Weekly digest, 8th 2012 Eth. C

ከጥቅምት 17 - 23 ቀን 2012 ዓ.ም. የሳምንቱን አንኳር ወሬዎች በጨረፍታ

አዴፓና አምስት ፓርቲዎች በጋራ ለመሥራት መስማማት

ኢዛ (ከጥቅምት 17 - 23 ቀን 2012 ዓ.ም.)፦ አዴፓን (የአማራ ዴሞክራቲክ ፓርቲ) ጨምሮ አማራን ማዕከል አድርገው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ያደረጉት ባሳለፍነው ሳምንት ነበር።

በጋራ ለመሥራት ጥምረት የፈጠሩት የፖለቲካ ፓርቲዎች አዴፓ፣ አብንና የአምስት የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጥምረት የያዘው የአማራ ድርጅቶች ናቸው።

ስምምነቱን በተመለከተ የወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ የአማራ ሕዝብ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጥቅሞች እንዲረጋገጡ፤ ከክልሉ ውጭ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች የሚደርስባቸውን በደል ለማስቆም፣ መብትና ጥቅማቸውን ለማስከበር ፓርቲዎቹ በጋራ የሚሠሩ ሲሆን፤ የአማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎችና ጥቅሞች ምላሽ እንዲያገኝም በጋራ ለመሥራት ተስማምተዋል። ከዚህ ቀደም የኦሮሚያ ላይ ትኩረት ያደረጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተመሳሳይ ስምምነት ማድረጋቸው አይዘነጋም።

ግዙፉ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት በአዲስ አበባ

ባሳለፍነው ሳምንት ከኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ውስጥ ጐልቶ የሚጠቀሰው በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ይፋ የኾነው የቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት የመሠረት ድንጋይ መቀመጥ ነው። በአዲስ አበባ በዘጠኝ ክፍለ ከተሞች ከ22 ሺሕ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ለማስጀመር የመሠረት ድንጋይ በማስቀመጥ ግንባታዎቹን ያስጀመሩት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂንየር ታከለ ኡማና ሌሎች የከተማ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች ናቸው።

እነዚህ በየክፍለ ከተማው የሚገነቡት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ከ1740 በላይ ጥቃቅንና አነስተኛ ማኅበራት የሚሳተፉበት ሲሆን፣ ከ52 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ዜጐች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር የቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽ/ቤት አስታውቋል።

በ20/80 እና በ40/60 የቤት ልማት መርኀ ግብር የሚከናወኑ ይሆናል። በእነዚህ የቤቶች ፕሮጀክት ግንባታ በይፋ ከተጀመረባቸው ቦታዎች አንዱ በኾነው የተገኙት ኢንጂንየር ታከለ ኡማ እንደተናገሩት፤ ከስድስት ወሮች በላይ በከተማዋ ያለምንም ግንባታ መሬት አጥሮ ማስቀጥ የማይቻል ስለመሆኑ ነው።

ከስድስት ወሮች በላይ መሬት አጥሮ የሚያስቀምጥ ማንኛውም አካል ከተገኘ፤ መሬቱ እንደሚወረስበትም አጥብቀው ተናግረዋል። ሀብት የሚባክንበት ወቅት ስለማለፉ ያመለከቱት ምክትል ከንቲባው፤ በመንግሥትና በባለሀብት ግንባታ ሳይካሄድባቸው የቆዩ መሬቶችን የመለየት ሥራ በጥናት የተሠራ መሆኑንም በማስታወስ፤ እነዚህ ግንባታ አልባ የሆኑ ቦታዎችን በመውሰድ ወደ መሬት ባንክ የመመለስ ሥራ ይሠራል ብለዋል። ይህም እርምጃ በቅርቡ የሚከናወን መኾኑን ያመለከቱት ኢንጂነሩ፤ ያለሥራ ሰፋፊ ቦታዎችን አጥሮ ማስቀመጥ ከዚህ በኋላ አይቻልም የሚለውንም መልእክታቸውን አክለዋል።

በዕለቱ ግንባታቸው የተጀመሩት ፕሮጀክቶች በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የሚወጣቸው ሲሆን፣ ለአብነት ያህልም በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የሚገነባው የጋራ መኖሪያ ቤት ከ5 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ይጠይቃል። በአሁኑ ወቅት በጋራ መኖሪያ ቤቶች ምዝገባ ያደረጉ ከ600 ሺሕ በላይ ነዋሪዎች አሉ ተብሏል።

ከከንቲባው ንግግር መረዳት እንደተቻለው አስተዳደሩ በከተማ ውስጥ 600 ሺሕ ቤቶችን ለመገንባት እቅድ የያዘ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 150 ሺሕ የሚሆነው በአስተዳደሩ የሚገነባ ሲሆን ቀሪው በባለሀብቶች፣ በመንግሥትና በባለሀብቶች እና በመሳሰለው መንገድ የሚገነባ ነው። አሁን አስተዳደሩ ባስጀመራቸው የጋራ ቤቶች ግንባታ ላይ ወደ 28 ኮንትራክተሮች ተሳታፊ የሚሆን ሲሆን፣ የግንባታው ሒደትም ከዚህ ቀደም ይካሄድ ከነበረው በተለየ የሚከናወን ነው ተብሏል።

የሽግግር መንግሥት ይቋቋም ጥያቄ

ወቅታዊውን የአገሪቱ ችግር ተንተርሶ የኢትዮጵያውያን አገር አቀፍ ንቅናቄ ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግሥት መቋቋም አለበት በማለት ገለጸ። የንቅናቄው መሪ ኢንጂንየር ይልቃል ጌትነት በሰጡት መግለጫ፤ የዜጐችን ደኅንነትና የአገር ሕልውና በመታደግና ዴሞክራሲን እውን ለማድረግ ሁሉም በቀዳሚነት መተግበር ያለበት የሽግግር መንግሥት ማቋቋም ነው ብለዋል።

መንግሥት ቀዳሚ የሆነውን ተግባሩን በመርሳቱ ዜጐችን ሥጋት ላይ የጣለ በመኾኑ፤ የግድ ብቸኛው አማራጭ የሽግግር መንግሥት መመሥረት እንደሆነ የፓርቲያቸው አቋም መሆኑን ገልጸዋል። የሽግግር መንግሥቱ በአስቸኳይ ተፈፃሚ መሆን እንዳለበትም አመልክተዋል።

እነ አቶ በረከት ተከላከሉ ተባሉ

ባለፉት 27 ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ኹነኛ ሚና የነበራቸውና በሙስና ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸው በእስር ኾነው ጉዳያቸውን በፍ/ቤት ሲከታተሉ የቆዩት አቶ በረከት ስምኦን፤ እንዲከላከሉ ብይን የተሰጠው በዚህ ሳምንት አጋማሽ ላይ ነው።

ከጥረት ኮርፖሬት ጋር በተያያዘ በከፍተኛ የሙስና ወንጀል ከአቶ በረከትና አብረዋቸው የተከሰሱት አቶ ታደሰ ካሣ ላለፉት ሦስት ወራት ጉዳያቸውን ሲከታተሉ እንደነበር ይታወሳል።

የፍቃዱ ማህተመወርቀ እስር

የግዮን መጽሔት ማኔጂንግ ኤዲተር አቶ ፈቃዱ ማህተመወርቅ “እንቁ” የሚል መጠሪያ ባለው መጽሔት ከአምስት ዓመት በፊት ተመሥርቶ በነበረበት ክስ ምክንያት የሰባት ዓመት ፅኑ እስራትና ሰባት ሺሕ ብር እንዲቀጣ ውሳኔ ተላልፎበታል።

አቶ ፍቃዱ የእንቁ መጽሔት አሳታሚ ከ2002 – 2006 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ ከሽያጭና ከማስታወቂያ ያገኝ የነበረውን 629,140 ብር የገቢ ግብር ለገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን መክፈል ባለመቻሉና የግብር አዋጁን በመተላለፍ ክስ ተመሥርቶበት ጉዳዩን ሲከታተል ቆይቶ፤ ጥፋተኛ በመባሉ የሰባት ዓመት እስራትና የገንዘብ ቅጣቱ እንዲፈፀምበት የፌዴራል አንደኛ ደረጃ ፍ/ቤት እንደፈረደበት ታውቋል።

ክሱ እንዲቋረጥ ተደጋጋሚ አቤቱታ ሲያቀርብ የነበረው አቶ ፍቃዱ፤ አቤቱታው ተቀባይነት ሳያገኝ ቆይቷል። ከአንድ ዓመት ተኩል ወዲህ “ግዮን” የሚል መጽሔት አሳታሚና ማኔጅንግ ኤዲተር ሆኖ እየሠራ ነበር።

ፍቃዱ ማህተመወርቅ በኢትዮጵያ ነፃ ፕሬስ እንቅስቃሴ ውስጥ በተለያዩ አስተዋጽኦዎች የሚታወቅ ነው።

አሁን ከሚታወቅበት አሳታሚነቱ ባሻገር የተለያዩ መጽሔትና ጋዜጦች ታትመው እንዲሠራጩ በወኪል አከፋፋይነት ሲሠራ የቆየ ነው። ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ የነፃ ፕሬስ ውስጥ ከፍተኛ ሕትመት የነበራቸው ጋዜጦችን ጭምር ቀጣይነት ኖሯቸው እንዲታተሙ በማድረግም ጉልህ ድርሻ ነበረው።

ሰሞኑን በፍ/ቤት እሥራት ከተፈረደበት በፊት ሠጥቶ በነበረው መግለጫ፤ ከአምስት ዓመታት በላይ የቆየው የክስ ሒደት ይቋረጣል የሚል እምነት ነበረው። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!