Ethiopia Zare's weekly news digest, week 21, 2012 Ethiopian calendar

ከጥር 18 - 24 ቀን 2012 ዓ.ም. የሳምንቱን አንኳር ወሬዎች በጨረፍታ

የዓመቱ ሃያ አንደኛ ሳምንት አንኳር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክንውኖች

ኢዛ (ከጥር 18 -24 ቀን 2012 ዓ.ም.)፦ በቀዳሚው ሳምንት ብዙ መነጋገሪያ ኾኖ የሰነበተው የደንቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች እገታ አሁንም መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ ቀጥሏል። የታገቱ ተማሪዎች እንዲለቀቁ መንግሥት ላይ ግፊት የሚያደርጉ የተቃውሞ ሰልፎች በተለዩ የአማራ ክልል ከተሞች ተደርገዋል። በአዲስ አበባም ትናንት ጥር 24 ቀን 2012 ዓ.ም. ይደረጋል ተብሎ የነበረ ቢኾንም ሰላማዊ ሰልፉ አልተደረገም። ኾኖም ባሳለፍነው ሳምንት በዚህ ጉዳይ ላይ በተለየ የሚታየው ክስተት የመንግሥት ባለሥልጣናት በጉዳዩ ላይ መግለጫ መሥጠታቸው፣ የአማራ ክልል ጠንከር ያለና ተማፅኖም የነበረው መግለጫ ማውጣቱ ሊጠቀስ ይችላል። የታገቱ ተማሪ ወላጆችም ወደ አዲስ አበባ መጥተው ከባለሥልጣናቱ ጋር የተነጋገሩ ሲሆን፣ ታጋቾቹ በሕይወት አሉም ተብሏል። ግን አሁንም በዚህ እገታ ዙሪያ ያለው መረጃ ጥርት ያለ አይደለም የሚለው የብዙዎች ምልከታ እንደኾነ ይታወቃል።

ባሳለፍነው ሳምንት አነጋጋሪ ከነበሩ ጉዳዮች አንዱ የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረበው ሪፖርት ላይ ከ1600 በላይ ተጠርጣሪዎች መያዝ አልተቻለም ማለቱ ነው።

የሳይንስ ሚኒስቴር ያቀረበውም ሪፖርት ተጠቃሽ ነው። በሌላ ያሳለፍነው ሳምንት የፓርላማ ውሎ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚባል ደረጃ የሦስት ሚኒስትሮችን ሹመት እንዲጸድቅ ሲቀርብ የተቃውሞ አስተያየት የተስተናገደበት መኾኑን ነው።

ሌላው ሰሞናዊ አነጋጋሪ ጉዳይ የህዳሴ ግድብን በተመለከተ በዋሽንግተን የተደረገው ውይይት ስምምነት የሚደረስበት ይኾናል ቢባልም፤ በተጨባጭ ግን እንደታሰበው ሊኾን አለመቻሉ መታወቁ ነው። በመንግሥት ደረጃ የተሠጠው መግለጫ ደግሞ ስምምነት የተደረሰበት አለ፤ ያልደረስንባቸው ነጥቦችም አሉ የሚል ኾኗል።

የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የዓለማችን የሥጋት አጀንዳ የኾነው የኮሮና ቫይረስ ጉዳይ ኢትዮጵያንም ደፋ ቀና ማድረጉ አልቀረም። በዚህ ቫይረስ ተጠቅተው ይኾናል የተባሉ አራት ከቻይና የመጡ ኢትዮጵያውያን ተገልለው ምርመራ ተደርጐላቸው ነፃ ወጥተዋል። ጤና ጥበቃ ሚኒስትርም ቫይረሱ ቢከሰት በሚል ለይቶ የመመርመሪያና የማከሚያ ቦታ አሰናድቷል። ችግሩ ግን የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቻይና በረራዎቹን አለማቆሙ ወደ ኢትዮጵያ ቫይረሱ ሊመጣ ይችላል የሚለውን ሥጋት እንዲጨምር ማድረጉ ነው። አየር መንገዱ በኦፊሴል በረራውን እንደማያቋርጥ በመናገር፤ ጥንቃቄ ቫይረሱን በተመለከተ ጥንቃቄ እያደረግኹ ነው በማለት ማስታወቁ መነጋገሪያ መኾኑ አልቀረም።

የአገሪቱ የፖለቲካ ጉዳይ ከተነሳ፤ ከሰሞኑ የኦፌኮ አመራሮችና የጃዋር መሐመድ የዜግነት ጉዳይ ምርጫ ቦርድንም ጥያቄ እንዲያቀርብ ያስገደደው መኾኑ ነው። እንዲህ ካሉ የሳምንቱ ዜናዎችና ሌሎች ዘገባዎች በኢትዮጵያ ዛሬ ድረገጽ ዘጋቢዎች ተጠናክረው እንደሚከተለው ቀርበዋል።

እስካሁን በእገታ ላይ የሚገኙት ተማሪዎች

የደንቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የእገታ ዜና ከተሰማ ወዲህ ብዙ እየተባለ ነው። የታገቱ ተማሪዎችን ጉዳይ የሚያጣራ ቡድን መቋቋሙን መንግሥት ካስታወቀ በኋላ በጉዳዩ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ጉዳዩ ይመለከታቸዋል የተባሉ የመንግሥት ኃላፊዎች መግለጫ የሠጡት በዚሁ ባሳለፍነው ሳምንት ነው።

በሳምንቱ አጋማሽ ላይ መግለጫውን የሠጡት ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁን፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ዲኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ እና የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ጀኔራል ኮሚሽነር እንደሻው ጣሰው ነበሩ። በዚህ መግለጫ ላይ የእገታውን ጉዳይ አመላካች ናቸው የተባሉ ቀደም ያሉ መረጃዎች የተሠጡበት ነበር።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በብዙ የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች በተከሰቱ የጸጥታ ችግሮች ሳቢያ የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም በተመሳሳይ ያጋጠማቸው ችግር ለደኅንነታችን እንሰጋለን ያሉ ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲውን ለቀው ሲወጡ እንደነበረ የሚያስታውሰው መግለጫ፤ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ጥለው እንዳይሔዱ የፌዴራል ፖሊስ ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርጉ መቆየታቸውንም ያትታል።

የፌደራል ፖሊስ በአካባቢው ያለውን የጸጥታ መደፍረስ ከግምት ውስጥ በማስገባት ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲውን ጥለው ከወጡ ችግር ሊገጥማቸው እንደሚችል ሲያስጠነቅቅና መረጃ ሲሠጥ እንደነበረም ይጠቁማል።

ኾኖም ተማሪዎች በማይጠበቅ መንገድ በጋምቤላ በኩል ጉዟቸውን ሲያቀኑ አንፋሎ ወረዳ ሱዲ በምትባል ቦታ ላይ ችግሩ እንደተፈጠረ መግለጫው ያስረዳል። በተለይ አቶ ንጉሡ እንደገለጹት በተጠቀሰው አካባቢ ሰዎች መያዛቸው እንደተሰማ መመከላከያ ሠራዊት አሰሳ አካሒዶ 21 ተማሪዎችና ሌሎች ተጨማሪ ሰዎችን ማስለቀቁን ጠቅሰው፤ ባሳለፍነው ሳምንት መግለጫቸው ላይ ደግመው ተናግረዋል። እነዚህም 21 ተማሪዎች ተመልሰው ወደ ዩኒቨርሲቲው እንዲገቡ መደረጉንም ጠቅሰዋል። ይህም ቀደም ብለው በዚህ ጉዳይ የሠጡት መግለጫ ትክክል እንደነበር ያመለከቱበት ነው።

አቶ ንጉሡ እንደገለጹት ታገቱ በተባሉት ተማሪዎች ቁጥር ላይ ያለውን የተምታታ ጉዳይ በተለከተ በተለያዩ መንገዶች የሚገለጸው የታገቱት ተማሪዎች ቁጥር 17 ነው የሚባለው ላይ ጉዳዩ ሲጣራö ከዩኒቨርሲቲው ያገኘነው መረጃ የሚያሳየው 12 ብቻ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች መኾናቸውን ነው። 5ቱ ግን የዩኒቨርሲቲው ተማሪ ስለመኾናቸው መረጃ አልተገኘም ብለዋል።

በመግለጫው ላይ መታወቅ የቻለው ሌላው አኀዛዊ መረጃ ከዩኒቨርሲቲው የወጡት ተማሪዎች 800 የሚኾኑ ተማሪዎች መኾናቸውን ነው።

በጥምረት በተሠጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የገለጹት ደግሞ፤ እገታው ተፈጠረ የተባለበት አካባቢ የሕዝብ እንቅስቃሴን የሚገቱና ሕዝብ አላላውስ ያሉ አካላት መኖራቸውን ነው።

“በደምቢ ዶሎ አካባቢ ታጥቆ የሚንቀሳቀስ ኃይል ተደምስሷል። ተደምስሶ ግን አልቀረም። የተረፈው አሁን ራሱን አደራጅቶ በሽፍታ መልክ እየተንቀሳቀሰ ነው። መንግሥት ዝም አላለም” በማለት አክለዋል። እርምጃ ጭምር እየተወሰደ ስለመኾኑ በማመልከትም፤ እገታው የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችን ብቻ ሳይሆን፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን፣ የአካባቢው ነዋሪዎችን እንዲሁም ነጋዴዎችን ጭምር ያካተተ ስለመኾኑ አስረድተዋል።

ጥርት ባለ መንገድ መገለጽ የሚኖርበት ጉዳይ የተማሪዎቹ ደኅንነት ጉዳይ በመኾኑ፤ በዚህ ጉዳይ ላይ በመግለጫው ላይ የተሠጠው መልስ አሁንም ብዥታ ያለው ነው የሚል አስተያየት እየተሠጠበት ነው። የባለሥልጣናቱ መግለጫ ጥያቄ “በእጃችን በቂ መረጃ አለ። እነዚህ መረጃዎች ተገቢ ክትትል እየተደረገባቸው ነው የሚገኙት የሚል ነው። ከዚህ መግለጫ ጐን ለጐን ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት የተሠጠው ተጨማሪ ማብራሪያ ደግሞ ደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ በኅዳር ወር ገደማ በዩኒቨርሲቲዎች ግጭት ከተስተዋለባቸው ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ነበር። በዚህም የፌደራል መንግሥቱና የክልሉ የጸጥታ አካላት ዩኒቨርሲቲውን የመጠበቅና የማረጋጋት ሥራ እንዲሠሩ ፌደራል ፖሊስ ሙሉ በሙሉ እንዲቆጣጠረው መደረጉ ነው።

“በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በተፈጠረው ግጭት ምክንያት የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ግቢውን ለቀው ወደ ቤተሰቦቻቸው መሔድ ሲጀምሩ የአካባቢው ሕብረተሰብና የጸጥታ መዋቅሩ ተማሪዎቹ እንዳይሔዱ በማግባባትም ወደ ግቢ ሲመልሱ ነበር” የሚለው ይኸው መረጃ፤ በዚህ ሁኔታ ውስጥ የተወሰኑ ተማሪዎች ወደ ጋምቤላ አቅንተው በመጓዝ ላይ እያሉ የአካባቢው አንድ አመራር፣ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች፣ ወጣቶችና ልዩ ልዩ ነዋሪዎች እንዲሁም የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በአንፋሎ ወረዳ ሱዲ በተባለ ቦታ ኅዳር 25 ቀን 2012 ዓ.ም. ታግተው የነበሩ መኾኑን ያረጋግጣል።

የተማሪዎች መታገት ከተሰማበት ጊዜ ጀምሮ የመከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የጸጥታ አካላት ባደረጉት አሰሳ 21 ተማሪዎችና ተጨማሪ የአካባቢው ነዋሪዎች ተለቀው እንደነበር የሚያትተው ይኸው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መረጃ፤ አቶ ንጉሡ ከዚህ ቀደም የሠጡትን መግለጫ የሚያጠናክር ተደርጐ ተወስዷል።

በሌላ በኩል አንድ ከአባቷ ጋር ስትጓዝ የነበረች የአካባቢው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪና ሌሎች አምስት ወጣቶች የተያዙ መኾኑን ዘግይቶ ጥቆማው ደርሶ እየተጣራና ሥራ እየተሠራበት ይገኛል። እነዚህን መረጃዎች በመያዝ መረጃ የማጣራትና ተማሪዎቹን የማፈላለግ ተግባራት በተለያዩ አካላት ሲከናወኑ ስለመቆየታቸው፤ በዚሁ ጉዳይ ላይ እስካሁን ተሠሩ የተባሉትን ሥራዎች እውነታዎችን ይገልጻል የተባለው መረጃ ያስረዳል።

በተለያዩ መንገዶች እንደጠፉ የተገለጡ 17 ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መኾን አለመኾናቸውን ከዩኒቨርሲቲው የመረጃ ማዕከልና ከአገር አቀፍ ፈተናዎች ድርጅት ሲጣራ፤ ዩኒቨርሲቲው ከ17ቱ ተማሪዎች 12ቱ በዩኒቨርሲቲው ተመድበው በመማር ላይ የነበሩ መኾናቸውን መረጋገጥ መቻሉ ነው። ቀሪዎቹ አምስቱ በዩኒቨርሲቲ ስማቸው ያለመገኘቱን ይጠቅሳል። አጠቃላይ ስማቸው በሚዲያም ያልተገለጸ፤ ነገር ግን ወላጆች ልጆቻችን ጠፍተዋል ያሏቸው ሁለት ተጨማሪ ተማሪዎች በመገኘታቸውን ከዩኒቨርሲቲው ሲጣራ፤ ከእነዚህ ሁለት ተማሪዎችን ጨምሮ በተያየ መልኩ ከተገለጹት 19 ተማሪዎች ውስጥ 14ቱ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሲሆኑ፤ አምስቱ ግን የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች አለመኾናቸውን ይኸው ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት የወጣው መረጃ ይጠቁማል።

እስካሁን ድረስ በልዩ ልዩ መልክ እንደጠፉ የተገለጸው የተማሪዎች ቁጥር 19 ሲሆን፤ ልጆቻችን ወደ እኛ አልመጡም፣ ጠፍተውብናል ብለው ለአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ያቀረቡት ወላጆች ቁጥር 11 መኾኑንም ይጠቅሳል። በተለያየ መልኩ ጠፍተዋል ተብለው ከተገለጹት ተማሪዎች ውስጥ 9ኙ ወላጆቻቸው ሪፖርት አላደረጉም ወይም የወላጆቻቸውን አድራሻ ለማግኘት አለመቻሉን ይህ መረጃ ይገልጻል።

እንዲህ ያሉትን መረጃዎች የያዘው መግለጫና ተጨማሪ ማብራሪያዎች የተሠጡበት ጉዳይ ግን አሁንም እርጋታ አላገኘም። መግለጫና መረጃዎቹ ከመሥጠታቸው በፊት የጉዳዩን አሳሳቢነት በማጉላት በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች ሰላማዊ ሰልፎች ተደርገዋል። መንግሥትን የሚወቅሱ መልእክቶችም ተላልፈዋል።

የአማራ ክልላዊ መንግሥትም ጠንከር ያለ መግለጫ ያወጣበት ጉዳይ ነው። በተለይ የኢትዮጵያ ሕዝብ እገታው የተደረገበት ክልል ሕዝብ ከእኛ ጋር ይቁም በማለት በድርጅቱ ተዋንያኖች ለሕግ መቅረብ የሚኖርባቸው መኾኑንም ያንጸባረቁበት መግለጫ ነበር። አሁንም ግን የዚህ ጉዳይ መቋጫው ምን ይሆን የሚለው ጉዳይ እንደተንጠለጠለ ነው። እንደ መንግሥት ካጋጠሙ ችግሮች አንዱ ስለመኾኑ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን መግለጻቸው ተሰምቷል።

ከዚህም ሌላ ትናንት እሑድ ጥር 24 ቀን በተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች የታገቱ ተማሪዎች ይለቀቁ ዘንድ ሰላማዊ ሰልፎች ተካሒደዋል። ሰላማዊ ሰልፎቹ የተካሔዱት ካለፈው ማክሰኞ ጥር 19 ቀን ጀምሮ ሲሆን፤ በደብረታቦር፣ ሰቆጣ፣ ጐንደር፣ ኮምቦልቻ፣ ላሊበላና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ። (ኢዛ)

ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግና ለሕግ ማቅረብ ያልቻላቸው ተጠርጣሪዎች

ባሳለፍነው ሳምንት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስድስት ወር ሪፖርታቸውን ካቀረቡት ውስጥ የጠቅላይ ዓቃሴ ሕግ ይገኝበታል። ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ባለፉት ስድስት ወሮች የተለያዩ ሥራዎችን የሠራ መኾኑን በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ ተገለጸ። ቢሆንም የብዙዎችን ትኩረት የሳበው የሪፖርታቸው አካል ተጠርጣሪ ወንጀለኞችን ለመያዝ የገጠመውን ፈተና የተመለከተው እንደነበር ለመረዳት ተችሏል። ሪፖርቱ እንደሚያመለክተውም በተለያዩ ወንጀሎች ለምርመራና ለክስ ከሚፈልጉ 3 ሺሕ ተጠርጣሪዎች ውስጥ ወደ 1 ሺሕ 600 አካባቢ የሚኾኑትን ለሕግ ማቅረብ አለመቻሉን ነው።

በዚህ ጉዳይ በተሠጠ ተጨማሪ ማብራሪያ ልዩ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን አፈፃፀም ለማሻሻል ባለፈው በጀት ዓመት የተጀመሩና በበጀት ዓመቱ አዲስ የተከፈቱ ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና የሙስና ወንጀሎች ትኩረት በመሥጠት ሲሠራ መቆየቱን ነው። ኾኖም በተለያዩ ወንጀሎች ለምርመራና ለክስ ከሚፈለጉ 3 ሺሕ ተጠርጣሪዎች ውስጥ ለሕግ ማቅረብ የተቻለው 1 ሺሕ 404 የሚኾኑትን ነው የሚለው ሪፖርት፤ ከተጠርጣሪዎቹ መካከል 1 ሺሕ 600 ገደማ የሚኾኑትን ለሕግ ማቅረብ አልተቻለም ይላል። እነዚህም ተጠርጣሪዎች በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 827፣ በደቡብ ክልል 655፣ በኦሮሚያ 50፣ በአማራ 18፣ በትግራይ 4፣ በሶማሌ 33፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ 9 ተጠርጣሪዎች ክስ ተመሥርቶባቸው እንዳልቀረቡ ይኸው የዓቃቤ ሕግ ሪፖርት አሳይቷል።

ተጠርጣሪዎቹን ለሕግ ማቅረብ ያልተቻለው ክልሎችና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት ባመቻላቸው መኾኑን የሚያመለክተው ሪፖርት፤ ከሙስና ጋር በተያያዘም ከሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የተቀበሏቸው 360 መዛግብት ላይ ውሳኔ ለማሠጠት መሟላት ያለባቸው ጉዳዮች እየተሟሉ ስለመኾኑም በዚሁ ሪፖርት ተጠቅሷል።

የሁሉም የወንጀል ዐይነቶችን የማጥራት ምጣኔ 100 በመቶ ለማድረግ ታቅዶ፤ የምርመራ ሒደታቸው የተጠናቀቁ 27 ሺሕ 959 የክስ መዝገቦች ቀርበው 27 ሺሕ 684 መዛግብት ውሳኔ ተሠጥቶባቸዋል፤ 175 መዛግብት ደግሞ በሒደት ላይ ይገኛሉ፤ በዚህም የማጥራት ምጣኔው 99.01 በመቶ ደርሷል ብለዋል። ውሳኔ ካገኙት ውስጥ 19 ሺሕ 238 መዛግብት ክስ የተመሠረተባቸው ሲሆን፣ 8 ሺሕ 446 በተለያዩ ሕጋዊ ምክንያቶች የተዘጉ መኾናቸውንም ነው አቶ ብርሃኑ ያብራሩት። የማስቀጣት ምጣኔ በአማካይ 96.1 በመቶ ለማድረስ ታቅዶ፤ 94.02 በመቶ ተፈጽሟል ያሉት አቶ ብርሃኑ፤ በዚህም 32 ሺሕ 949 መዛግብት በክርክር ሒደት የነበሩ ሲሆን፣ 7 ሺሕ 335 መዛግብት ውሳኔ ሲያገኙ፤ ከእነዚህ ውስጥ 6 ሺሕ 897 መዛግብት የጥፋተኝነት፤ 438 መዛግብት ደግሞ የነፃ ውሳኔ ያገኙ ናቸው ብለዋል።

በሙስና ከገንዘብ ቅጣት 10 ሚሊዮን 476 ሺሕ እንዲሁም ክስ ከተመሠረተባቸው ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መደረጉን ገልጸዋል።

ተቋሙ በቀጣይ የተገኙ ጥንካሬዎችን በማስቀጠልና ችግሮችን ለመፍታት የቀጣዩ 10 ዓመታት እቅድ ማዘጋጀቱንም አስታውቀዋል። የተደራጁ ወንጀሎች፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ ሙስናና ክስ ተመሥርቶባቸው በቁጥጥር ሥር ያልዋሉት በሕግ ተጠያቂ የማድረግ ተግባራት በትኩረት የሚሠራባቸው ጉዳዮች እንደኾኑም አቶ ብርሃኑ አብራርተዋል። የምክር ቤቱ አባላትም ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ባቀረቡት ሪፖርት ላይ ጥያቄ አቅርበው ምላሽና ማብራሪያ ተሠጥቶባቸዋል።

በዚህ የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሪፖርት ላይ የፓርላማው አባላት የተለያዩ ጥያቄዎችን በማቅረብ ዓቃቤ ሕግ የሥራ ኃላፊዎች ምላሽ የሠጡበት ነበር። (ኢዛ)

የህዳሴ ግድብና ያልቋጨው የሦስቱ አገራት ውይይት

ከሳምንቱ ዜናዎች ውስጥ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ በዋሽንግተን ሲካሔድ የነበረው ውይይት ነው። ላለፉት ወሮች በተከታታይ በተለያዩ ከተሞች ሲካሔዱ የነበሩ የሦስቱ አገራት ውይይት መቋጫ ያገኛል ተብሎ ቢጠበቅም፤ አሁንም ሊቋጭ አለመቻሉ እየተገለጸ ነው። ሰሞኑንም በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ደረጃ በዋሽንግተን ዲሲ ሲካሔድ የቆየው የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ ድርድር መጠናቀቁ ከተገለጸ በኋላ ግን፤ በድርድሩ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የውኃ ሙሌትና አለቃቀቅ በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ትኩረት የተደረገ ሲሆን፤ በድርቅ ዓመታት፣ የተራዘመ ድርቅ እንዲሁም በተራዘመ ዓመታት አነስተኛ የወንዝ ፍሰት ወቅት የሚኖረው የአሞላለ ሥርዓት ላይ መሠረታዊ መግባባት ተደርሷል የሚል ነው።

ኾኖም ስምምነት ያልተደረሰባቸው ቀሪ ጉዳዮች መኖራቸውን የዋሽንግተኑ የሰሞኑ ውይይት ከተጠናቀቀ በኋላ የተሠጠ መግለጫ አመላክቷል። ስምምነት ያልተደረሰባቸው ጉዳዮች ደግሞ በቀጣይ በሚደረጉ ውይይቶች መፍትሔ ያገኛሉ ተብሎ ተገምቷል። የሙሌትና ውኃ አለቃቀቅ ዝርዝር ረቂቅ ሰነድ ጭምር የሚዘጋጅ መኾኑ መነገሩ ደግሞ፤ የውኃ ሙሌትና አለቃቀቅ ላይ የተደረሰ ስምምነት ስለመኖሩ አመላክቷል።

በህዳሴው ግድብ የውኃ አሞላልና አለቃቀቅ ላይ የሚደረገው ድርድር በግድቡ ብቻ ላይ የተወሰነ መኾኑን የሚገልጸው የውጭ ጉዳይ መረጃ ኢትዮጵያ ነባርና የወደፊት በዓባይ ወንዝ የመጠቀም መብት በሙሉ የሚያስከብር ማድረግ የኢትዮጵያ መንግሥት የማይቀየር አቋም መኾኑንም ይገልጻል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ባሳለፍነው ሳምንት ውይይት ካበቃ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን ይዘው የህዳሴን ግድብ ጎብኝተዋል።

በዚህ ጉብኝት የግድቡን ሥራ የሚያመለክት ሪፖርት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበ ሲሆን፣ ሕልምን እውን ለማድረግ ውጤታማ ሥራ የማከናወንን አስፈላጊነት አጽንኦት ሠጥተው ገልጸዋል ተብሏል። “የዛሬው ጉብኝቴ ከዚህ ቀደም ካደረግኩት የተሻለ አፈጻጸም ያየኹበት በመኾኑ አስደስቶኛል” እንዳሉ ለማወቅ ችሏል። ከዚህ ጉብኝት ጋር ተያይዞ በተሠጠ መረጃ የግድቡ ሥራ 71 በመቶ መጠናቀቁንና ከ2013 ዓ.ም. የግድቡ ሁለት ተርባይኖች ሥራ ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል። (ኢዛ)

የኮሮና ቫይረስ ጉዳይ ከኢትዮጵያ አንፃር

የኮሮና ቫይረስ በዓለም መነጋገሪያ ከኾነ ሰነባበተ። ቻይናን እየፈተናት ነው። ዓለምንም ሥጋት ውስጥ ከትቷል። ኢትዮጵያዊው የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የሁኔታውን አደገኝነት በተደጋጋሚ የገለጹ ሲሆን፤ ወደ ቻይና በረው ከቻይናው ፕሬዝዳንት ጆኒንግ ጋር መክረዋል።

የኮሮና ቫይረስ አሳሳቢነቱ የሚጐላው ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ደሃ አገሮች ቫይረሱ ቢከሰት የመስፋፋት እድሉ ከፍተኛ ስለሚኾን፤ የቅድመ ጥንቃቄ ጉዳይ በብርቱ ሊታሰብበት የሚገባ መኾኑ ነው። ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ መንገደኞቹን መመርመር ጀምራለችና በቀዳሚው ሳምንትም በኮሮና ቫይረስ በመያዝ የተጠረጠሩ አራት ኢትዮጵያውያን በአገር ውስጥ ምርመራ ነፃ መኾናቸው የተረጋገጠ ሲሆን፤ ለተጨማሪ ምርመራ የደም ናሙናቸው ወደ ደቡብ አፍሪካ የተላከው ናሙናቸው ነፃ መኾኑን በማረጋገጡ፤ በዚህ ቫይረስ ኢትዮጵያውያን ያለመያዛችው ታውቋል። የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በጉዳዩ ላይ ሠጥቶት በነበረው መግለጫ፤ እነዚህ ከቻይና ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ የነበሩ አራት ኢትዮጵያውያን የሰውነታቸው የሙቀት መጠን ከፍ በማለቱ በጥርጣሬ በኳረንቲን ተለይተው ሕክምናቸውን እየተከታተሉ እንደነበር ይታወሳል። ከቻይና ዉሃን ግዛት ዩኒቨርሲቲ ከመጡት ከእነዚሁ አራት ተማሪዎች መካከል አንዱ የጉንፋን መሰል ምልክቶች የታዩበት በመኾኑ ሌሎቹንም ሦስቱ ተማሪዎች አብረው የመጡ በመኾናቸው በማቆያ ማዕከል እንዲቆዩ ተደርጓል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ያለውን የምርመራ ሥራ በተመለከተ የተጓዦች የጉዞ መረጃና ከማን ጋር እንደተገናኙ የሚያሳይ መረጃ በመሰብሰብ የምርመራ ሥራውን በማከናወን ላይ ይገኛል። ለምርመራ ሥራው ለዚህ ሥራ በሦስት ፈረቃ ተጨማሪ ባለሙያዎች ተመድበው ምርመራና ክትትል እየተደረገ ነው።

በተለይም ከቻይና ለመጡ መንገደኞች በየዕለቱ ባረፉበት ቦታ ክትትል የማድረግ ሥራ እየተሠራ ሲሆን፤ በቦሌ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ጊዜያዊ የለይቶ መከታተያ ክፍልና የሰው ኃይልን ጨምሮ አስፈላጊው ግብአት በማዘጋጀት እየተሠራ ሲሆን፤ ከዚሁ ቫይረስ መከሰት ጋር ተያይዞ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ራሱን የቻለ ማረፊያ ማዕከል አዘጋጅቷል።

ከዚህም ሌላ በበሽታው ለተጠረጠሩ መንገደኞች የጊዜያዊ ማቆያ ማዕከል በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ውስጥ የተዘጋጀና 30 ለሚኾኑ በቫይረሱ የሚጠረጠሩ ታካሚዎችን የሚይዝ የለይቶ ማከሚያ የሕክምና ማዕከል የተሰናዳ ሲሆን፤ በጽኑ ለታመሙና ከፍተኛ የሕክምና ክትትል ለሚያስፈልጋቸው ታካሚዎች ደግሞ በቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል የተለየ ክፍል መዘጋጀቱ ነው የተጠቆመው።

በመንግሥት ደረጃ እንዲህ ያለው ዝግጅት እየተደረገ መኾኑ እየተነገረበት ባለበት ሁኔታ ግን፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቻይና የተለያዩ ግዛቶች የሚያደርገውን በረራ አለማቆሙ አነጋጋሪ ኾኗል። ብዙ አየር መንገዶች በረራዎቻቸውን እየሰረዙ ባሉበት ሁኔታ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግን በረራዎቹን ቀጥሏል። የብዙዎች ሥጋትም እነዚህ በረራዎች ለምን ማቋረጥ አልተፈለገም? የሚለው ነው። (ኢዛ)

አነጋጋሪው የጃዋር መሐመድ የፖለቲካ ተሳትፎና የዜግነት ጉዳይ

ከለውጡ ወዲህ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ስሙ ተደጋግሞ የሚነሳው ጃዋር መሐመድ የአክቲቪስትነት ቆቡን አውልቆ በፖለቲከኛነት ለመጓዝ የወሰነው ከጥቂት ወራት በፊት ነው።

በአዲሱ መለዮው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ተሳታፊ ለመኾን ያስችለኛል ብሎ የመረጠው ደግሞ ኦፌኮን ነው። በፕሮፌሰር መረራ ጉዲና የሚመራው ኦፌኮ (የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ) አቶ ጃዋርን እንደ አባል ተቀብሎ ለዚህም የፓርቲውን መታወቂያ ሠጥቶታል። የፓርቲው መታወቂያ ላይ ደግሞ ዜግነት ኢትዮጵያዊ የሚለው ተመልክቷል።

ይህም ከኾነ ከሁለት ወር በላይ የኾነው ሲሆን፣ የጃዋር አሜሪካዊነት ባልቀረበት በሕግም ኢትዮጵያዊ ዜግነት ስለመቀበሉ የሚያረጋግጥ መረጃ ሳይቀርብ በኦፌኮ የተፈጸመ ነው። ይህ እንደ ዋዛ የኾነ ነገር ግን በወቅቱም ስለሁኔታው የተለያዩ አስተያየት የተሠጠበት ሲሆን፣ በተለይ ጃዋር መሐመድ ኢትዮጵያዊ አለመኾኑ እየታወቀ ኦፌኮ ይህንን ለምን አደረገ የሚለው ጉዳይ ብዥታ እንደፈጠረ ቆይቷል።

“ይህ ለምን ኾነ?” የሚል ጥያቄ ያላቸው ወገኖች ኦፌኮ ከዚህ ቀደም እንዲህ ያለ መታወቂያ አለው ወይ? ወይስ ለአቶ ጃዋር ተብሎ የተደረገ ነው? ብለው ላቀረቡት ጥያቄ ምላሽ አልነበረም።

አሁን ላይ ግን የኦፌኮና የአቶ ጃዋር ጉዳይ ምርጫ ቦርድ ደርሷል። ቦርዱም ማብራሪያ ስለመጠየቁና ምላሹን እስከ ጥር 29 ቀን እንዲቀርብለት ኦፌኮን ጠይቋል።

ፕሮፌሰር መረራ ዜግነት አረጋግጣችሁ ነው ወይ ይህንን ያደረጋችሁት? ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ የሠጡት ምላሽ ቀደም ብሎ በፌዝ የተሞላ ሲሆን፤ አሁን ምላሻችንን እንሠጣለን ብለዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት ደግሞ ጃዋር መሐመድ አሜሪካዊነቱን ሊመልስ አዲስ አበባ ለሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ማመልከቱንና ለኢትዮጵያ የዜግነትና ኢሚግሬሽን ጽሕፈት ቤት ኢትዮጵያዊ ዜግነቱ ይመለስለት ዘንድ ማመልከቻ አስገብቷል ተብሏል። እነዚህ እርምጃዎች ዜግነቱን ለማስገኘት የማያስችል በቂ መረጃዎች እንዳልኾኑ የሕግ ባለሙያዎች ትንታኔ የሚያሳይ ሲሆን፤ የአሜሪካ መንግሥት ዜግነቱ እንዲነሳለት የፈቀደበት ማረጋገጫ ሊሠጡትና ይኸው መረጃ ለኢትዮጵያ መቅረብ ይኖርበታል በማለት ይጠቅሳሉ።

ስለዚህ አቶ ጃዋር እስካሁን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በሕግ ሊያሳትፈው የሚችል ነገር ያለመኖሩን የሚያመለክትና የዜግነቱ መመለስ ማረጋገጫ ስላልተሠጠው እስካሁን በፖለቲካ ውስጥ መሳተፉ፤ ኦፌኮም ይህንን ሳያረጋግጥ ማድረጉና የውጭ ዜጋን በፓርቲው አባልነት መመዝገቡ ሕገወጥ መኾኑን የሚያረጋግጠው የምርጫ ሕግን እንደተላለፈ የሚቆጠር ነው የሚለውን ምልከታ ሠጥቷል። በመኾኑም የምርጫ ቦርድ በሠጠው የጊዜ ገደብ የሚቀርብለት የኮፌኮ ምላሽ ምን ውጤት ያስገኛል የሚለው ጉዳይ የብዙዎች ጥያቄ ሆኗል።

ባሳለፍነው ሳምንት ፕሮፌሰር መረራ ለአንድ ጣቢያ በሠጡት ቃለምልልስ፤ አቶ ጃዋር ኢትዮጵያዊ መኾኑን ሊያረጋግጥልኝ ይችላል ያለውን መረጃ አቅርቦልናል ከማለት ባለፈ፤ ይህ ሰው መንግሥት ፈቅዶለት ወደ አገር የገባ መኾኑንም በማስታወስ ሞግተዋል። በሌላ በኩል ግን ኦፌኮ የኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ከተሞች ነዋሪዎች ጋር ሲያደርግ በነበረው ውይይት ጃዋር እንደ አንድ የምርጫ ተወዳዳሪ ሕዝብን ሲቀሰቅስ ከመገኘቱ ጋር ተያይዞም ይህ ይቻላል ወይ? የሚለውንም ጥያቄ ምርጫ ቦርድ ይመለከተዋል ወይ? የሚለው ጥያቄ መልስ የሚጠይቅ ኾኗል።

ይህ ጉዳይ ባለፈው ሳምንት ጐልቶ ውይይት የተደረገበት ሲሆን፤ እንደ አቶ ጃዋር ዜግነት የሌላቸው ኢትዮጵያውያን ጉዳዮችም መታየት አለበት የሚሉ አሉ። እንደ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ያሉ ታዋቂ ፖለቲከኞች በአሁኑ ወቅት ከፓርቲ ተሳትፏቸው የራቁት የውጭ ዜግነት ስላላቸው እንደኾነ የሚያስታውሱ ወገኖች፤ ለጃዋር የተለየ ነገር ይኖራል ብለው እንደማይጠብቁ ያመለክታሉ። (ኢዛ)

የሰንሻይን ባለቤት አቶ ሳሙኤል ታፈሰ የክብር ዶክትሬት ተበረከተላቸው

በኢትዮጵያ ሪልስቴት ኢንቨስትመንት ውስጥ ከሚታወቁ ኩባንያዎች ውስጥ አንዱ የኾነው የሰንሻይን ሪል ስቴት ባለቤትና ሌሎች ኩባንያዎችን በማካተት ሰንሻይን ኢንቨስትመንት ግሩፕ የተባለው ኩባንያ ፕሬዝዳንት የኾኑት አቶ ሳሙኤል ታፈሰ ከሊንከን ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ተበረከተላቸው።

ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያለው የኢንቨስትመንት ግሩፕ ባለቤት አቶ ሳሙኤል የክብር ዶክትሬቱ የተበረከተላቸው በሥራ ፈጠራና ሰንሻይን ፋውንዴሽን በሚል መጠሪያ በሚታወቀው የበጐ አድራጐት ድርጅታቸው ላበረከቱት አስተዋጽኦ እንደኾነ ታውቋል። አቶ ሳሙኤል በተለይ በበጐ አድራጐት ድርጅታቸው በሦስት የክልል ከተሞች በራሳቸው ወጪ በገነቡት ትምህርት ቤት 1300 የሚሆኑት የችግረኛ ልጆችን እያስተማሩ ሲሆን፤ ለእነዚህ ልጆችም በየወሩ 200 ብር የኪስ ገንዘብ በመሥጠት ጭምር ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ እያደረጉ ነው። ለዚህ ተግባራቸው ባለፉት ሦስት ዓመታት በየወሩ 850 ሺሕ ብር ወጪ እያደረጉ ነው። በሚቀጥለው ዓመትም በአንድ ሌላ ክልል ለተመሳሳይ አገልግሎት እየተገነባ ያለ ትምህርት ቤት ሲጠናቀቅ፤ ተጨማሪ 300 የችግረኛ ቤተሰብ ተማሪዎችን በማከል የሚያስተምሯቸውን ተማሪዎች ቁጥር 1600 እንደሚያደርሱ ይጠበቃል።

ከዚህም ሌላ 500 አረጋውያንን የሚይዝና 65 ሚሊዮን ብር ወጪ ይደረግበታል የተባለ የአረጋውያን መንደር በመገንባት ላይ ሲሆኑ፤ ግንባታው ካለቀ በኋላ 500ዎቹ መንከባከብ ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል።

የሊንከን ዩኒቨርሲቲ ይህንን የክብር ዶክትሬት ሲሠጣቸው ሌሎች ተግባሮቻቸውንም ከግምት በማስገባት እንደኾነ ታውቋል። ሊንከን ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬቱን ለአቶ ሳሙኤል የሠጠው ወኪሉ በኾነውና አዲስ አበባ የሚገኘው ዌስተርን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ነው። ከዚህ የክብር ዶክትሬት አሠጣጥ ጐን ለጐን አቶ ሳሙኤል የሕይወት ታሪካቸውን የሚዘክር “ተግባር” የሚል ርዕስ የጻፉትን መጽሐፍ አስመርቋል። በሰንሻይን ኢንቨስትመንት ግሩፕ ሥር ያሉት ኩባንያዎች ሰንሻይን ሪልስቴት፣ ሰንሻይን ኮንስትራክሽን፣ ሰን ሲስተር ኢንዱስትሪያል ላውንደሪ፣ ሰን ሲስተርስ ትሬዲንግ፣ ሰንሻይን ፋውንዴሽን የተባሉ ሲሆን፤ እነዚህ ኩባንያዎች ከ6,000 በላይ ሠራተኞችን ይዘዋል።

በሌላ ኢንቨስትመንት ደግሞ ማሪዮት ሆቴል መጠሪያ ያለው ሆቴል ግንባታ ያጠናቀቀ ሲሆን፣ ሁለተኛው ተማሪዎች ደግሞ በ2014 ግንባታው አልቆ ሥራ ይጀምራል። ከሒልተን ዓለም አቀፍ ሆቴል ጋር ባደረጉት ስምምነት በሐዋሳ ባለአምስት ኮከብ ሆቴል እየገነቡ ናቸው። ሰንሻይን ወርልድ ስፓ የተባለውም ፕሮጀክታቸው ግንባታው እየተጠናቀቀ ይገኛል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!