌተናል ኮሎኔል አበረ አሰፋ፣ ሌተናል ኮሎኔል ዓለሙ ጌትነት፣ ሌተናል ኮሎኔል ፋንታሁን ሙሃባ፣ ሌተናል ኮሎኔል ሠለሞን አሻግሬ፣ ሌተናል ኮሎኔል ጌታቸው ብርሌ፣ ሻለቃ አደፍርስ አለማየሁ፣ ሻለቃ መኮንን ወርቁ፣ ሻለቃ አዱኛ አለማየሁ፣ ሻለቃ መሰከረ ካሣ፣ ሻለቃ ምስጋናው ተሰማ፣ ሻለቃ ፋናዬ ውቤ፣ ሻምበል ተመስገን ባይለየኝ፣ የመቶ አለቃ አባቡ ተፈሪ፣ ሳጅን ውደነህ ተመስገን፣ ዋና ሳጅን አመራር ባያብል፣ ምክትል ሳጅን ጎበና በላይ፣ ረዳት ምክትል ሳጅን የሺዋስ ምትኩ፣ ሳጅን ይበልጣል ብርሃኑ፣ አቶ አሳምነው ጽጌ፣ አቶ ክፍሌ ስንሻው፣ አቶ የሺዋስ መንገሻ፣ አቶ መንግሥቱ አበበ፣ ወይዘሮ እማዋይሽ ዓለሙ፣ አቶ ጎሽይራድ ፀጋው፣ አቶ መላኩ ተፈራ፣ አቶ ጌቱ ወርቁ እና አቶ ጽጌ ኃብተማርያም (የ80 አዛውንት የሆኑት የግንቦት 7 መሥራችና መሪ የሆኑት የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ወላጅ አባት) ናቸው።

 

በሦስት ሺህ ብር ዋስትና ከእስር ቤት ውጭ ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከላከሉ የተበየነባቸው ደግሞ ኢንስፔክተር አራጋው አስፋው ረታ፣ ሳጅን አይተን ካሣ መኰንን እና አቶ ጌቱ ወልዴ አባሆይ ናቸው።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ